አንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሲታወሱ
ሐሙስ፣ ጥር 1 2017የቀድሞ ፖለቲከኛ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በተለይም በኢትዮጵያ ፓርላማ ስያደርጉ በነበረው ምክንያታዊ ሙግታቸው በበርካቶች ይታወሳሉ፡፡
ቡልቻ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ለግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ እገት ስማቸው በደማቁ ይነሳል፡፡ባለፈው ሰኞ ጠዋት በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይፋ የሆነው አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በፖለቲካውም ሆነ በምጣኔ ሃብት ዘርፉ ባበረከቱት ጉልህ አሻራቸው ይታወሳሉና በርካቶች ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በአቶ ቡልቻ ሞት ዴሞክራሲ ሻምፒዮናውን አጥቷል በማለት ሃሳባቸውን የገለጹም በርካቶች ናቸው፡፡
የአቶ ቡልቻ ፖለቲካዊ ተሳትፎና አስተዋጽኦአቸው
አቶ ቡልቻን በቅርበት የምያውቃቸው እና በአንድ የፖለቲካ ድርጅት እስከመታገል የደረሱት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና አቶ ቡልቻን ስገልጹ የኢትዮጵያን ፓርላማ እውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመስል ያስቻሉ ይሏቸዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ፓርላማ ህይወት ኖሮት ፓርላማ እንዲመስል ካደረጉት ውስጥ አንዱ ናቸው” የሚሉት ፕሮፈሰር መረራ በተለይም ከወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የሚያደርጓቸው ክርክሮች ቀልቡ የሚስቡ በማለት ገልጸውታል፡፡ “የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ የተሸለውን መብት እንዲጎናጸፍና የተሸለች አገር እንድትፈጠር የበኩላቸውን ጥረዋል” በማለት አቶ ቡልቻ በፖለቲካው ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አንስተዋል፡፡ “የጡረታ እድሜያቸውን በሚገባ ተጠቅመውበት ያለፉ” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል፡፡
ከመጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበሩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እስከ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌደን) ፓርቲ ምስረታ የዘለቀውን የፖለቲካ ህይወታቸውን አስታውሰው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የቅርብ ጓደኛቸውና የፖለቲካ ጓዳቸው አቶ ገብሩ ገብረመድህን፤ “ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ በፕሮፈሰር መረራ ጉዲና የሚመራውን በወቅቱ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ከተባለው የፖለቲካ ድርጅታችን ጋር የኦዴንን ስቀላቅሉ ብሎም በፓርላማ አጠገባቸው ስለነበርኩ ብዙ እንድንቀራረብ እድል ሰጥቶኝ ነበር” የሚሉት አቶ ገብሩ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ስር ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ያላቸው የፖለቲካ ፍላጎትን አድንቀዋል፡፡
አቶ ገብሩ አከሉ፤ “አገር ወዳድነታቸው ቀላል አይደለም፡፡ ግልጽም ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡ በተሌም ለኢትዮጵያ አንድነት ያላቸው እምነት ጽኑ ነበር” በማለት የፖለቲካ አመለካከታቸውን አጋርተውናል፡፡
የአቶ ቡልቻ የኢኮኖሚ ዘርፉ አስተዋጽኦ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሲራካስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ጥናት ተመራቂው አቶ ቡልቻ በ1960ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የዓለም ባንክ የአፍሪካ ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግል ባንኮች ግዙፉና ቀዳሚው አዋሽ ባንክ ሲመሰረት እሳቸው ከፊትለፊት ነበሩ፡፡ ባንኩን በዋና ስራ አስፈጻሚነትና በቦርድ ዳይሬክተርነት በመምራት በስኬት ጎዳና እንዲጓዝ ካደረጉት ከሳቸው ስም ቀድሞ የሚነሳ የለም፡፡ በ1997ቱ ምርጫ በትውልድ ስፍራቸው ምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ብርመጂ ወረዳ ተወዳድረው የኢትዮጵያ ፓርላማ የተቀላቀሉት ቡልቻ፤ በተባበሩት መንግስታትም አገልግለው ያውቃሉ፡፡
የቅርብ ጓደኛቸው አቶ ገብሩ አቶ ቡልቻ ከፖለቲካም በበለጠ በኢኮኖሚው በኩል ያለው አበርክቶአቸው እንደሚጎላ ነው አስተያየታቸውን ያጋሩን፡፡ “ከመጀመሪያው በፖለቲካ ውስጥ ያን ያህል ያልነበሩ አቶ ቡልቻ በሙያቸው አገራቸውን አገልግለዋል” ሲሉ ገልጸውአቸዋል፡፡ ገቢ መር ኢኮኖሚ እንዲፈጠርና የግል ድርጅቶች ስፍራ እንዲኖራቸው አሁን ላይ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰውን አዋሽ ባንክ በመመስረት አሳየይተዋልም ነው ያሉት፡፡
አቶ ቡልቻ ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ህልፈታቸው እስከተሰማበት ድረስ በጡረታ ዘመናቸውም በሚችሉት የማማከር ሚና አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተነግሮላቸዋል፡፡ ቡልቻ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት ነበሩ። የፊታችን እሁድ ጥር 04 ቀን 2017 ዓ.ም. መንግስታዊ ስርዓተ ቀብራቸው አዲስ አበባ ቦሌ ከሚሊኒየም አዳራሽ ሽንት እንደሚደረግላቸውም ተጠቁሟል፡፡
ስዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ፀሀይ ጫኔ