1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክን የሚቀላቀሉ 25 አገራት

ረቡዕ፣ ጥር 17 2009

ኢትዮጵያ የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክን ልትቀላቀል አቅዳለች። በመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ሰፋፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታ የምታካሒደው ኢትዮጵያ በባንኩ ውስጥ የሚኖራት ድርሻ ግን እስካሁን አልታወቀም። 

https://p.dw.com/p/2WObK
China AIIB Entwicklungsbank Jin Liqun
ምስል picture alliance/dpa/W. Hong

ኢትዮጵያ እና ግዙፉ የእስያ ባንክ

ኢትዮጵያ የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክን ከሚቀላቀሉ 25 አዳዲስ የአፍሪቃ፤አውሮጳ እና ደቡብ አሜሪካ አገሮች መካከል አንዷ ሆናለች። የዓለም ባንክን ይገዳደራል የሚል ወሬ የተናፈሰበት የእስያውያኑ ባንክ ቻይና የፈረጠመ ኤኮኖሚዋን የምትፈትንበት እና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያጋደለውን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቃናት የምትጥረበት ተደርጎ ተስሏል። የባንኩ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን ባለፈው ሰኞ እንደተናገሩት የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ አባላት መብዛት በ57 ባለድርሻ አባል አገራት የተመሰረተውን ተቋም የማበደር አቅም ያጠናክረዋል። 

ኢትዮጵያ፤ ሱዳን ፤አየርላንድ እና ካናዳ  በያዝንው የጎርጎሮሳውያኑ 2017 ዓ.ም. የእስያ የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክን ከሚቀላቀሉ አገሮች ጎራ እንደሚገኙበት ፋይናንሺያል ታይምስ የተሰኘው የብሪታኒያ ጋዜጣ ዘግቧል። ዋና ቢሮውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን የቀድሞ ኃላፊ ካርሎስ ሎፔዝ ከአፍሪቃ ሶስት አገራት ባንኩን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጠው በተለይ የኢትዮጵያን ተነሳሽነት «ታላቅ ጠቀሜታ» ያለው ብለውታል። ሰውየው የአፍሪቃ አገራት የቻይና ገንዘብ ተቀባይ ብቻ ሳይሆኑ የቤጂንግ ፖሊሲ ደጋፊ መሆናቸውን ጭምር ባንኩን በአባልነት በመቀላቀል ለማሳየት ፍላጎት እንዳላቸው ጨምረው ተናግረዋል። 

አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ቻይና-አፍሪቃ የተሰኘ የማማከር አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ተባባሪ መሥራች ናቸው። በቦን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የጥናት ማዕከል ቻይና በኢትዮጵያ ልሒቃን የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያላት ሚና ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የፒ.ኤች.ዲ. ምርምራቸውንም እየሰሩ ነው። ኢትዮጵያ በቻይና በተቋቋመው ባንክ ውስጥ መግባቷ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆናት የሚናገሩት አቶ አሌክሳንደር በባንኩ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሚና እንዲኖራት ያግዛታልም ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት አቶ አርከበ እቁባይ ኢትዮጵያ ባንኩን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየቷን ለፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ አረጋግጠውለታል። አቶ አርከበ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የባንኩ መሥራች የመሆን እቅዷ ቀነ-ገደቡ በማለፉ ሳይሳካ መቅረቱንም ጨምረው ገልጠዋል። አቶ አርከበ 60 በመቶ አገራዊ በጀቷን ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የምታውለው ኢትዮጵያ የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ ውስጥ የሚኖራት የድርሻ መጠን ላይ እስካሁን ሥምምነት አለመፈጸሙን ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒሥትሩ አማካሪ ባንኩ ለኢትዮጵያ አዲስ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆናት ተስፋ አድርገዋል። 

Infografik Chinas neue Seidenstraße Deutsch

በብሪታኒያው ኦቨርሲስ የልማት ማዕከል የልማት ፋይናንስ ባለሙያዋ አናሊሳ ፕሪዞን ዓለም ያለባትን የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ጉድለት ለመሙላት የእስያው ባንክ ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ እምነት አላቸው። 
«በመጀመሪያ ደረጃ የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ ለአፍሪቃ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ይሆናል። በዓለም ባንክ ግምት መሰረት አህጉሪቱ የመሰረተ-ልማት ልማት የ31 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለባት። ባንኩ የሚሞላው እንዲህ አይነት ጉድለቶችን ነው። ሁለተኛው ከሌሎች የገንዘብ ተቋማት እገዛ ማግኘት ያልቻሉ እቅዶችን ይኸው ባንክ መደጎም ይችላል።»

ቻይና የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ ከዓለም ባንክ እና ሌሎች መሰል የልማት ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር እንዲነፃጸር አትሻም። አገሪቱ የዓለም ባንክ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን እኩል አይወክልም የሚል ትችት ታቀርባለች። አቶ አሌክሳንደር ዓለም ባንክን የመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት የሚከተሉት ውስብስብ አሰራር ታዳጊ አገራት የሚፈልጉትን የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ለማግኘት ፈተና እንደሚሆንባቸው ይናገራሉ። በቻይና የተጠነሰሰው የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ ሥራውን ሀ ብሎ ከጀመረ አመት ሞላው። ደጋፊዎቹ አንደ አቶ አሌክሳንደር ሁሉ የዓለም አገሮች የሚፈልጉትን የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ክፍተት ይሞላል የሚል ተስፋ አላቸው። ተቺዎቹ በበኩላቸው ቻይና የኤኮኖሚ እና ሥልታዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምትጠቀምበት መሳሪያ አድርገው ያቀርቡታል። ከትችቱ ጎራ የተሰለፉቱ አደረጃጀቱ በውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ለቻይና ከፍ ያለ ድርሻ ይሰጣል የሚል ወቀሳም ያቀርባሉ። ባንኩን በጥርጣሬ የምታየው ዩናይትድ ስቴትስ ከምታነሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይኸው ያልተመጣጠነ የድምፅ አሰጣጥ ጉዳይ ይገኝበታል። አቶ አሌክሳንደር  እንዲህ አይነት ችግሮች ቢኖሩበት የአውሮጳ አገራት  የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክን አይቀላቀሉም ነበር የሚል መከራከሪያ አላቸው። 
የዓለም ባንክ፣ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም የእስያ እና የአፍሪቃ የልማት ባንኮች እያሉ ይኸ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄም አለ። ከአፍሪቃ አገራት ጋር የፈረጠመ ፖለቲካዊ ወዳጅነት ባፈራችው እና ጠንካራ የኤኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ቻይና ዋንኛ ባለቤትነት የተመሰረተው ተቋም የአፍሪቃ ልማት ባንክን የመጫን አቅም ይኖረው ይሆን? የልማት ፋይናንስ ባለሙያዋ አናሊሳ ፕሪዞን በፍጹም ይላሉ። እንዲያውም የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ ባለፈው ዓንድ ዓመት ከሌሎች አህጉራዊ የገንዘብ ተቋማት ጋር በትብብር ሲሰራ ተስተውሏል-እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ
«ይኽ ባንክ ከሌሎች የእስያ የልማት ባንኮች ጋር ባለፈው ዓንድ አመት በትብብር ሲሰራ ተስተውሏል። ከዚህ ባንክ ጋር እንደ ዓለም ባንክ እና የአውሮጳ የመልሶ ግንባታ እና ልማት ባንክ እና የእስያ ልማት ባንኮች ጋር በሁለትዮሽ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። እንዲህ አይነት ትብብር በእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ እና የአፍሪቃ ልማት ባንክ መካከል ይደረጋል ብዬ እጠብቃለሁ። ሌላው ነገር ስሙ እንደሚጠቁመው የእስያው ባንክ በመሰረተ-ልማት ላይ ብቻ የሚያተኩር ሲሆን እንደ አፍሪቃ ልማት ባንክ ያለ ተቋም ግን ከመሰረተ-ልማት ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል። የአፍሪቃ ልማት ባንክ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የማማከር የማሳደግ ሥራዎች ይሰራል። የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ በአንፃሩ እቅዶችን ከመደገፍ ባለፈ በፖሊሲ ማማከር ላይ ይሳረፋል ብዬ አልጠብቅም።» 

China AIIB Entwicklungsbank Eröffnungszeremonie
ምስል picture alliance/ZUMA Press/L. Weibing

ባንኩ የሚቀርቡለትን የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች የሚመዝንበት መሥፈርቶች እንደነ ዓለም ባንክ ከፍ ያሉ አይሆኑም የሚል ሥጋትም ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል ይደመጣል። የከባቢ አየር ጥበቃ፤የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ጸረ-ሙስና በእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ የመመዘኛ መሥፈርቶች ውስጥ ላይካተቱ ይችላሉ ባይ ናቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ወግነው የሚከራከሩት ባለሙያዎች።  አቶ አሌክሳንደር የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ ባንክ መርሆዎች እንዲህ አይነት ችግሮች የሉበትም ይላሉ። 

የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ በአንድ ዓመት ውስጥ ዘጠኝ የልማት እቅዶች ላይ እጁን ማስገባቱን ፕሬዝዳንቱ ጂን ሊኩን ተናግረዋል። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር ያቀደው ባንክ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። የባንግላዴሽ የኃይል ማከፋፈያ፤ የኢንዶኔዥያ ብሔራዊ የድሕነት ቅነሳ፤ የታጃኪስታን እና የፓኪስታን የመንገድ ግንባታ እቅዶች ባንኩ በብድር ከደገፋቸው መካከል ይገኙበታል። 


እሸቴ በቀለ 
አዜብ ታደሰ