1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የጀርመን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓት 

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 20 2013

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ለምን አልሰራም የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ የማስጠንቀቂያ ደውል መስራት አልቻለም።በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ድምጽ የለም።በዚህ ምክንያት በጎ ፈቃደኖች ከቤት ቤት እየዞሩ ሰዉን ሲያሳውቁ ነበር።መንግሥት ዜጎች ማስጠንቀቂያው በእጅ ስልካቸው እንደደርሳቸው አቅዷል።

https://p.dw.com/p/3y96v
Deutschland Unwetterkatastrophe | Bad Neuenahr-Ahrweiler in Rheinland-Pfalz
ምስል Ferdinand Merzbach/AFP/Getty Images

አወዛጋቢው የጀርመን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓት 


ባለፈው ሰሞን በሁለት የጀርመን ፌደራል ክፍላተ ሃገር፣አደገኛው ጎርፍ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ አለመድረሱ ሲያነጋገር ቆይቷል። በዚህ ጉዳይ ሲወቀሱ የከረሙት የጀርመን ባለሥልጣናት ወደፊት ሊደርስ የሚችል አደጋን ለመከላከል ይረዳል ያሉት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዜጎች በስልካቸው እንዲደርሳቸው ወስነዋል።የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።የምዕራብ ጀርመኖቹ ፌደራዊ ክፍላተ ሃገር ራይንላንድፋልስና ኖርድራይንቬስትፋለንን ከዛሬ ከአስራ ሁለት ቀናት በፊት ያጠቃቸው ከባድ የጎርፍ አደጋ በህይወትም በንብረትም ላይ ያደረሰው ጉዳት በሃገሪቱ የመቶ ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል።ከሁለት ቀናት ከባድ ዝናብ በኋላ የተከተለው ጎርፍ የገደላቸው ሰዎች ብዛት አሁን ወደ 180 ተጠግቷል።ጎርፉ በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።በአደጋው መንገዶች ድልድዮች የባቡር ሀዲዶች እንዳልነበሩ ሲሆኑ የኤሌክትሪክ የኢንተርኔት እና የመደበኛ ስልክ አገልግሎቶችንም አቋርጧል።በአንዳንድ አካባቢዎች እነዚህ አገልግሎቶች  ቀስ በቀስ ቢጀምሩም እስካሁን መንገድ የተዘጋባቸው የኤሌክትሪክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ያልተቀጠለላቸው መንደሮች ብዙ ናቸው። ራይንላንድፋልስ በተባለው የጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ የሚገኘው የአርቫይለር ወረዳ ራድዮ ጣቢያችን ካለበት ከቦን ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። አር የተባለው ወንዝ የሚገኝበት ይህ ወረዳ ጎርፉ ክፉኛ ካጠቃቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።  ።አደጋው በደረሰበት ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን ለሊት ለሐሙስ አጥቢያ በወረዳው በሚገኘው የአር ሸለቆ ብቻ 132 ሰዎች ሞተዋል። የ66 ዓመቱ ቮልፍጋንግ ሁስተ የአርዋይለር ነዋሪ ናቸው። እንደ ሌሎቹ የወረዳዋ ነዋሪዎች ጎርፍ እንደሚመጣ ሰምተዋል።ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ግን የነገራቸው የለም። ገበያ ላይ በቀላሉ የማይገኙ ጥንታዊ መጻህፍት በመሸጥ የሚተዳደሩት ሁስተ በመጀመሪያ አህር ወንዝ አቅራቢያ ለሚገኙ ነዋሪዎች በድምጽ ማጉሊያ የተላለፈውን ጠንከር ያለውን የመጀመሪያው ማስጠንቀቂያ  ሰምተዋል።ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አለያም ፎቅ ቤቶች ካሏቸው ወደ ላይኛው የቤታቸው ክፍል እንዲወጡ የሚያሳስብ ነበር። 
«በመጀመሪያ የእሳት አደጋ ብርጌድ ወደኛ መጥቶ ከወንዙ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኙ በሙሉ እባካችሁ ቤታችሁን ለቃችሁ ውጡ አለያም ወደ ላይኛው የቤታችሁ ክፍሎች ተዛወሩ ሲል ተናገረ።ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ ባልሳሳት ለአጭር የአደጋ ማስጠንቀቂያ ድምጽ ተሰማ።የቤተ ክርስቲያን ደውሎችም በጥቂቱ ተደወሉ።ከዚያ በኋላ አበቃ።የሞት ዝምታ ነበር።ልክ እንደ አስፈሪ ፊልም ነበር።»
ማስጠንቀቂያው የተነገረው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነበር።ሁስተ ምድር ቤት ያስቀመጡትን መኪናቸውን ፈጥነው አውጥተው መንገድ ላይ ሲያቆሙ ውሐው ጉልበታቸው ድረስ ነበር።ከአምስት ደቂቃ በኋላ ቤታቸው ተመልሰው ወደ ውጭ ሲመለከቱ እንዲያ ተሯሩጠው ያወጡት መኪናቸው ተንሳፎ ውሐው ሲወስደው አዩ።የጥንታዊ መጻህፍት መሸጫ መደብራቸው በውኃው በመጥለቅለቁ መፃህፍቱ እንዳልነበሩ ሆኑ። እርሳቸው እንደሚገምቱት የደረሰባቸው ኪሳራ ከ200 ሺህ ዩሮ ወይም ከ235 ሺህ ዶላር በላይ ነው።ሁስተ እንዳሉት የማስጠንቀቂያው ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ነበር። እስካሁን በጀርመንና በጎረቤት ቤልጅየም ጎርፍ የገደላቸው ሰዎች ቁጥር ከ210 በልጧል። አሁንም 150 ሰዎች የት እንደደረሱ አይታወቅም።የደረሰው የኤኮኖሚ ኪሳራ በቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ነው።የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ለምን አልሰራም የሚለው ጥያቄ ብዙዎች የሚያነሱት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ የማስጠንቀቂያ ደውል መስራት አልቻለም።በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ድምጽ የለም። በዚህ ምክንያት በጎ ፈቃደኖች ከቤት ቤት እየዞሩ ሰዉ ማድረግ ያለበትን ሲነግሩ ነበር። 
ሁስተ እንደሚሉት የጎርፉን ፍጥነት መገመት የቻሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው።በተግባር እንደታየው ይላሉ ሁስተ ክፍለ ግዛቱ ማድረግ የነበረበትን በሰዓቱ አላደረገም።የጀርመን ባለሥልጣናት ከአውሮጳ የጎርፍ ማሳወቂያ ስርዓት  ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።ይህን መረጃም የጀርመን ባለሥልጣናት ባሉት መስመሮች  በማስተላለፋቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንዲሁም ስማርት ፎናቸው ላይ የአደጋ ማስጠንቀቂያ መተግበራያ የጫኑ በተጠንቀቅ ሲጠብቁ ነበር። ሆኖም እነዚህን መተግበሪያዎች ግን በስፋት ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ለችግሩ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታመናል።

Deutschland | Überschwemmungen in Schuld
ምስል Wolfgang Rattay/REUTERS
Deutschland | Überschwemmungen in Erftstadt
ምስል Thilo Schmuelgen/REUTERS
Deutschland | Überschwemmungen in Ahrweiler
ምስል Joachim Bywaletz/Xinhua/picture alliance

በጎርፉ ከመወሰድ ተርፈው በአፈር ደለልና በውኃ የተሞሉ ቤቶች እየፀዱ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የጉዳቱ መጠን ግልጽ እየሆነ ነው። አንዳንዶቹ ምንም አልተረፋቸውም።
«ሁሉንም በእጃችን ነበር የሰራነው።ሁሉም ሄደ»
በጀርመን ለአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ የተዘጋጁ ስርዓቶች በሙሉ ላለፈው ሰሞኑ ጎርፍ አለመስራታቸው ንዴቱን አባብሷል።የአደጋ መከላከያ አስተባባሪ ቶማስ ሊንትስ ሰዎች ቢበሳጩ ምክንያት አላቸው ይላሉ።
« ንዴቱን እረዳለሁ። እዚህ የተጋጋለው ስሜትም ይገባኛል ።ሰዎች እዚህ ህይወታቸው ተበላሽቶ ነው የሚያዩት። አንዳንዶቹ ዘመዶቻቸው ሞተውባቸዋል። ብዙዎች ሞተዋል።ንዴቱን በደንብ በደንብ እረዳዋለሁ። በሌላ በኩል እንደገና ደግሜ እናገራለሁ።ይህ ማንም አስቀድሞ ሊተነብዬው የሚችል አልነበረም።ውኃው ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በፍጥነት ነበር ወደ ላይ ከፍ ያለው።የውኃ መጠን መለኪያዎቹም አንድ ደረጃ ላይ ሲደርሱ መስራት አቆሙ።እነርሱ ለዚህ ዓይነት ሁኔታ የተሰሩ አይደሉም።አልተሰሩም ነበር። ማንም ይህን አስቀድሞ ሊያውቅ አይችልም ነበር። የአሁኑ ውኃ መጠን ባለፈው ጎርፍ ከነበረው በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ወይም ከዚያም በላይ ነበር።»  
294 አካባቢያዊና 107 የማዘጋጃ ቤቶች አስተዳደሮች በሚገኙባት በጀርመን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ያለ አንዳች ችግር እንደሚሰራ  የፌደራል ጀርመን የአደጋ መከላከያ ድርጅት በጀርመንኛ ምህጻር BKK ሃላፊ አርሚን ሹስተርም ተናግረዋል። ሆኖም በትክክል አደጋው ሊደርስ የሚችልበትን ቦታ ለይቶ ማወቅ ግን እንደማይቻል ነው ያስረዱት።
«አጠቃላይ የማስጠንቀቂያ ስርዓታችን ሙሉ በሙሉ ይሰራል።በሐሙስና በቅዳሜ መካከል 15o ያህል የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን አስተላልፈናል።አሰራሩ እንዴት ነው፥የጀርመን የአየር ንብረት ትንበያ መስሪያ ቤት ትንበያውን ያሳውቃል። ቀደም ባሉት ቀናት የነበረው ትንበያ ጥሩ ነበር።እርግጥ ነው ይህ ይደርሳል ብሎ፣ የትኛውን ቦታ በተለይ እንደሚያጠቃ በምን ያህል መጠንና እስከምን ድረስ ሊመታው እንደሚችል  በትክክል ማወቅ አይቻልም። »
ሹስተር እንሚሉት የጎርፉን አደጋ የተመለከተ መረጃ ወደ ጎርፍ መከታተያና መቆጣጠሪያ ማዕከላት ደርሷል።ማስጠንቀቂያው በአደጋ ማስጠንቀቂያ መተግበሪያዎችም ተሰራጭቷል።
« መረጃው ወደ ጎርፍ መከታተያ ማዕከላት  ይተላለፋል።እነርሱም ያስጠነቅቃሉ።ይህም ጥሩ ነበር።ከዚያ መረጃው ለወረዳ ባለሥልጣናት ይተላለፋል።እነርሱም በመቆጣጠሪያ ማዕከሎቻቸው አማካይነት የማስጠንቀቂያ ማስተላለፊያው ስርዓት መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ። ይህንንም አድርገዋል።ከዚያም ለመገናኛ ብዙሀን 150 ጊዜ መረጃው ተሰራጭቷል። በማስጠንቀቂያ መተግበሪያዎችም ተበትኗል።»
 ይሁንና ነገሮች መስራት እንደነበረባቸው ሊሰሩ አለመቻላቸውን ነው ሃላፊው ሹስተር ያስረዱት ።መስሪያ ቤታቸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ምን ያህል የማስጠንቀቂያ ደውሎች እንደተነሱ ለማወቅ እየሞከረ ነው ። ለወደፊቱም ዜጎች በተወሰነ አካባቢ ሊደርስ የሚችል አደጋ ማስጠንቀቂያ በእጅ ስልካቸው እንደደርሳቸው የማድረግ እቅድ መያዙን ተናገረዋል።የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ማስጠንቀቂያው ለዜጎች እንዲደርስ መወሰነታቸውን ተናግረዋል። ዜሆፈር እንዳሉት ወደፊት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ያሉትን አማራጮች መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። 
«ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉንም አስፈላጊ የመረጃ ማስተላለፊያ ና የማስጠንቀቂያ ስርዓቶች ኒና አፕ፣SMS የማስጠንቀቂያ ደውሎች ራድዮና ቴሌቪዥን በየመንደሩ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች የእሳት አደጋ ሠራተኖች ፖሊሶች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ መረጃዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ደግሜ አጽንኦት መስጠት እፈልጋለሁ።»

Deutschland, Esch  | Unwetter in Rheinland-Pfalz
ምስል Thomas Frey/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ