ኢትዮጵያ በምሥረታ ላይ በሚገኘው ካፒታል ገበያ ባንኮች ላቅ ያለ ሚና እንዲጫወቱ ትሻለች
ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2015የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚያዝያ 2000 ዓ.ም በይፋ ሥራ ሲጀምር የግብርና ውጤቶች ግብይትን ከመሠረቱ የመለወጥ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ገበያው በወቅቱ ሲመሰረት በአፍሪቃ የመጀመሪያው ነው። ይሁንና በየቦታው የሚካሔደውን እና የደላሎች ረዣዥም እጆች የተሰነዘሩበትን ግብይት ለመለወጥ ሲነሳ በርካታ አዳዲስ አሰራሮች መዘርጋት አስፈልጎት እንደነበር ምርት ገበያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከመሩ ኃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ያስታውሳሉ።
ለግብይት የሚቀርብ ምርት "ወደ መጋዘን በሚመጣ ጊዜ በላብራቶሪ ተፈትሾ ትክክለኛ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ፣ ላብራቶሪ የገቡ [የግብርና ምርቶች] የእርጥበት ቁጥጥር ተደርጎላቸው የሚቆዩበት ሁኔታ ከዚያ ውስጥ ደግሞ ለገዥዎች እና ለሻጮች ርክክብ የሚደረግበት ሥርዓት (clearing and settlement)" መዘርጋት ያስፈልግ እንደ ነበር አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል። ገበያው በገዥ እና ሻጭ መካከል መተማመን መፍጠሩን የሚገልጹት አቶ ኤርሚያስ የክፍያ ሥርዓት ጭምር ከተለምዷዊው ግብይት መቀየሩን ያስታውሳሉ።
ምርት ገበያው ዛሬ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ እና ሽምብራ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች የሚያገበያይ ሆኗል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ተቆጣጣሪ ሲሆን የሚሳተፉ ነጋዴዎችም ተመዝግበው ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ናቸው። የግብርና ምርቶች ከገበሬ ማሳ ተሰብስበው ለሽያጭ የሚቀርቡበትን ስልት በሕግ ወደሚመራ መደበኛ ግብይት የሚቀይር የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት "ቀላል" ይምሰል እንጂ "ውስብስብ ሥራ" ነበር።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሁለት እግሩ ከቆመ ከአስራ አምት ዓመታት በኋላ መንግሥት ተቀራራቢ ግን ደግሞ የበለጠ የተወሳሰበ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም በጥድፊያ ላይ ይገኛል። በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ "በእህል ቦታ አክሲዮን ይኖረናል፣ በቡና ቦታ አክሲዮን በሰሊጥ ቦታ ሌላ አይነት አክሲዮን ይኖረናል ማለት ነው" ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል። የካፒታል ገበያውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ዶክተር ብሩክ ታዬ የሚመሩት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ግብይቱ የሚመራባቸውን ሕግጋት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
የካፒታል ገበያውን ለማቋቋም ባለፈው ግንቦት 8 ቀን፣ 2015 አክሲዮን በይፋ መሸጥ ተጀምሯል። በገበያው መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል 25 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን የግሉ ዘርፍ 75 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል። የገበያውን የምሥረታ ሒደት የሚያስተባብሩት ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እና ባልደረቦቻቸው ባለፉት ሣምንታት አዲስ በሚቋቋመው ገበያ እንዲሳተፉ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር ምክክር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከፍተኛ የፕሮጀክት ማኔጀር የሆኑት ዶክተር ጥላሁን "ባንኮች የወደፊቱ የኢንቨስትመንት ባንክ እንደሚሆኑ፤ የወደፊቱ ሌላ ሁለተኛ ግብይቱን የሚያሳልጥ ተቋም እንደሚያቋቁሙ ነው የምንረዳው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
ባንኮች "በተለይ በዕዳ ገበያ (fixed income securities) ቀጥተኛ ተሳታፊ ስለሚሆኑ ለእነሱ የሚጠቅም መሠረተ-ልማት ሆኖ ነው የሚመጣው። ስለዚህ እኛም ገለጻ ስናደርግ ከሌሎች የፋይናንስ ጥቅሞቹ ይልቅ መሠረተ-ልማትነቱን ተረድተውት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ነው የምንጠይቀው" የሚሉት ዶክተር ጥላሁን ከፋይናንስ ተቋማት "በጣም ከፍተኛ ፍላጎት" መኖሩን ታዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በ2016 ሥራ ሲጀምር የመንግሥት የግምዣ ቤት ሰነዶች ለሽያጭ ይቀርባሉ። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚገኙ የሚገኙ "እስከ አምስት የሚሆኑ ኩባንያዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ገበያው ይገባሉ" ተብሎ እንደሚጠበቅ ዶክተር ጥላሁን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባንኮችም በገበያው በመሳተፍ ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ካፒታል ያሰባስባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት መካከል ናቸው።
"በተለይ በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ከካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የመጡትን መመሪያዎች ለማሟላት ብዙ የሚከብዳቸው አይደሉም" የሚሉት ዶክተር ጥላሁን "የፋይናንስ ሪፖርቶች ያወጣሉ፤ የኮርፖሬት አስተዳደራቸው ከሌሎች በተነጻጻሪ የተሻለ ነው። አክሲዮን ሽጦ የማስተዳደር ልምድ አላቸው። ስለዚህ እነሱን ወደ ገበያ ለማምጣት ከባድ ሆኖ አላገኘንውም" ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ገበያ በአሁኑ ወቅት 31 ባንኮች፣ 44 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ፣ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይገኛሉ። በተለይ ባንኮች ተጨማሪ ካፒታል ለማሰባሰብ ያላቸው ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እንዲያመሩ ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል። "አሁን በባንክ ዘርፍ ያለው ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል ከ240 ቢሊዮን ብር አይበልጥም" የሚሉት የፕሮጀክት ማኔጀር በባንኮች የባለ አክሲዮኖች ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች "ከአራት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ብቻ ተጨማሪ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ" ፍላጎት እንዳለ የሚጠቁሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። በገበያው ከአንድ ሺሕ በላይ ኩባንያዎች በአክሲዮን ተቋቁመዋል። ዶክተር ጥላሁን እንደሚሉት ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት "በሰፊውም ባይሆን ሥርዓት ባለው መልኩ ለሕዝብ አክሲዮን" የሸጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን የመመሥረት ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ባከናወኑት ጥናት በኢትዮጵያ "ከ400 ሺሕ በላይ ባለ አክሲዮኖች አሉ፤ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ አክሲዮኖች ገበያ ላይ ተሸጠዋል" የሚል መረጃ አግኝተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት መደበኛ ባልሆነ መንገድ በተካሔደ የአክሲዮን ግብይት ሦስት ቢሊዮን ብር ከአንዱ ወደ ሌላው መዘዋወሩን በምሳሌነት የሚጠቅሱት ዶክተር ጥላሁን እስማኤል "ይኸ ሲደረግ አክሲዮን የሚሸጡ ተቋማት ወደ ገበያ ሲመጡ ምን አይነት መረጃዎች መስጠት እንዳለባቸው የሚቆጣጠራቸው እና የሚመራቸው ተቋም አልነበረም" ሲሉ ገበያው ያለበትን ጉድለት ያነሳሉ።
"ምን አይነት የፋይናንስ ሪፖርት፣ ምን አይነት ኦዲተር እንደሚጠቀሙም የሚደነግግ አልነበረም" የሚሉት ዶክተር ጥላሁን እንዲህ አይነቱ ግብይት በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ብቻ እንዲገደብ ምክንያት እንደሆነም እምነታቸው ነው። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሲቋቋም ግን "የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢ የሆኑትን እንደ ብሮከር፣ ኦዲተር፣ ኢንቨስትመንት ባንክ የፋይናንስ እና የሼር አድቫይዘር" የመሳሰሉ ተሳታፊዎች በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ይገባሉ። አክሲዮኖቻቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እና ተቋማት "ምን አይነት መረጃዎች" ለባለወረቶች ማቅረብ እንደሚገባቸው በመወሰን የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሥርዓት እንዲበጅ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ይወጣል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በገበያው ለሽያጭ የሚቀርቡ ሰነዶች እና አክሲዮኖች የማሻሻጥ ሥራውን ለሚያከናውኑ ግለሰቦች እና ተቋማት በመጪዎቹ ቀናት ፈቃድ መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ባለሥልጣኑ መደበኛ ባልሆነ መንገድ አክሲዮኖች የሚያሻሽጡ ደላሎችን ተገቢውን ሥልጠና እና ፈቃድ በመስጠት ወደ ግብይቱ የማስገባት ዕቅድ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ብሩክ ታዬ ተናግረዋል።
ይኸን ውስብስብ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም ከሕግጋት እና ተቋማት በተጨማሪ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ይሻል። የኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ እሸቱ እንደሚሉት የካፒታል ገበያው ሥራ ሲጀምር "ብዙ የተለያየ መልክ እና ባህሪ ያላቸው አክሲዮኖች ወደ ገበያው መግባት አለባቸው።" የግብይቱ ጠባይ ግን በወረቀት መልክ የሚታወቁትን የመዋዕለ-ንዋይ ሰነዶች እና አክሲዮኖች ሙሉ በሙሉ ይቀይራቸዋል። በወረቀት መልክ የሚታወቀው አክሲዮን ወደ ዲጂታል ቅርጽ ተቀይሮ በአንድ የሚከማችበት ሰንዱቅ (Central securities depositories) እንደሚያስፈልግ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
ለኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ከእንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች እና በርካታ ሕግጋት ባሻገር ግብይቱን የሚያመቻቹ ብቁ ባለሙያዎች ማዘጋጀት ያስፈልገዋል። ባለፉት ሣምንታት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ኢንቨስትመንት ባንኪንግ እና ካፒታል ገበያን በመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎች እየሰጠ ነው። ሥልጠናዎቹ እንደ ብሎምበርግ እና ዴሎይት ያሉ ኩባንያዎች ጭምር የሚሳተፉባቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የምሥረታ ሒደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርገውን ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት አቶ ኤርሚያስ "እዚህ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ባህሪያቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው [ተቀባይነት] ለዚህ ብዙ ቁመና እንዳላቸው መረጋገጥ አለበት። ለገበያው ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ የተመሠከረላቸው ናቸው ብሎ ማመን አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን በተመለከተ የሚደረገው ውይይት፤ የሚዘጋጀው ሥልጠና በዋናነት አዲስ አበባ ላይ ያተኮረ ቢሆንም መሰል ገበያ በሌሎች አገሮች ያለውን ፋይዳ በተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዎንታዊ አቀባበል ገጥሞታል። "የዚህ ሙያ ያላቸው በዚህ ኢንዱስትሪ፤ በፋይናንስ፣ በባንክ እና በኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ፤ በአገራችን አሉ የሚባሉ ኤኮኖሚስቶች የፋይናንስ ገበያ ተንታኞች፣ የሌላውን አገር የገበያ ስኬት እያዩ አይናቸው ሲጓጓ የነበረ ሁሉ በተቻለ መጠን ሕጉ በሚጠይቀው መንገድ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ብቁ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተወዳዳሪም ሆኖ ለመገኘት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ አውቃለሁ" ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ