ኢትዮጵያ የቻይና ብድሯን መክፈል ቢሳናት ምን ይፈጠራል?
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2011ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተሳተፉበት እና ከሚያዝያ 17 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሔደው የመቀነት እና መንገድ ዕቅድ ስብሰባ (Belt and Road Forum) ኢትዮጵያ ከቻይናው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ-ልማት ግንባታ ኩባንያ (State Grid Corporation of China) ጋር የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርማለች። ገንዘቡ ለ16 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ለኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የመሰረተ-ልማት ግንባታ ለማከናወን ሥራ ላይ እንደሚውል የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።
አራት ቢሊዮን ዶላር የወጣበት እና 752 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሯትን አገር ከዕዳ ጫና ውስጥ ከከተቱ ውድ ሥራዎች መካከል ቀዳሚው ነው። አንዴ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሌላ ጊዜ በአፋር ክልል በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ግልጋሎቱ ሲቆራረጥ የታየው ይኸ የባቡር አገልግሎት እስካሁን እዳውን ጨርሶ መክፈል አልቻለም። ኢትዮጵያ ከቻይና ያበጀችው ወዳጅነት ስኬታማነት ማሳያ ተደርገው ከሚቆጠሩ ሥራዎች መካከል ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተዘረጋው የምድር ባቡር አገልግሎት ይገኝበታል። የዓለም አቀፍ ንግድ አማካሪው አቶ ሞገስ በቀለ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከቻይና ባበጀችው ወዳጅነት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ትርፍ አግኝታበታለች።
አቶ ሞገስ "ቻይና በፖለቲካው አንፃር ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ለማመጣጠን የሚያስችል አማራጭ ኃይል ሆናለች። በአሁኑ ሰዓት ቻይና ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እያሰፋች መጥታለች። ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ በሚባለው የትብብር ስምምነት ከመቶ በላይ አገራት ጋር ውል ስምምነት ገብታለች። ያ ደግሞ ከፖለቲካ አንፃር ተደማጭ ሆና እንድትቀርብ አስችሏታል። ሌላው ኢትዮጵያ ለተለያዩ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶች የምትፈልጋቸውን ብድሮች በአጭር ጊዜ እና በምትፈልገው መጠን እንድታገኝ በር ከፍቶላታል" ሲሉ ይናገራሉ።
475 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው እና ዛሬም የመንገደኞችን ፍላጎት መሙላት ያልሆነት የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መጓጓዣ ኢትዮጵያ ከቻይና የመሰረተችው ወዳጅነት ውጤት ነው። በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበው የአዲስ አበባው አደይ አደባ ስታዲየም ግንባታ በቻይናዎች ይከወናል። በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስገነባው ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ የቻይና ኩባንያዎች ማስታወቂያ እና ቻይናውያን ሰራተኞች በብዛት ይታዩበታል። ከሌሎች በርካታ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ጀርባ ቻይና እና ቻይናውያን በገንዘብ፣ በሰው ኃይል እና በግንባታ ሲሳተፉ ይታያል።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በቅርበት ያጠኑት የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ጌዲዮን ገሞራ ጃለታ እንደሚሉት ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የሚያሻቸውን ገንዘብ በማቅረብ ጉድለታቸውን ሞልታለች።
አቶ ጌዲዮን "የአፍሪካ አገሮች ፋይናንስ የማግኘት ችግር አለባቸው። የራሳቸውን ገንዘብ አሰባስበው የመንገድ፤ የትምህርት ቤት እና የሆስፒታል [አገልግሎቶች] የማሟላት ችግር አለባቸው። መንገድ ከሌለ ኤኮኖሚው ሊያድግ አይችልም። የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣው ሰነድ በመሠረተ-ልማት ረገድ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለ ይላል። ኢትዮጵያንም ሌላ የአፍሪካ አገሮችንም ከአገር ውስጥ ገንዘብ የመሰብሰብ አቅማቸው ከአጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው ከ10 በመቶ በታች ነው። ስለዚህ ከዚያ ችግር ውስጥ ለመውጣት እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶችን መጠቀም ምንም ጉዳት የለውም" ይላሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታቸው የተጓተቱ የስኳር ፋብሪካዎችን ለማጠናቀቅ የቻይና ገንዘብ እና ኩባንያዎች እገዛ አስፈልጎታል። ካንስ የተባለ የቻይና ኩባንያ የጣና በለስ እና የወልቃይት የስኳር ፋብሪካዎችን እየገነባ ነው። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት የስኳር ፋብሪካ ጄጄአይስ ለተባለ ሌላ የቻይና ኩባንያ ተሰጥቷል። አቶ ጌዲዮን "በአፍሪካ ኅብረት አንገብጋቢ የሚባሉ ፕሮጀክቶች አሉ። ከዚያ ውስጥ አንዱ የአጀንዳ 2063 የፈጣን ባቡር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ርዋንዳ ላይ ባለፈው አመት የተፈረመ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አለ። 22 አገሮች ፈርመዋል፤ ሕግ ይሆናል ፤ እርስ በርስ ይገበያያሉ። ያ ማለት መንገድ ማደግ አለበት፤ አየር መንገድ ማደግ አለበት፤ ባቡሩ ማደግ መቻል አለበት። የአፍሪካ አገሮች ፍላጎታቸውን አስተባብረው [ገንዘብ] ከቻይና መውሰዱ ችግር የለውም" ሲሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ወደ ቻይና ማማተራቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ጠለቅ ብለው ያጠኑት ባለሙያው ኢትዮጵያን የመሰሉ አገሮች የሚበደሩት ገንዘብ "ለመጣለት አላማ ካልዋለ እና የሙስና ወጥመድ ውስጥ ከወደቀ በጣም ከባድ ነው። የዕዳ ጫና ይፈጥራል። ያንን ለመክፈል ደግሞ አገሮች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ይኸ ዕዳ በየሶስት ወሩ ነው የሚከፈለው። በጣም የዶላር ጫና ይፈጥራል" የሚል ሥጋት አላቸው።
ኢትዮጵያ ከቻይና የተበደረችው ገንዘብ በሙስና ባክኗል? የመንግሥቱ ባለሥልጣናት እርስ በርስ ተካሰው የተመዘበረ ገንዘብ ስለመኖሩ ጥቆማ ቢገኝም ግልፅ ያለ ማረጋገጫ ግን የለም። አቶ ሞገስ በቀለ ኢትዮጵያ ጥንቃቄ ልታደርግባቸው ይገባል ከሚሏቸው ጉዳዮች አንዱ አቶ ጌዲዮን የጠቀሱት የብድር ጫና ቀዳሚው ነው። የዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ንግድ አማካሪው አቶ ሞገስ "ኢትዮጵያ በ2008 አንድ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የነበረው የብድር ጫናዋ አሁን ወደ 23 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሆኗል። ከአጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠኗ ከ40 ከመቶ እና ከዚያ በላይ በሚያልፍ ደረጃ የብድር ጫና ውስጥ እየገባች ነው። ከ2005 ዓ.ም. ወደዚህ ያሉ የተለያዩ ትላልቅ ግንባታዎችን ስናይ የገንዘብ ምንጭ ሆና የምትገኘው ቻይና ናት።" ሲሉ ገልጸዋል።
የዕዳ ወጥመድ?
አሳሳቢው ቅርቃር ግን የዕዳ ጫናውን የሚከተለው የአገሮችን ሉዓላዊነት የሚፈታተን የቻይና እርምጃ ነው። አቶ ሞገስ ቻይና የምትሰጠውን ብድር "እንደተገኘ መጠቀም ኋላ ኋላ የአገሪቷን ኤኮኖሚ የሚያቃውስ ከፍ ሲል ሉዓላዊነቷን የሚጎዳ ሆኖ የሚቀርብ ይሆናል። ይኸ እንግዲህ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የታየ ነው" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የቀድሞው የስሪ ላንካ ፕሬዝዳንት ማሒንዳ ራጃፓክሳ ከአገራቸው በስተደቡብ ዘመናዊ ግልጋሎት ለመስጠት የሚያስችል ወደብ ለመገንባት ከቻይና ብድር እና እርዳታ በጠየቁ ቁጥር የፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ መንግሥት ምላሽ አዎንታዊ ነበር። ፕሬዝዳንቱ የስሪ ላንካ የብድር ጫና ከአሳሳቢ ደረጃ ቢደርስም የወደብ ግንባታው አያዋጣም የሚሉ ጥናቶችን ችላ ብለው በጅማሯቸው ገፉበት። ከአመታት በኋላ ግንባታው ሲጠናቀቅ እንደተተነበየው ወደቡ ስኬታማ መሆን አልቻለም። እጅግ በርካታ መርከቦች በሚመላለሱበት አካባቢ የሚገኘው የሐምባንቶታ ወደብ በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም ያስተናደው 34 መርከቦችን ብቻ ነበር። ከቻይና የተበደረችውን ገንዘብ መመለስ የተሳናት ስሪ ላንካ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ለወራት ከተደረገ ብርቱ ድርድር በኋላ የሐምባንቶታ ወደብን እና በዙሪያው የሚገኝን 6,000 ሔክታር ገደማ መሬት ለ99 አመታት ለቻይና አሳልፋ ሰጠች። የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ውሳኔው የስሪ ላንካን ሉዓላዊነት ይጎዳል ቢሉም ብድሩን ፈርመው ያጸደቁት ፕሬዝዳንት ማሒንዳ ራጃፓክሳ በምርጫ ተሸንፈው ከሥልጣን ተባረው ነበር።
ኬንያ እና ዛምቢያን የመሳሰሉ ተበዳሪ አገሮች ዕዳቸውን መክፈል ሲሳናቸው ተመሳሳይ ፈተና ውስጥ መውደቃቸውን የሚያስታውሱት አቶ ሞገስ በቀለ "ይኸ ነገር ወደ ኢትዮጵያ የማይመጣበት ምክንያት አይኖርም። አሁን ጥሩ የሆነውን የኢትዮጵያን እና የቻይናን ግንኙነት አሉታዊ ሊያደርግ የሚችል ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት የዚህን የብድር ጫና መቋቋም በሚችልበት መልኩ መፍትሔዎችን መቀየስ ያስፈልጋል። የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን የሚያሳድግበትን የፊስካል ፖሊሲ መከተል አለበት" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ከዕዳ ጫናው ባሻገር በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የተዛባ የንግድ ሚዛን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አቶ ሞገስ ጠቁመዋል። የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ክፍተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ነው የሚሉት ባለሙያው በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. "ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የላከችው ከ200 እና ከ300 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጥ ምርት ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የቻይና ምርቶች ናቸው። እርግጥ አብዛኞቹ የኢንዱስትሪያል ውጤቶች ናቸው። ሆኖም ግን ሰፊ የሆነ የንግድ ሚዛን መዛባት የሚታይበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በቤጂንግ በተካሔደው ስብሰባ ቻይና ብድር ካጎበጣቸው አገሮች ለመደራደር እና የአንዳንዶቹንም ዕዳ ለመሰረዝ ያላትን ፈቃድ አሳይታለች። ምዕራባውያኑ ተበዳሪዎችን ከዕዳ ወጥመድ ውስጥ ይጥላል የሚሉት የመቀነት እና የመንገድ ዕቅድ ባለፉት አምስት አመታት ስኬታማ ነበር ሲሉ የሚሞግቱት የቻይና ባለሥልጣናት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የሚያነሱትን ሥጋት ፈፅሞ አይቀበሉም። ዕቅዱን በመላው ዓለም የማስተዋወቅ ኃላፊነት የተሰጠው የቻይና መንግሥት ቢሮ ዳይሬክተር ዢያዎ ዌይሚንግ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ የተሳተፉ አገሮች ሲያድጉ መታየታቸው ዕቅዱ "የዕዳ ወጥመድ" ነው የሚለው ወቀሳ ሐሰት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የቤጂንጉ ስብሰባ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት የዕቅዱን ስኬታማነት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ዢያዎ ዌይሚንግ ሲያስረዱ "ተበዳሪ አገር ገንዘቡን መዋዕለ-ንዋይ በማበረታታት፣ መሠረተ-ልማትን በማጠናከር እና ወደ ኢንዱስትሪ የሚያደርጉትን ሽግግር በማፋጠን ምጣኔ-ሐብቱን ለማሳደግ ማዋል አለበት። እንደ ቻይና ያሉ አበዳሪ አገራት በበኩላቸው በአንጻራዊነት ምጣኔ-ሐብታቸው ወደ ኋላ የተጎተተ አገራትን የመርዳት ግዴታ አለባቸው። በጥምር ምክክር፤ በመተጋገዝ እና አብሮ የመስራት መርኅን በመከተል የዕዳ ጫና መፍትሔ ሊበጅለት ይችላል። አንዳንድ አገሮች የዕዳ ጫናቸው ከፍተኛ ቢሆንም እንኳ ኢንዱስትሪን እና ከተሜነትን በማፋጠን መቀነስ ይቻላል። ነገር ግን ያለ ዕድገት እና ያለ ብርቱ ሥራ ምንም ተስፋ አይኖርም" ብለው ነበር።
"መንገዶች ሁሉ ወደ ቤጂንግ ያቀናሉ"
ቻይና ለኢትዮጵያ የደረሰችው የያኔው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ መንግሥት በምርጫ ጣጣ ከምዕራባውያኑ በተቃቃረበት የዓለም ምጣኔ-ሐብትም በቀውስ ተመቶ በተቀዛቀዘበት ሁነኛ ወቅት ነበር። የቻይና-አፍሪካን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ አንድ አማካሪ እንዳሉት የዢ ዢንፒንግ አገር የኢትዮጵያን ባቡር ግንባታ ለማከናወን ስትነሳ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ ሆነዋል። በተለይ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ማጓጓዣ ግንባታን በቅርበት ያጠኑት ባለሙያው በስምምነቱ ኢትዮጵያ ለመሠረተ-ልማት ግንባታ የሚያሻትን ገንዘብ ስታገኝ ቻይና በበኩሏ በአፍሪካ ለሰፊው ውጥኗ አጋር ማበጀቷን ጠቁመዋል።
ቻይና አንድ መንገድ አንድ መቀነት የተሰኘውን እና ዓለምን በየብስ እና በባሕር በማስተሳሰር የንግድ ልውውጥን ለማፋጠን የጀመረችው ይኸ ዕቅድ ምጣኔ-ሐብታዊ ኃያልነቷን የምታሳይበት እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ። አገሪቱ ከፖለቲከኞች ባሻገር በጥበብ ባለሙያዎቿ ጭምር ጠቀሜታውን ለዓለም ልታስረዳ ጥረት ታደርጋለች። በዚህ ዕቅድ ከኢትዮጵያ ጅቡቲ ከተዘረጋው ባሻገር በኬንያ ከናይሮቢ እስከ ሞምባሳ ተመሳሳይ የምድር ባቡር ገንብታለች። ቻይናዎቹ ምሥራቃዊ አፍሪካን የሳኅል ቀጠናን በማቋረጥ በሚዘረጋ የምድር ባቡር ከምዕራቡ ጋር የማስተሳሰር ውጥን ጭምር አላቸው።
አቶ ጌዲዮን "ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼየቲቭ የሚባለውን ዕቅድ ያመጡት ፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ ናቸው። ዓላማው የቻይናን የድሮ ዝና መመለስ ነው። እነሱ በፊት ቲያንጂ ከተባለ ከተማ በመላው አውሮፓ የሸክላ ምርቶቻቸውን ይሸጡ ነበር። በየብስ እና በባሕር ሁሉንም ዓለም ከቻይና ጋር የማስተሳሰር ውጥን አላቸው። በፊት ሁሉም መንገዶች ወደ ሮም ይመራሉ እንደሚባለው አሁን ሁሉም መንገዶች ወደ ቤጂንግ ያመራሉ ሆኗል" ሲሉ ከግዙፉ እና ከውስብስቡ ዕቅድ ጀርባ ያለውን ዓላማ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች አፍሪካውያን ምጣኔ ሐብታቸውን ለማነቃቃት ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ግንባዎች ያሻቸዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች አፍሪካውያን አገሮች በቻይና ጥገኛ መሆናቸውን ገታ አድርገው የገንዘብ ምንጮቻቸውን በርከት ያደርጉ ዘንድ ይመክራሉ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቻይና ባሻገር ዓለም ባንክን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ገንዘብ ማፈላለግ መጀመራቸው የዚሁ ጥረት ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል። ኢትዮጵያ ግን እንዲህ በቀላሉ ከቻይና የምትላቀቅ አይመስልም። አገሪቱ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣችባቸው ነገር ግን ዛሬም ድረስ መጠናቀቅ የናፈቃቸውን የታላቁ ኅዳሴ ግድብ እና የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታዎች ለቻይና ኩባንያዎች ሰጥታለች። አቶ ጌዲዮን "ፈረንጆቹም እንደሚሉት ነፃ ምሳ የለም። ቻይና እንደዚህ ስትረዳ ዝም ብላ አይደለም የምትረዳው። በ1970 እና 80ዎቹ ጃፓን ወደ ቻይና እና ወደ ጎረቤት አገሮች ብድርን ወደ ገበያዎቻቸው ለመግባት እንደ ሥልት ነበር የሚጠቀሙት። የሚሰጡት ዝቅተኛ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ነው ነገር ግን ቅድመ-ሁኔታዎች አሉት። ቁሳቁሱ ከዚያ ነው መምጣት ያለበት፤ ቴክኖሎጂው ከዚያ ነው መምጣት ያለበት፤ ኩባንያዎቹ ከዚያ ነው መምጣት ያለባቸው፤ ስለዚህ ብድር ብቻ አይደለም። ብድር ብቻ ሳይሆን ገበያ ፈልፍሎ መግቢያ ሥልት ነው። የእነሱ ኩባንያዎች እዚህ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ፤ የሚጠቀሙበት ነው። በቀላሉ ኩባንያዎቹ እዚህ ይመጣሉ ከዚያ ተመልሰው አይሔዱም። ሌላ ጨረታ ይወዳደራሉ" ሲሉ ሌላውን ፈተና ይገልጹታል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ