1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ ዝግጁ ትሆን?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 21 2013

ለተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የካፒታል ገበያ የአዋጅ ረቂቅ ሲጸድቅ የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን ይቋቋማል። ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በሚሰጠው ፈቃድ በአክሲዮን በሚቋቋመው ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የተባለ ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ25 በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ይኖረዋል። ቀሪው 75 ከመቶ የውጭ ባለወረቶችን ጨምሮ በግሉ ዘርፍ የሚያዝ ይሆናል

https://p.dw.com/p/3nNzx
Symbolbild Börsen-Chart
ምስል picture-alliance/imageBROKER/S. Belcher

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ ዝግጁ ትሆን?

ኢትዮጵያ ከረዥም አመታት በኋላ እንደገና የምትጀምረውን የካፒታል ግብይት የሚያቋቁመው የአዋጅ ረቂቅ ከምኒስትሮች ምክር ቤት ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።ጉዳዩን የሚከታተሉ ባለሙያዎች የአዋጅ ረቂቁ "በቅርብ" ይጸድቃል ብለው ይጠብቃሉ። አዋጁ ሲጸድቅ "በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለመመሥረት ለሚያስፈልጉ መሠረታዊ ተቋማት እውቅና ይሰጣል" ሲሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ገበያ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ አሰፋ ሱሞሮ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን   

ረቂቁ አዋጅ ሆኖ ሲጸድቅ ከሚቋቋሙ መካከል አንዱ የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን ይሆናል። ይኸ ባለሥልጣን የአክሲዮን ግብይት የሚያካሒደው እና እንደ ኩባንያ ለሚቋቋመው የሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ፈቃድ የሚሰጥ ነው። አቶ አሰፋ እንደሚሉት የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን "በገበያው የሚሳተፉ የገበያው ተዋናዮችን በሙሉ የሚቆጣጠር፤ ፈቃድ የሚሰጥ፤ ፍትኃዊ፣ ግልጽ እና ውጤታማ ገበያ እንዲመሠረት የሚያደርግ ተቋም ነው።" "እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የካፒታል ገበያ እንዳይኖር ያደረገው የሕግ እና ቁጥጥር ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው" የሚሉት አቶ አሰፋ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የአዋጅ ረቂቅ ለዚህ መፍትሔ የሚያበጅ መሆኑን አስረድተዋል።

የካፒታል ገበያ ሥርዓት (Secondary Market) "ከዚህ በፊት ድርጅቶች ሲቋቋሙ የተሸጡ አክሲዮኖችን እንደገና ለሽያጭ እንዲቀርቡ ገዢዎችን እና ሻጮችን የሚያገናኝ ቦታ ወይም የገበያ መሥመር ነው" ሲሉ በኢስታንቡል ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ እና የስቶክ ኤክስቼንጅ ጥናት ባለሙያው ዶክተር አብዱ ሰዒድ ያስረዳሉ።

"በኢትዮጵያ አንድ ሰው አክሲዮን ከገዛ በኋላ ከዚያ ድርጅት መውጣት ቢፈልግ ወይም ብሩን ለሌላ ጉዳይ ፈልጎ መሸጥ ቢፈልግ እንደዚያ የሚያደርግበት አሰራር ለረዥም ጊዜ አልነበረም። ይኸ ገበያ ባለመኖሩ የአንድ የአክሲዮን ድርሻ የገበያ ዋጋ ስንት እንደሆነ የምናውቅበት መንገድ ለረዥም ጊዜ አልነበረም" የሚሉት ዶክተር አብዱ ወደፊት የሚቋቋመው የካፒታል ገበያ ግብይቱን ለማከናወን እንዲሁም "ድርጅቶች በተቻለ መጠን ፕሮጀክቶችን እና ማስፋፊያዎችን የሚደግፉበትን መንገድ እንዲያገኙ" ያግዛል።  

Symbolbild Abwärtstrend
የካፒታል ገበያ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የደረጀ የያንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት እና ጠንካራ የሕግ እና ቁጥጥር ማዕፍን ይሻል። ምስል picture-alliance/K. Ohlenschläger

የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ  

የአዋጅ ረቂቁ ሲጸድቅ በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቶት ግብይት ያከናውናል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የተባለ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ "የሚቋቋመው እንደ አክሲዮን ኩባንያ ነው። ስለዚህ ኩባንያውን በባለቤትነት የሚይዙ የተለያዩ ኢንቨስተሮች አሉ" የሚሉት አቶ አሰፋ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ25 በመቶ የማይበልጥ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

"ወደ 75 በመቶ የሚሆነውን የግሉ ዘርፍ ነው የሚይዘው። ከግሉ ዘርፍ ግለሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ፤ የግል ኩባንያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ጭምር በሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በባለቤትነት መያዝ ይችላሉ" ብለዋል።  

"የመንቀሳቀሻ ካፒታል ማሰባሰብ ወይም ሌሎች ኩባንያዎች ውስጥ ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ ተቋማት የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በሚያደርገው ግብይት ሊሳተፉ ይችላሉ።  "በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በጣም ብዙ ኩባንያዎች በአክሲዮን ተቋቁመዋል። ሁሉም ባንኮች፣ ሁሉም ኢንሹራንሶች፣ ውኃ እና ቢራ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአክሲዮን መልክ ተቋቁመዋል። እነዚህ በአክሲዮን መልክ የተቋቋሙ ኩባንያዎች ሊመዘገቡ ይችላሉ። ነገር ግን ምዝገባው አስገዳጅ አይደለም" ያሉት አቶ አሰፋ የኢትዮጵያ ሴኩዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በይፋ ሥራ ሲጀምር በትንሹ 50 ኩባንያዎች ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

Video Still TV Magazin The 77 Percent
"ምንም እንኳ ብዙ ሰው ባያውቀውም በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1956 አካባቢ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚያ በኋላም በ1965 የአዲስ አበባ የአክሲዮን ግብይት ቡድን የሚል ስያሜ ያለው የአክሲዮን ገበያ ነበር።" ምስል DW

አቶ አሰፋ "ሁሉም ባንኮች እና ሁሉም ኢንሹራንሶች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮም፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከኃይል ማመንጨት ጋር የተያያዙ ኩባንያዎች ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ላይ ራሳቸውን ማስመዝገብ ከፈለጉ ሊመዘገቡ ይችላሉ። በእኛ አስተሳሰብ 50 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ኩባንያዎች እንደ መነሻ ሊመዘገቡ ይችላሉ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግሉ ክፍለ ኤኮኖሚ አቅም ውስን በገያው ያለው ሚናም የተገደበ ነው። ይኸ የግሉን ክፍለ ኤኮኖሚ ጠንካራ ሚና የሚፈልገው የካፒታል ገበያ ምን ይፈይዳል የሚል ጥያቄ ያጭራል። ዶክተር አብዱ የኢትዮጵያ መንግሥት በፋይናንስ እና የኤኮኖሚ ዘርፎች ተግባራዊ ማድረግ የጀመራቸውን ማሻሻያዎች እንዲሁም አገሪቱ አሏት የሚሉትን ዕምቅ አቅም እየጠቀሱ ፋይዳ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።

የአፍሪካ አገራት በርከት ያሉ የካፒታል ገበያዎች ባለቤቶች ቢሆኑም ጥንካሪያቸውም ሆነ ኤኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በጎርጎሮሳዊው 1954 ዓ.ም የተቋቋመው የናይሮቢ የአክሲዮን ገበያ (Nairobi Stock Exchange) ዕድሜ ጠገቡ ነው። ዶክተር አብዱ እንደሚሉት ኢትዮጵያም ለእንዲህ አይነቱ ገበያ አዲስ አይደለችም።

"ምንም እንኳ ብዙ ሰው ባያውቀውም በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1956 አካባቢ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚያ በኋላም በ1965 የአዲስ አበባ የአክሲዮን ግብይት ቡድን የሚል ስያሜ ያለው የአክሲዮን ገበያ ነበር። ነገር ግን እነዚህ የአክሲዮን ገበያዎች ብዙም ያልተደራጁ፤ የሕግ ድጋፍ የሌላቸው የሰው ኃይል አቅርቦታቸውም እና ሽፋናቸው በጣም ዝቅተኛ ስለነበር በጊዜውም ባለው ሁኔታ እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበሩም" ይላሉ ዶክተር አብዱ።

የካፒታል ገበያ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የደረጀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት እና ጠንካራ የሕግ እና ቁጥጥር ማዕፍን ይሻል። ዶክተር አብዱ በመጪዎቹ ወራት ሥራ የሚጀምረው የካፒታል ግብይት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሊሰሩ ይገባል ከሚሏቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ይኸው የሰለጠነ የሰው ኃይል ጉዳይ ነው።

አቶ አሰፋ የቴክኖሎጂ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጦት ፈተና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይስማማሉ። ቢሆንም በእርሳቸው አባባል ግብይቱን ከመጀመር የሚያግዱ አይደሉም። በተለይ የውጭ ባለወረቶች በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እንዲሳተፉ መፈቀዱ ዘርፉ የዳበረውን ቴክኖሎጂ ከእጁ ለማስገባት በሒደትም ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መንገድ እንደሚከፍት አቶ አሰፋ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ