1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኅዳር 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2014

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዛሬ ማታ አርሰናል ከኤቨርተን ጋር ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዳግም መሪር ሽንፈት ቀምሷል። በሻምፒዮንስ ሊጉ አሰልጣኙ ተስፋ ሰንቀዋል። የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ነገ እና ከነገ በስትያ ይቀጥላሉ። በቫለንሺያ ማራቶን ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም ፉክክር የሁለተኛ ደረጃን አግኝተዋል።

https://p.dw.com/p/43uG9
Champions League Spieltag 5
ምስል Peter Klaunzer/Keystone/picture-alliance/dpa

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቦ በመገስገስ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ወደ ቦትስዋና ተጉዞ ስለተቀዳጀው ድል በነገው ዕለት መግለጫ ይሰጣል። የዋሊያዎቹ የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር የደጋፊዎች ጉዞን የሚመለከት ሌላ መግለጫም በነገው ዕለት ይኖራል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዛሬ ማታ አርሰናል ከኤቨርተን ጋር ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዳግም መሪር ሽንፈት ቀምሷል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ግን አሰልጣኙ ተስፋ ሰንቀዋል። የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ነገ እና ከነገ በስትያ ይቀጥላሉ። በቫለንሺያ ማራቶን ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም ፉክክር የሁለተኛ ደረጃን አግኝተዋል።

አትሌቲክስ

ስፔን ቫሌንሺያ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ውድድር በወንዶችም በሴቶችም ኬንያውያን አትሌቶች አሸናፊ ኾነዋል። በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደግሞ የሁለተኛና ከዛ በታች ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በሴቶች ፉክክር፦ አትሌት እታገኝ ወልዱ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች።  በወንዶች ፉክክር ደግሞ 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ የሮጠው አትሌት ጫሉ ዴሱ በ2ኛ ደረጃ አጠናቋል። አትሌት በየኑ ደገፉ ውድድሯን በ3ኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሰአት፣ ከ23 ደቂቃ፣ ከ04 ሰከንድ ነበር። በዚሁ ውድድር አትሌት ረሂማ ቱሳ 4ኛ፤ አዝመራ ገብሩ 6ኛ፤ አዳነች አንበሳ 7ኛ እንዲሁም መሰረት ድንቄ 9ኛ ደረጃን አግኝተዋል። በወንዶች ፉክክር አትሌት አበበ ነግዎ አምስተኛ፣ ክንዴ አጣነው ሰባተኛ እንዲሁም ሄርፓሳ ነጋሳ ዐሥረኛ በመሆን አጠናቀዋል።  በተያያዘ የአትሌቲክስ ዜና፦ «ለኢትዮጵያ ሠላም እሮጣለሁ» በሚል መሪ ቃል የፊታችን እሁድ ከጥዋቱ አንድ ሰአት ጀምሮ በደብረዘይት ወይንም ቢሾፍቱ ከተማ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እንደሚኖር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

እግር ኳስ፥

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ምድብ ማጣሪያ ከሜዳው ውጪ ያደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታውን አስመልክቶ በነገው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል። መግለጫው ከ9፡00 ሰዓት ጀምሮ በሸራተን ሆቴል በላሊበላ አዳራሽ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ዐስታውቋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጨዋታ የቦትስዋና አቻውን ባለፈው ዐርብ 3 ለ1 ማሸነፉ አይዘነጋም። ቡድኑ ቦትስዋና ኦቤድ ኢታኒ ቺሉሚ ስታዲየም ላይ ያገኘው ድል በኮስታሪካ አዘጋጅነት በ2022 ለሚካሄደው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። በቦትስዋናው ግጥሚያ ለኢትዮጵያ የማሸነፊያዎቹን ግቦች ያስቆጠሩት አሪያት ኦዶንግ፤ ረድኤት አስረሳኸኝ እና መሳይ ተመስገን ናቸው። በነገው ዕለት የወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንም(ዋሊያዎቹ) ለአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር የደጋፊዎች ጉዞን አስመልክቶ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቅዳሜ ዕለት በዌስ ትሀም ዩናይትድ የ3 ለ2 ሽንፈት የገጠመው ቸልሲ የመሪነቱን ስፍራ ለማንቸስተር ሲቲ አስረክቦ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራቷል። ማንቸስተር ሲቲ ዋትፎርድን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ1 ድል አድርጎ በ35 ነጥቡ የመሪነቱን ሥፍራ ተቆናጧል። ማንቸስተር ሲቲ ቸልሲን በ2 ነጥብ በልጦ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሊቨርፑል ጋርም በአንድ ነጥብ ብቻ ተራርቋል። ሊቨርፑል ዎልቨርሐምፕተን ላይ ባገኘው ብቸኛ ግብ የሁለተኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ቸልሲን ጉድ ያደረገው ዌስትሀም ዩናይትድ 27 ነጥብ ሰብስቦ እዛው ባለበት በአራተኛ ደረጃው ላይ ሰፍሯል።  አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቶትንሀም ትናንት ኖርዊችን 3 ለ0 ድል በማድረግ በ25 ነጥቡ የአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ስድስተኛ ከፍ ማድርግ ችሏል። አርሰናል ዛሬ ማታ ከኤቨርተን ጋር ይጋጠማል። ካሸነፈ ደረጃውን እስከ አምስተኛ ድረስ የማሻሻል ዕድል ይኖረዋል። በእርግጥ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በሚቀረው ቶትንሀም ውጤትም ይወሰናል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው በርንሌይ፤ ኒውካስል እና ኖርዊች ከ18ኛ እስከ 20ኛ ተደርድረዋል።

Großbritannien Fußball Chelsea Torwart Edouard Mendy
ምስል Shaun Brooks/Action Plus/picture alliance

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድን 3 ለ2 ያሸነፈው ባየርን ሙይንሽን በ34 ነጥቡ በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 30 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። በርካታ ግብ በተንበሸበሸበት የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያ ባየር ሌቨርኩሰን ግሮይተር ፊዩርትስን 7 ለ1 አንኮታኩቷል። ነጥቡንም 27 አድርሷል። ሌላ ትናንት የታየው አስደናቂ ግጥሚያ ፍራይቡርግ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ያደረጉት ነበር። በዚህ ጨዋታ ፍራይቡርግ 6 ግቦችን አስቆጥሮ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን የጎል ጎተራ አድርጎታል። በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፍራይቡርግ ከስሩ የሚገኘው ሆፈንሀይምን የሚበልጠው በ2 ነጥብ ነው። አውግስቡርግ፣ አርሚኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዩርትስ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ በተከታታይ ከታች ሰፍረዋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ።  በነገው ዕለት ፓሪስ ሳንጃርሞ ከክሉብ ብሩዥ እንዲሁም ላይፕትሲሽ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በተመሳሳይ ሰአት ምሽቱን ይጋጠማሉ።  ሊቨርፑል ከኤሲሚላን እንዲሁም ፖርቶ ከአትሌቲኮ ማድሪግ የሚያደርጉት ጨዋታም በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ካለቁ በኋላ ይከናወናል። አያክስ ከስፖርቲንግ እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቤሽክታስ ጋር ምሽቱን ይጋጠማሉ። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ማርኮ ሮስ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ጉዟቸውን በድል እንደሚያጠናቅቁ ተስፋ ሰንቀዋል። አምስቱንም ጨዋታዎቹን የተሸነፈው የቱርኩ ተጋጣሚያቸውን እንደሚያሸንፉ ርግጠኛ መሆናቸውን ገልጠዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንዶች ከምድባቸው ጥሩ ሦስተኛ ስለሆኑበአውሮጳ ሊግ 16 ተፎካካሪዎች ምድብ ውስጥ በደርሶ መልስ ይጫወታሉ።ሪያል ማድሪድ ከኢንተር ሚላን እንዲሁም ሻካታር ዶኒዬትስክ ከሸሪፍ ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያም በነገው ምሽት የሚከናወኑ ናቸው።

Russland WEB Arena Moskau
ምስል Dan Mullan/Getty Images

ረቡዕ ማታ በሚኖሩ ጨዋታዎች፦ባየርን ሙይንሽን ከባርሴሎና፤ ቤኔፊካ ከዲናሞ ኪዬቭ በሚያደርጉት ይጀመራል። በተመሳሳይ ሰአት አታላንታ ከቪላሪያል እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከያንግ ቦይስ ጋር ይጋጠማሉ።  ዛልስቡርግ ከሴቪያ እና ቮልፍስቡርግ ከሊል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎች የምሽቱ ድምቀቶች ናቸው። ቀደም ብሎ በሚኖሩ ጨዋታዎች፦ ጁቬንቱስ ከማልሞ እንዲሁም ቸልሲ ከዜኒት ሴንት ፒተርስበርግ የሚያደርጉትም ይጠበቃል።

የመኪና ሽቅድምድም

ትርምስምስ በተስተዋለበት የጂዳ ፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን አሸነፈ። ለጥቂት የተሸነፈው ማክስ ፈርሽታፐን ከ7 ጊዜያት ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን ጋር በነጥብ ተስተካክለዋል። ዘንድሮ ብርቱ ባላጋራ የገጠመው የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የፊታችን እሁድ በሚካኼደው የዱባይ ሽቅድምድም ድሉን ያስረክብ አለያም ያስጠብቅ ይሆናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ