1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና ከአንድ ልጅ በላይ መውለድ መፈቀዷ

ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2008

ከዓለም ሕዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውን የቻይናውያን ሥነ-ተዋልዶ ለመቆጣጠር በሚል የሀገሪቱ መንግሥት ዜጎች ከአንድ ልጅ በላይ እንዳይወልዱ አግዶ ነበር። አሁን በቻይና ማንኛውም ሰው ሁለት ልጅ መውለድ ተፈቅዶለታል። ቻይናን ለዚህ ውሳኔ ያበቃት በሀገሪቱ የሴቶች ቁጥር በማሽቆልቆሉ ነው።

https://p.dw.com/p/1GxRN
China Rudong Kinder Spielplatz
ምስል Getty Images/AFP/J. Eisele

[No title]

1.37 ቢሊዮን ነዋሪ ባላት ቻይና የቀድሞው አንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ብቻ መውለድ የሚፈቅደው ደንብ ወደ ሁለት መቀየሩ ባሳለፍነው ሐሙስ ይፋ ሆኗል። ምክንያት? በቻይና ከወጣቶች ይልቅ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች መበራከታቸው። የቀድሞው ደንብ በእርግጥ በከፍተኛ ፍጥነት ያድግ የነበረውን የቻይና ሕዝብ ቁጥር መግታት ችሏል። ሆኖም ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት የሠራተኛ ኃይል እንዲቀንስ ማድረጉ አልቀረም። አሁን የቻይና መንግሥት ማንኛውም ቻይናዊ ሁለት ልጅ መውለድ ይችላል ሲል ይፋ ያደረገውን አዲስ ውሳኔ በርካታ ቻይናውያን በደስታ ተቀብለውታል።

«ገንዘቡ የሚገኝ ከሆነ ሁለተኛ ልጅ መውለድ መፈቀዱን በጣም ጥሩ ውሳኔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እያረጀ የመጣው ማኅበረሰብ በዛው እንዳይቀጥል ይረዳል። በተጨማሪም በቻይና መሥራት የሚችለውን ኃይል ያጠናክራል። እኔ በበኩሌ አንድ ቤተሰብ ሁለት አለያም ሦስት ልጆች እንዲኖሩት ነው የምፈልገው፤ ሕይወት እንዲያ ነው።»

China Rudong Kinder
ምስል Getty Images/AFP/J. Eisele

በርካታ ቻይናውያን የቀድሞውን አንድ ልጅ ብቻ መውለድ የሚፈቅደውን መርኅ ከእግር ኳስ አሰላለፍ ጋር በማመሳሰል 4-2-1 እያሉ ነበር የሚዘባበቱበት። በአብዛኛው የቻይና ቤተሰብ ውስጥ የሚካተቱትን አራት አያቶች፣ ሁለት ወላጆች እና አንድ ብቸኛ ልጅ ለመግለጥ በሚልም ነበር 4-2-1 ማለታቸው። ይህ ሁናቴ በቻይና ምን ያህል እድሜያቸው የገፉ ሰዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ መበራከታቸውን አመላካች ነው።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1949 የቻይና ኮሙኒስት መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ሰሞን የቻይናውያን ቁጥር እንዲበራከት ያበረታታ ነበር። ሆኖም ከ20 ዓመታት ግድም በኋላ በ1970ዎቹ «የአንድ ልጅ መርኅ» የሚለውን ውሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔው የተላለፈው በቻይና 400 ሚሊዮን ግድም ወሊድን ለመቆጣጠር ታስቦ ነበር። አሁን ደግሞ ቻይና እያደገ ከመጣው ኢኮኖሚዋ አንፃር በርካታ ወጣት የሰው ኃይል ያስፈልጋታል ተብሏል።

«መርኁ ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በ1980ዎቹ ነው የተወለድኩት፤ ለቤተሰቦቼም ብቸኛ ልጅ ነኝ። ብዙውን ጊዜ ብቸንነት ያጠቃኝ ነበር። ከእህትና ወንድሞች ጋር ማደጉን ነው የምመርጠው። ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ የገንዘብ ጫናውን መካፈል ይቻላል። በቤተሰብ ውስጥ ሁለት ልጆች መኖራቸው እጅግ የተሻለ ነው። እንዲያ ከሆነ በብቸኝነት ማደግ የለም።»

China Rudong Demografie Bevölkerung Senioren Ein-Kind-Politik
ምስል Getty Images/AFP/J. Eisele

ሁለት ልጅ መውለድ የሚፈቅደው አዲሱን ሕግ ተከትሎ የሕፃናት ቁሶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከወዲሁ ተገልጧል። በዛው መጠን ደግሞ የኮንዶም አምራቾች ንግዳቸው ይቀዘቅዝ ይሆናል ተብሏል።

በቻይና ቀደም ሲል ደንብ ተላልፎ ከአንድ ልጅ በላይ የወለደ ሰው በገንዘብ ይቀጣ ነበር፤ ገንዘብ ከሌለው ደግሞ በአስገዳጅ ሥራ። ይኽ ሕግ አሁንም ከሁለት ልጅ በላይ በሚወልዱት ላይ ተግባራዊ ሊሆን ይችል ይሆናል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል። ብዙዎች ግን ሁለት ልጅ መውለድ የሚፈቅደው ውሳኔ ዘግይቶ የተሰጠ ነው ባይ ናቸው።

ምንም እንኳን አሁን ሁለት ልጅ መውለድ ቢፈቀድም፤ በርካታ ቻይናውያን ለአራት ዐሥርተ ዓመት ግድም በአንድ ልጅ ብቻ እንዲወሰኑ መገደዳቸው፤ የኑሮው ውድነት፤ እንዲሁም በብቸኝነት የማደጉ ልምድ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ