1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አርባምንጭ አቅራቢያ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች 18 ሰዎች ሳይገድሉ እንዳልቀረ ተገለጸ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 20 2015

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ 18 ሰዎች በፀጥታ አባላት መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የግድያ ድርጊቱ የተፈጸመው በጋሞ ዞን አስተዳደር አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ ነው ፡፡

https://p.dw.com/p/4Vbj2
Äthiopien - Arba Minch
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ የተፈጸመው ጥቃት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ 18 ሰዎች በፀጥታ አባላት መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የግድያ ድርጊቱ የተፈጸመው በጋሞ ዞን አስተዳደር አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ ነው ፡፡

ከከተማው በዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  በሚገኘውና ሻራ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ/ም ምሽት ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተኩስ ልውውጡ የቀበሌው ነዋሪ የሆኑ አሥራ ስምንት ሰዎች በጸጥታ አባላቱ መገደላቸውንና ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸውን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ DW  ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ የደቡብ ክልል የምትገኘው የአርባ ምንጭ ከተማ
ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ/ም ምሽት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አርባ ምንጭ ከተማ አቅራቢያ ወሰዱ በተባለፈው እርምጃ 18 ያህል ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው የጋሞ ዞን አስተዳደርና  የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አባላት ወደ ቀበሌው መግባታቸውን ተከትሎ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ የግጭቱና የግድያው መንስኤ በአርባ ምንጭ ወረዳ ዙሪያ ሥር ሲተዳደር የቆየውና ሻራ የተባለው ቀበሌ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ይካለል በሚል በተነሳ አለመግባባት መሆኑን ነው የአይን እማኞች የገለጹት፡፡በህዝበ ውሳኔው ዙሪያ የዎላይታ እና የጋሞ ዞን ነዋሪዎች አስተያየት

ዶቼ ቬለ DW በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸው በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ይገኛሉ ሥለተባሉት ተጎጂዎች ሁኔታ ለመጠየቅ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ወንደሰን ወርቁ ጋር ደውሏል ፡፡ ይሁንእንጂ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ከደቂቃዎች በኋላ ደውሉልኝ ባሉት መሠረት ቢደወልላቸውም ሥልካቸው በመዘጋቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ የሆሰፒታሉ ባልደረባ ነኝ ያሉ አንድ የህክምና ባለሙያ  12 ሰዎች መሞታቸውና ሌሎች በጥይት ተመተው የመጡ 15 ሰዎችን ማየታቸውን  ለዶቼ ቬለ DW  አረጋግጠዋል ፡፡የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተቃዉሞና ወቀሳ

ዶቼ ቬለ DW  ለተጨማሪ አስተያየት የጋሞ ዞን ፖሊስንም ሆነ የዞኑ መንግሥት ኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር ቢደውልም የሥራ ሃላፊዎቹ ጥሪ ባለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያምሆኖ የዞኑ መንግሥት ኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በሻራ ቀበሌ ተከሰተ በተባለው ጉዳይ ዙሪያ በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ መግለጫ አውጥቷል ፡፡ መምሪያው በዚሁ መግለጫው በቀበሌው ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ለማፍረስና የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ ነበር ባለው ኃይል ላይ የተሳካ የኦፕሬሽን ሥራ መከናወኑን ገልጿል፡፡በተካሄደው ኦፕሬሽንም ድምፅ አልባ የሆኑ ስለታማ መሣሪያዎችን ጨምሮ  ክላሽ፣ ሽጉጥና በርካታ የግልና የቡድን ጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን መምሪያው አስታውቋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ  
ታምራት ዲንሳ