1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራቱ ሰላማዊ መንገድን መክራለች

እሑድ፣ ሰኔ 11 2009

ኢትዮጵያ ድንበር የምትጋራቸው ኤርትራ እና ጅቡቲ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ከማባባስ እንዲታቀቡ አሳሰበች፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የ“እውነት አፈላላጊ ቡድን” በአካባቢው ለማሰማራት መወሰኑንም እደግፋለሁ ብላለች፡፡

https://p.dw.com/p/2etOC
Karte Nil Verlauf und Renaissance-Staudamm Englisch

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የጅቡቲ እና ኤርትራ ወታደራዊ ኃይሎችን ለመለየት በድንበራቸው ላይ ሰፍሮ የነበረው የኳታር ጦር ሰራዊት ከአካባቢው ለቅቆ  መውጣቱን ተከትሎ እየሆነ ያለውን ኢትዮጵያ በቅርበት እየተከታተልኩ ነውም ብላለች፡፡ በመግለጫው ኢትዮጵያ ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የ“እውነት አፈላላጊ ቡድን“ በአካባቢው ለማሰማራት መወሰኑንም እደግፋለሁ ብላለች፡፡

በጅቡቲ እና ኤርትራ መካከል እየተጋጋለ የመጣው ውጥረት ያሳሳበው የአፍሪቃ ኅብረት ወደ ሁለቱ ሃገራት ድንበር ቡድኑን ለመላክ መወሰኑን ያሳወቀው ቅዳሜ ዕለት ነው። የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ኅብረቱ “ከሁሉም ወገኖች ጋር እንደሚሠራ” ተናግረዋል፡፡ህብረቱ ሁለቱም ሀገራት ውጥረቱን ከማባበስ “እንዲታቀቡ” ጥሪ አድርጓል፡፡

ጅቡቲ ባለፈው ሐሙስ ባወጣችው መግለጫ የኳታር ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ ከኤርትራ ጋር በይዞታ የምትወዛግብበትን የዱሜራ ተራራን የኤርትራ ወታደሮች ተቆጣጥረውታል ስትል ወንጅላለች፡፡ ክሷንም ለአፍሪካ ህብረት በይፋ አሳውቃለች፡፡ በጅቡቲ በኩል ለሚሰነዘርባት ውንጀላ በቀጥታ ምላሽ ያልሰጠችው ኤርትራ ትላንት ባወጣችው መግለጫ የኳታር ጦር ከአካባቢው ስለለቀቀበት ምክንያት ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም ብላለች፡፡ የኤርትራ መንግስት መረጃውን እንዳገኘ አቋሙን ይፋ እንደሚያደርግም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡    

 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ