ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀዉስ እንድትወጣ ሁሉን አቀፍ ዉይይት መጠየቁ
ዓርብ፣ የካቲት 15 2016“ለኢትዮጵያ ሰላም የፖለቲከኞች መፍትሄ”
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ውይይት ተካሂዶ አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ እና ጸጥታ ቀውስ እንድትወጣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጠየቁ፡፡ ሰባት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን የወከሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በትናንትናው እለት አዲስ አበባ ውስጥ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው ይህ የተጠየቀው፡፡
ፖለቲከኞች ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር የካሄዱት ውይይት
ብሪቲሽ ካውንስል ተዘጋጀ በተባለው በዚህ የምክክር እና ገለጻ መድረክ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀምንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ፣ የአረና ትግራይ ፓርቲ ተወካዩ ገብሩ አስራት፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የእናት ፓርቲ እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም ፖለቲካኛ የሺዋስ አሰፋ በግል ተሳትፈው አዲስ አበባ ውስጥ መቀመጫቸውን ላደረጉ ከ10 በላይ ኤምባሲዎች ገለጻ እና ከወቅታዊ ችግሮች መውጫ የመፍትሄ አቅጣጫ ከጠቆሙት ናቸው ተብሏል፡፡
በውይይት መድረኩ ተገኝተው ገለጻውን ካደረጉ ሰባት ፖለቲከኞች አንዷ የሆኑት ዶ/ር ራሔል ባፌ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የምክክሩ ዋነኛ ዓለማ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ መገንዘብ ነው ብለዋል፡፡ “በምክክር መድረኩ የተገኙት ከ10 በላይ የሚሆኑ ኤምባሲዎች ተወካዮች ነበሩ፡፡ መረዳትም የፈለጉ አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን እንደሚመስል እንድናብራራላቸው ነው፡፡ የብሔራዊ ምክክሩ እየተሄደበት ያለው መንገድ ላይም ማብራሪያ ጠይቀውን ገልጸንላቸዋል” ነው ያሉት፡፡
በፖለቲከኞቹ የተነሱ አሁናዊ የፖለቲካ ተግዳሮቶች እና እልባቶቹ
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ስዊድን ኤምባሲ በምክክር መድረኩ ወኪሎቻቸውን ልከው ገለጻው ከተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡ ፖለቲከኛ ራሔል በመድረኩ ከተነሱ አበይት ሃሳቦች የተነሱትን ሲያስረዱም “አገሪቷ ብምን አቅጣጫ እየሄደች ነው በሚለውና በምን አይነት መንገድ ወደ ትክከለኛ መረጋጋት ማምጣት በሚቻልበት መንግድ ላይ ነው አስተያየት የጠየቁን፡፡ በዚህም ነጻና አካታች ውይይት ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ነው የተወያየነው፡፡
ከብሔራዊ ምክክር ሂደትም ጋር ተያይዞ አሁን ላይ መረጋጋት የተሳናቸው የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አብዛኛ ቦታዎችን ነጻና አካታች ውይይት ከማድረግ አኳያ ከተመከረባቸው ነትቦች ተጠቃሽ ነው” ያሉት ፖለቲከኛዋ የትግራይ ጦርነትን የቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበርና ተግዳሮቱም ተነስቶ ፖለቲከኞቹ ለተሳታፊዎች ሃሳባቸውን አጋርተዋል ብለዋል፡፡ ታጣቂዎች ጭምር የሚሳታፉበት፤ ምንገስትም በሀቀኝነት የሚወያይበት አገራዊ ምክክርም ተደርጎ ከወቅታዊ ችግሮች መውጣት የሚቻልበት አውድ ብፈጠጠር የሚሉ ሃሳቦችም በዚሁ መድረክ መንጸባረቁ ነው የተብራራው፡፡
መንግስት ለህዝብ እንዲሁም ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጆሮ መስጠት አለበት ያሉት ፖለቲከኛ ራሔል በነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከል የአለመደማመጥ ችግር እንዲቀረፍ ሃሳብ መነሳቱንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለአሁናዊው ቀውሶች ይዘው የቀረቡት መፍትሄ አሊያም ሰላማዊ የመፍትሄ ሂደቱን የሚያግዙበት መንገድ ላይ የገቡት ቃል ስለመኖር አለመኖርም የተጠየቁት ፖለቲካዋኛ፤ “እነሱ ትክክለኛ እና ግልጽ መረጃዎችን በአሁናዊ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ ማግኘት ፈልገው እንጂ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ከማመልከት አኳያ የገቡት ቃል አሊያም ያመላከቱት አቅጣ የለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ ከተደረገው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከበርካታ አገር ዲፕሎማቶች ጋር የሁለትዮች ምክክር ማድረጓ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ