ቻይና እና ግዙፉ የመከላከያ በጀቷ
ረቡዕ፣ የካቲት 26 2006በቻይና እና በጎረቤቶችዋ መካከል እየተካረረ የሄደውን ውጥረት አስመልክቶ በቤይዢንግ የሚገኘው የሀገሪቱ አመራር በሰጠው መግለጫው ይህንን ልዩነት ለማባባስ አንዳንዶች የሚያደርጉትን ሙከራ ነቅፈዋል። ቻይና ከተነካች ምላሹን እንደምትሰጥም አመራሩ አክሎ አስረድቶዋል። የዶይቸ ቬለ ሩት ኪርኽነር እንደዘገበችው፣ በደቡብ ምዕራባዊ ቻይና ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በተጣለ ጥቃት 33 ሰዎች በመገደላቸው ለዘንድሮው የብሔራዊ ሸንጎ ጉባዔ ጠንካራ ጥበቃ ይደረጋል። ቻይና ባለፈው ዓመት ለወታደራዊ ወጪዋ በመቶኛ ሲሰላ ከአስር ከመቶ በላይ ነበር ያደገው። አዲሱ የጦር በጀት ለብሔራዊው ሸንጎ በሚቀርብበትም ጊዜ የመከላከያው ወጪ በጉልህ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ይሁንና፣ ወጪው በዝቷል በሚል የሚሰማውን ሂስ ቃል አቀባይዋ ይንግ ፉ አጣጥለውታል።
« ከታሪካዊ ተሞክሮአችን ስንነሳ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ጥንካሬ ሲኖር ብቻ መሆኑን ተረደተናል። ሕዝባችን ካለ ጠንካራ የመከላከል አቅም በሰላም ሊኖር እና ሊሰራ አይችልም። »
ቻይና ባለፈው ዓመት በተለይ ብዙ ገንዘብ ያወጣችው የባህር ኃይሏን በማስፋፋቱ ላይ ነበር። ብቸኛው የሕዝባዊት ቻይና ሬፓብሊክ አይሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በዚህ ሳምንት ነው ለሙከራ ወደ ምሥራቃዊ የቻይና ባህር የተጓዘው። በዚሁ አካባቢ ውጥረቱ በተካረረበት በአሁኑ ጊዜ ቻይና ሌሎች ተመሳሳይ መርከቦችንም ለመገንባት ዕቅድ ይዛለች። በሲንግሁዋ ዩኒቨርሲቲ እንግዳ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ሮስ የመርከቦቹ ግንባታ ዕቅድ በቻይና እና ጃፓን መካከል ካለው የግዛት ይገባኛል ንትርክ ጋ ግንኙነት አለው ይላሉ። ሁለቱ ሀገራትበምሥራቃዊው እና በደቡባዊው የቻይና ባህሮች በሚገኙ ሰው የማይኖርባቸው ደሴቶች የባለቤትነት ጥያቄ የተነሳ መወዛገብ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ ሆኖዋቸዋል።
« አሁን የምናየው ውጥረት እየተጠናከሩ ከሚመጡ ኃይላት ጋ ይፈጠራል ብለን ሁሌ የምናዛምደው ውጥረት ነው። ግዙፍ ወታደራዊ አቅም ወደ ግዙፍ የጥቅም ጥያቄ ያመራል፣ ግዙፍ የጥቅም ጥያቄም ከሌሎች ጋ ትልቅ ውዝግብ ያስነሳል። »
ቻይና በምሥራቃዊው የቻይና ባህር ባለፈው ህዳር ወር ሳይታሰብ አንድ የአየር ክልል መከላከያ ቀጠና ባቋቋመችበት ጊዜ ብዙ ወቀሳ ነበር የተፈራረቀባት። በደቡባዊው ባህሯም ተመሳሳይ ቀጠና ለማቋቋም ዕቅድ እንዳላት ግን ገና በግልጽ አልታወቀም። ይኸው የቻይና የራስ መተማመን ባካባቢው ትልቅ ስጋት ፈጥሮዋል። እርግጥ፣ ይህ ሁሉ ራስን ለመከላከል መሆኑን ቻይና አስታውቃለች፤ ግን፣ ከተናካች ምላሹን ከመስጠት ወደኋላ እንደማትል ቃል አቀባይዋ ዪንግ ፉ አስጠንቅቀዋል።
« አንዳንድ ሀገራት ከተነኮሱን እና ያካባቢውን ፀጥታ እና ሥርዓት ስጋት ላይ ከጣሉ ያኔ ቻይና አስፈላጊውን ርምጃ ትወስዳለች። »
ያለፈው ዓመት በአስር ከመቶ ጨምሮ ወደ 90 ቢልዮን ዩሮ ከፍ ያለው የቻይና የመከላከያ በጀት በዓለም ከዩኤስ አሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።
ሩት ኪርኽነር/አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ