1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ማመንጫዎች እና መሠረተ-ልማቶች ግንባታ 14 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017

ኢትዮጵያ ከናፍጣ ከሚመነጭ ብርሀን ከተዋወቀች ከ127 ዓመታት ገደማ በኋላም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ቀበሌዎች አሁንም ጭለማ ውስጥ ናቸው። ሀገሪቱ እየጨመረ የሚሔደውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ የኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለመገንባት 14 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያስፈልጋታል።

https://p.dw.com/p/4oxOm
ግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ
ኢትዮጵያ እየጨመረ የሚሔደውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ የኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለመገንባት 14 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያስፈልጋታል። ምስል Getty Images/AFP

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ማመንጫዎች እና መሠረተ-ልማቶች ግንባታ 14 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2017 በጀት ዓመት ለ200 የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ የማድረስ ዕቅድ አለው። በዕቅዱ መሠረት 140 ከተሞች ከብሔራዊ ቋት፣ የተቀሩት 60 ከተሞች ከጸሀይ ኃይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክ ያገኛሉ። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 43 የገጠር ከተሞች ኃይል ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ ባለፈው ሣምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።

“እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ተደራሽነት 54% ነው” ያሉት አቶ ሽፈራው “ኤሌክትሪክ ያገኙ ከተሞች ቁጥር 8, 245” መድረሱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ120 ሚሊዮን እንደበለጠ በሚገመትበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉት ደንበኞች ግን 5 ሚሊዮን ገደማ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ከ1999 ጀምሮ ተግባራዊ በምታደርገው የገጠር የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ መርሐ-ግብር ኃይል ያገኙ ከተሞች ቁጥር ቢጨምርም አሁንም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ቀበሌዎች ጭለማ ውስጥ ናቸው። በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ባለፉት 14 ገደማ ዓመታት ለገጠር የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ 15 ቢሊዮን ብር መንግሥት ወጪ አድርጓል።

ባለፉት አምስት ገደማ ዓመታት መንግሥት “በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ ሲመድብ ነበር” ሲሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክቶች ፖርትፎሊዮ ሥራ አስፈጻሚ ክንፈ ነጋሽ ተናግረዋል። ይሁንና የሚመደበው ገንዘብ ሥራው ከሚጠይቀው ወጪ አንጻር ባለመመጣጠኑ “የምናቅዳቸው ከተሞች እየቀነሱ መጥተዋል” በማለት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት ከተሞች 65% ከብሔራዊ ቋት የተቀሩት 35% ጸሀይን ከመሳሰሉ አማራጮች የሚመነጭ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ አቅዳለች። ዕቅዱን ለማሳካት 6.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሎ ቢሰላም በተለያዩ “ተለዋዋጭ” ምክንያቶች ሲከለስ ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን አቶ ሽፈራው ተናግረዋል።

በመንግሥት በጀት እና ዓለም ባንክን ከመሳሰሉ ተቋማት በሚገኝ ብድር ኤሌክትሪክ ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ግን የዜጎችን ፍላጎት መሙላት አልቻለም። ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሁለት ዓመታት የተሰበሰቡ ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች በቀረቡበት ወቅት በኃይል አቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለው አለመጣጣም ቁልጭ ብሎ ታይቷል።

ከንፋስ የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ
ከንፋስ፣ ከጸሀይ እና ከጂዖተርማል በግል አልሚዎች ኃይል ማመንጫዎች ለመገንባት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዕቅድ ዕክል ገጥሞታል።ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughn

የምክር ቤቱ አባላት የተወከሉባቸው የምርጫ ክልሎችን ጨምሮ ኤሌክትሪክ ያላገኙ ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች እና ከተሞች በርካታ መሆናቸውን ለኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ኤሌክትሪክ ከሀገሪቱ ማዕከላዊ ክፍሎች በራቁ አካባቢዎች በፍትኃዊነት ሊዳረስ ይገባል በማለት የሞገቱ የምክር ቤቱ አባላት የኃይል መቆራረጥ ያስከተላቸውን ችግሮች በተደጋጋሚ አንስተዋል።

የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማጠናከሪያ እና ማስፋፊያ መሠረተ-ልማቶች ጥያቄ በቀረበባቸው አካባቢዎች ሊገነቡ ይገባል የሚል ሙግት ገጥሟቸዋል። የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠት ግን የኢትዮጵያን አቅም የሚፈታተን ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ሲዓ “ከትራንስሚሽን እና ሰብስቴሽን ጋር ተያይዞ ወደ 5.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“በእኛ ግምት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በተጨማሪነት የሚመጣውን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ያስፈልጋል” ያሉት ኃላፊው በአጠቃላይ ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር ሀገሪቱ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከውኃ 5,600 ሜጋ ዋት፣ ከነፋስ 404 ሜጋ ዋት እንዲሁም ቆሻሻ በማቃጠል ከሚፈጠር ሙቀት 25 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል። ግማሽ ያክሉን የሚያመነጨው ግብጽ በአይነ ቁራኛ የምታየው ታላቁ የኅዳሴ ግድብ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ተናግረዋል።

የግድቡ “የማመንጨት አቅም 5,150 ሜጋ ዋት ነው” ያሉት አሸብር “ለምን ቀነሰ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ኢነርጂው አልቀነሰም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ግድቡ “ወደ 15,600 ጊጋ ዋት ሰዓት በዓመት” እንደሚያመነጭ ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው “6,000 ሜጋ ዋትም ቢሆን የሚያመነጨው ኢነርጂ ተመሣሣይ ነው። 15,670 ጊጋ ዋት ሰዓት ነው። ወደ ገንዘብ ወይም ወደ መብራት የሚቀየረው የሚመነጨው ኢነርጂ ነው እንጂ ሜጋ ዋቱ አይደለም” በማለት ተከላክለዋል።

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ
የታላቁ የኅዳሴ ግድብ “የማመንጨት አቅም 5,150 ሜጋ ዋት ነው” ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈባሚ አሸብር ባልቻ “ለምን ቀነሰ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ኢነርጂው አልቀነሰም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

አቶ አሸብር የሚመሩት ተቋም ከሚያመነጨው ኃይል 85% ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሸጥ ነው። የስሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ሣፋሪ ኮምን የመሳሰሉ ከፍ ያለ ኃይል የሚጠቀሙ ተቋማት በአንጻሩ ኤሌክትሪክ በቀጥታ ከተቋሙ ይሸምታሉ።

በ2011 በጀት ዓመት 6.2 ቢሊዮን ብር የነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገቢ በ2016 ወደ 27 ቢሊዮን ብር አድጓል። ይሁንና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሸብር ባልቻ እንዳሉት ተቋሙ አሁንም ከኪሳራ አልተላቀቀም። በዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ መሠረት በ2012 በጀት ዓመት 30 ቢሊዮን ብር የነበረው የተቋሙ ኪሳራ በ2016 ወደ 10 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

“የሀገር ውስጥ ብድር አለብን፤ የውጪ ብድር አለብን። ለብድር ወለድ እንከፍላለን። እንደዚሁም በምንዛሬ ለውጥ የሚመጣ ኪሳራ አለ” ያሉት አሸብር ኩባንያው ለሚያከናውናቸው ግንባታዎች የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ከውጪ ሀገር የሚገዛ በመሆኑ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ለውጥ ሲደረግ “የተቋሙ ኪሳራ እየጨመረ ነው የሚሔደው” ሲሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 790 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ አጠቃላይ ሀብት ያለው ተቋም ነው። በቅርቡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር ከተካተቱ አንዱ የሆነው ተቋም የነበረባቸው ከፍተኛ ዕዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ከተዘዋወረላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ይገኝበታል።

አቶ አንዱዓለም ሲዓ “ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት በአጠቃላይ 454.7 ቢሊዮን ብር የሚሆን ዕዳ ነው” ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደተዘዋወረ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው “ወደ 263 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር” መዘዋወሩን መንግሥት ለሚያደርገው ድጋፍ በበጎ ማሳያነት ጠቅሰዋል።

በሥርቆት ምክንያት የወደቀ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ
ግጭት ውስጥ የሚገኙት አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸም የመሠረተ ልማት ሥርቆት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፈተና ሆኗል። ምስል Esayas Gelaw/DW

የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥርቆት ሌላው መንግሥታዊውን ተቋም እየተፈታተነ የሚገኝ ጉዳይ ነው። ችግሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አሸብር “ከፍተኛ ጥፋት” ሲሉ ገልጸውታል። የኃይል ማስተላለፊያ ማማዎች ሥርቆት እና የመሠረተ-ልማት ውድመት መበርታቱን ያስታወሱት ኃላፊው በአማራ ክልል የሚገኘው “አዘዞ ጭልጋ ሰብስቴሽን ከሁለት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ” ቢጠናቀቅም “የመሥመር ዝርጋታው ሙሉ በሙሉ ባለማለቁ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እየገባን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“የሠራንውም የኮንዳክተር እና የማስተላለፊያ መሥመር እየተዘረፈ ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው “ፕሮጀክቱ ከ80% አፈጻጸም ወደ 60% እየወረደ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “በዋናነት ችግሩ የጸጥታ ነው” ያሉት አቶ አሸብር መፍትሔ ለማበጀት “የዓለም ባንክ ቀጥታ ለጎንደር ከንቲባ ደብዳቤ ጽፏል። ለክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ እንዲያግዙን ጥያቄ አቅርበናል” ሲሉ አስረድተዋል። ጉዳዩ እስካሁን እንዳልተፈታ ጠቅሰው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ በመንግሥት በጀት ሀገሪቱ ያለባትን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መቅረፍ አይቻልም የሚል መግባባት ያለ ይመስላል። ባለሥልጣናቱ በተለያዩ አሠራሮች የውጪ ባለሐብቶች እና የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፉ ይሻሉ። በቅርቡ የተከናወነው የታሪፍ ጭማሪ፣ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ እና መንግሥት የሚያደርጋቸው የሕግ ማሻሻያዎች የባለወረቶችን ቀልብ ይስባሉ የሚል ተስፋ አላቸው።

እንዲያም ሆኖ ግን ከዚህ ቀደም በግል ኩባንያዎች የተጀመሩ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ስኬታማ አልሆኑም። በአሰላ ከንፋስ ኃይል ለማመንጨት የተጀመረው ዕቅድ ውል በገባው “ደካማ የሥራ ተቋራጭ” እና “በመንገድ ብልሽት” ምክንያት ዘግይቷል። በቱሉ ሞዬ ከእንፋሎት ኃይል ለማመንጨት በመጋቢት 2012 ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሥምምነት የተፈራረመው ኩባንያ የጸጥታ ችግር በአካባቢው በመኖሩ ሥራውን አቋርጦ ጥሎ ወጥቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ለሁለት ዓመታት የተካሔደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሁለት የኃይል ማመንጫዎች ለመገንባት ጨረታ ያሸነፉ “የግል ባለሀብቶች ሥራ እንዳይሰሩ እንቅፋት” እንደሆኑ የተቋሙ ኃላፊዎች አስረድተዋል። የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ጨምሮ የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የምታመነጭባቸውን ዘርፎች ለማስፋት ባላት ዕቅድ ላይ ጫና አሳድረዋል።  

የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ባለፉት 14 ገደማ ዓመታት ለገጠር የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ 15 ቢሊዮን ብር መንግሥት ወጪ አድርጓል።ምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ “አስር ዓመት እየጠበቀ ድርቅ” እንደሚያጠቃት የገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ “ወደፊትም ተጋላጭነታችን ስለሚሰፋ” በውኃ የኃይል ማመንጫ ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ “አማራጭ ማስፋት የግድ ነው” የሚል አቋም አላቸው።

ኢትዮጵያ ከ92% በላይ ኃይል የምታመነጨው ከውኃ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸብር “የተቋሙ ዕቅድ ወደ 70% ማውረድ” እንደሆነ ተናግረዋል። ከንፋስ፣ ከጸሀይ እና ከጂዖተርማል በግል አልሚዎች ኃይል ማመንጫዎች ለመገንባት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዕቅድ ዕክል ገጥሞታል።

አቶ አሸብር “በነበረው የሀገሪቱ ሁኔታ፣ ዓለም ላይ በተፈጠረው የማክሮ ፋይናንስ ሁኔታ እንዲሁም የሀገራችን የፋይናንስ ግሬድ በጣም ዝቅ በመደረጉ የግል አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው እየቀነሰ በመምጣቱ ዕቅዳችንን ባሰብንው ልክ መፈጸም አልቻልንም” ብለዋል።

መንግሥት ታላቁ የኅዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ እና አምስት ከንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የማጠናቀቅ ዕቅድ አለው። ተጨማሪ 1,000 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና 27 አዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢዎች በሦስቱ ዓመታት ይገነባሉ። “እነዚህ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሲጠናቀቁ የነበረውን ተደራሽነት ከ87% ወደ 91% ያሰፋዋል” የሚል ተስፋቸውን አቶ አሸብር ባልቻ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት እስካሁን ባለው አገልግሎት አዲስ አበባ፣ ሐረሪ ክልል እና ድሬዳዋ በኤሌክትሪክ አቅርቦት “የተሻለ ተደራሽ ሕብረተሰብ” ያለባቸው ናቸው። ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና አፋር ክልሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው “ዝቅተኛ” አገልግሎት ያገኛሉ።

እሸቴ በቀለ