ኢትዮጵያና ሶማሊያ የማይነጣጠሉ ሕዝቦች ግን የወዳጅ-ጠላቶች ምድር
ሰኞ፣ ጥር 5 2017
አምና ይኸኔ አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ፅናት፣ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትዋ ብስራት ይዘመር፣ይወደስ፣ ይተነተን ነበር። ሞቃዲሾ ላይ ባንፃሩ የኢትዮጵያ የሶማሊያ ታሪካዊ ጠላትነት፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የመድፈሯ እብሪት በአደባባይ ሰልፍ ጭምር ይወገዝ፣ለአድማ-ብቀላ ይዛት፣ የካይሮ-አስመራ-አንካራዎች ድጋፍ ይሰበክ ነበር።ዘንድሮ ባመቱ የአዲስ አበባና የሙቃዲሾ መሪዎች የሁለቱን ሐገራት ወዳጅነትና አዲስ ትብብርን ሲተርኩ፣አዲስ አበባ፣ በሁለቱ መሪዎች ፎቶ አሸብርቃለች።ካይሮም የሶማሊያና የኤርትራን ሚንስትሮችን አስተናግዳለች።የአፍሪቃ ቀንድ የፍቅር-ጥላቻ፣የትብብር-ሽኩቻ፣የወዳጅነት-ጠላትን አብነት ምድር።ያፍታ ቅኝታችን ነዉ።
እንደ ጠላት የሚያዋጉ፣ እንደ ወዳጅ የሚሞጋገሱ መሪዎች
ኃምሌ 1977 የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦር ኃይላት ኦጋዴን ላይ በቀጥታ የገጠሙት አስከፊ ዉጊያ ቆሞ በ1980ዎቹ አጋማሽ በተዘዋዋሪ ጦርነት ሲተካ፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች እንደ አዲስ ፍቅረኛ ይሞጋገሱ፣ ይወዳደሱ፣ ለመተባበር ቃል ይገባቡ ገቡ።የየዉስጥ ጠላት የበዘባቸዉ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ጄኔራል መሐመድ ሲያድ ባሬ አንዱ የሌላዉን ጠላት እየደገፉ፣ መጀመሪያ ጀቡቲ፣ቀጥሎ አዲስ አበባ፣ አሰልሰዉ ሶደሬ ላይ የተጨባበጡ እጆቻቸዉን ሽቅብ እያጓኑ ወንድሜ-ወላሎ የመባባላቸዉ ዚቅ ለብዙ ታዛቢዎች አነጋጋሪ፣ አደናጋሪ፣ አስተዛዛቢም ብጤ ነበር።
በልማዱ የኦጋዴን የሚባለዉ ጦርነት ከአረብ ሊግ አባል ሐገራት እስከ ዋሽግተን፣ከሐቫና እስከ ሞስኮ ያሉና የነበሩ የካፒታሊሲት-ሶሻሊስ ኃያል፣ ሐብታም ጠላቶችን ግራ-ቀኝ አሰልፏል።በትንሽ ግምት የሁለቱን ሐገራት 25 ሺሕ ሰላማዊ ህዝብ ፈጅቷል።ከ14 ሺሕ በላይ የሁለቱን ሐገራት ወታደሮች፣ በመቶ የሚቆጠሩ የኩባ፣የደቡብ የመንና የሶቭየት ሕብረት ወታደሮችና የጦር አማካሪዎችን ሕይወት አጥፍቷል።50 ሺዎችን አፈናቅሏል።የሁለቱን ሐገራት ሐብት አዉድሟል።
እስከ ዓለም ፍፃሜ ሊነጣጠሉ አይችሉም
የሶማሊያዉ ማስታወቂያ ሚንስትር ዳዉድ አዌስ ባለፈዉ ሳምንት ለዶቼ ቬለ እንደነገሩት ሶማሊያና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ ጎረቤቶች ናቸዉ።
«ሶማሊያና ኢትዮጵያ ሊጣጠሉ አይችሉም።ጎረቤታሞች፣ ወድምና እሕትማማቾች ናቸዉ።ጎረቤታሞች ሊነጣጠሉ አይችሉም።ይሕ ዓለም እስኪያበቃ ድረስ አብረን እንኖራለን።ከሚነጣጥለን ይልቅ የሚያቀራርበንን ነገር ማምጣት አለብን።»
አላበሉም።የሁለቱን ሐገር ሕዝብ ከማቀራረብ ይልቅ ከ1977ቱ አዉዳሚ ጦርነት የማገዱት፣አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመጣል እያሴሩ ባደባባይ ከተሞጎገሱት ከሁለቱ ሐገራት መሪዎች-ሲያድ ባሬ ጥር 1991 ከሥልጣን ተወግደዉ ከሐገር ሸሽተዋል። ኮሎኔል መንግሥቱም «የምሥራቁን ጠላት ጎማዉን አስተንፍሰነዋል» እያሉ ባፌዙ በወራት ዉስጥ ሲያድ ባሬን ተከትለዋል።ግንቦት 1991።
ሁለቱ መሪዎች፣ ቀዳሚዎቻቸዉም ሆኑ ተከታዮቻቸዉ ሲወዳጁ-የተወዳጁበትን ምክንያት፣አላማ ዉጤቱን ለየሕባቸዉ ከማስረዳት ይልቅ ገደብ የለሽ ፍቅርን፣ ሲኳረፉ ለትዉልድ የሚዘልቅ ጠላትነትን ለማይነጣጠለዉ ህዝባቸዉ መስበካቸዉ፣ ምናልባትም ከዉጊያ መማገዳቸዉም በርግጥ እንደቀጠለ ነዉ።
አምና ጥላቻ ዘንድሮ ፍቅር
አምናና ዘንድሮም የሆነዉ የተለየ አይደለም።የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች ጥር 1 2024 የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸዉን ሰማን።ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት በሌሎች ዘንድ የሚኖረዉ ትርጉም፣ የሚያስክትለዉ መዘዝና መዘዙን ለመከላከል የተደረገዉን ዝግጅት ከፈራሚዎቹና ከረዳቶቻቸዉ በስተቀር በቅጡ የሚያቀዉ የለም።
ሌላዉ ቀርቶ የመግባቢያዉ ሥምምነት «የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ የባሕር በር አገኘች» ከማለታቸዉ ወይም የሐርጌሳ ባለሥልጣናት «ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የመንግሥትነት ዕዉቅና ልትሰጥ ነዉ» ከማለታቸዉ ባለፍ ዝርዝር ይዘቱ ሚስጥር ነዉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር፣ ሶማሊላንድ የመንግሥትነት ዕዉቅና ሊያገኙ ነዉ በሚሉ የሩቅ ተስፋ ዜማዎች የአዲስ አበባና የሐርጌሳ መሪዎች ሕዝባቸዉን ሲያጨፍሩ ሙቃዲሾዎች «ሉዓላዊነታችን ተደፈረ» በሚል ቀረርቶ ህዝባቸዉን ለዉጊያ፣ የካይሮ፣አስመራ፣ አንካራ ወዳጆቻቸዉን ለወታደራዊ ድጋፍ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ለትብብር ያሳድሙ ያዙ።
ዘንድሮ ባንፃሩ የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ሸምጋይነት ባለፈዉ ወር «የአንካራ መግለጫ» የተባለዉን ሥምምነት ተፈራርመዋል።በአዲሱ ስምምነት መሰረት ሰሞኑን አዲስ አበባና ሞቃዲሾ ላይ የአምናዉ ቀርቶ-ሌላ ታሪክ መጥቶ ይተረክ «አዲስ ፍቅር ይዞኛል» ይቀነቀን ይዟል።የቀድሞዉ የሶማሊ ክልል ምክር ቤት አባልና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት ሁለቱ ሐገገራት መስማማታቸዉ ጥሩ ነዉ።
«ባጠቃላይ አሁን እንደገና የታደሰዉ ግንኙነት ጥሩ ነገር ነዉ።»የኢትዮጵያ የሲቪልሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምሕርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕም ይስማማሉ።
«በአንድ ወገኖች በኩል ወደ ጦርነት ያመራል የሚለዉን ሥጋት በማርገብ ረገድ የሚኖረዉ ሚና ቀላል አይደለም።»
«ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ----»
ግን ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት ሁለቱ መንግሥታት አምና ለየሕዝባቸዉ የጋቱት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የፈጠረዉ ስሜት በቀላሉ መስከኑ ያጠራጥራል።
«ነገር ግን ሁለቱ ሐገራት በጣም ከጫፍ እስከ ጫፍ ዋልታ ረገጥ የሆኑ ክሶች ነበሩ የሚያቀርቡት።በሶማሊያ በኩል ፕሬዝደንቱ ኢትዮጵያ ከአሸባብ የበለጠ ጠላታችን ናት እስከማለት ደርሰዉ ነበር።በኢትዮጵያ በኩልም የሞቅዲሾ መንግሥት ያለኛ እገዛ አንድ ቀን ሙቅዲሾ አይቆይም ሲል ብርሐኑ ጁላ ባለፈዉ ያቀረበዉ---ሶማሊያ የግብፅና የኤርትራን ድጋፍ መጠየቅዋ።
ዶክተር ሙከረም የሰሞኑ ሆይ ሆይታ ችግሩን መፍታቱን ይጠራጠራሉ።
«የሶማሊያ መንግስት እዚሕ እሰጥ አገባ ዉስጥ እንዲገባ ያደረገዉ ጥያቄዉ ምንድነዉ።ያ ጥያቄ በዚሕ ሁለት ሶስት ቀን ዉስጥ ሚዲያ ላይ እንደሚራገበዉ አዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ በሚገርም ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩና የሐሰን ሼክ ፎቶ በየቦታዉ ተቃቅፈዉ---ምናምን---ሲንቦሊክ ነዉ።በጭብጥ ደረጃ።-----»
የአዲስ አበባ መሪዎች የኤርትራዉን ፕሬዝደንት «ኢሱ፣ ኢሱ» ባሉበት ዘመንም ርዕሰ ከተማይቱ እንዲሕ ነበረች።ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት ግን የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት አዲስ አበባን መጎብኘታቸዉ ይኸን ያሕል የሚያስፈነጭ መሆን አልነበረበት።ለምን?
«የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ መንግሥት፣መንግስት ራሱ እንደሚያስቀምጠዉ ለኢትዮጵያ የሕልዉና ጉዳይ ነዉ።የሕልዉና ጥያቄ ከሆነ ባንድ ሰሞን የዲፕሎማሲ ጂምናስቲኮች እንዲሕ በቀላሉ ሊረግብ ይችላል ወይ የሚለዉ መመለስ አለበት።የሶማሊያ መንግሥትም ሉዓላዊነቴ ተጥሷል ነዉ ያለዉ።እንግዲሕ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ከምር ከያዘዉ ለዚሕ የወደብ ጥያቄዉ ምላሽ የሚሆን አማራጭ ነገር መፈለግ አለበት።»
የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ የመግባቢያ ሥምምነት እጣ
የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ሸምጋይነት የተፈራረሙት ሥምምነት ኢትዮጵያ ወደብ እንድታገኝ ሶማሊያ እንደምትተባበር ይጠቅሳል።የትብብሩን ደረጃ፣ የወደቡን የትነትም ሆነ ወደቡ ለምን አገልግሎት እንደሚዉል በዝርዝር ያስቀመጠዉ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችዉ የመግባቢያ ስምምነት ሥለመፍረስ-አለመፍረሱም የአንካራዉ መግለጫ የሚለዉ ነገር የለም።የሶማሊያ መንግሥት ደጋፊዎች ግን የመግባቢያ ስምምነቱን ለማፍረስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቃል መግባታቸዉን አስታዉቀዋል።ዉስጥ አዋቂ የሚባሉ ተንታኖችም ስምምነቱ መፍረሱን ይናገራሉ።
ዶክተር አብዲ እንደሚሉት የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች ራሳቸዉ የፈጠሩትን ችግር መሠረታዊ ምክንያት ተራ በተራ ከመፍታት ይልቅ ለስምምነትና ወዳጅነት የተጣደፉት ከዉስጥ የገጠማቸዉን ጫና ለማቃለል ይመስላል።
«ሁለቱም መንግሥታት ከፍተኛ የዉስጥ ጫና ነዉ ያለባቸዉ።አሁን ችግሩን በመፍታት ላይ ያሉበት ሁኔታ የፈጠነና የጥግሩን መሰረታዊ ምክንያት ከመፍታት ይልቅ ያለባቸዉን የዉስጥ ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ይመስላል።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ፣ የኑሮ ዉድነትና ሙስናም እየተንሠራፋ ነዉ።ሶማሊያም ሠላም የላትም።ሁለቱም ሐገራት ለምርጫ ተቃርበዋል።በተለይ የሶማሊያ ምርጫ ዶክተር አብዲ እንደሚሉት ለፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ወሳኝ ነዉ።
«እንደሚታወቀዉ የሐሰን ሼሕ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ሶስተኛ ዓመቱ ነዉ።ምርጫ ተቃርቧል።በሶማሊያ እስካሁን ምርጫ የሚደረገዉ በስምምነት (ዉክልና) ነዉ።ያንን ምርጫ ለማድረግ ከፌደራል ግዛቶች የተዉጣጣ ዋና ኮሚቴ ነበር።ኮሚቴዉ ምርጫዉ እንዴትና መቼ መካሔድ እንዳለበት ይወስናል።ያ ተቋም ሐሰን ሼኽ፣ ከፑንትላንድና ከጁባላንድ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት (ምክንያት) ፈርሷል።»
ፕሬዝደንቱ አዲስ አበባ፣ ሚንስትሩ ካይሮ
የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ባለፈዉ ቅዳሜ አዲስ አበባ ሲገቡ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ካይሮ ነበሩ።የአዲስ አበባ መሪዎች ለታላቅ እንግዳቸዉ ደማቅ አቀባባል ሲያደርጉ የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በድር አብድላትይ የሶማሊያና የኤርትራ አቻዎቻቸዉን ስብሰበዉ ሥለ ፀጥታና ወታደራዊ ትብብር ይነጋገሩ ነበር።
የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በድር አብድላትይ ፣ የኤርትራ አቻቸዉ ዑስማን ሳሌሕ መሐመድና የሶማሊያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሕመድ ሞአሊን ፊቂ የሶስትዮሽ ትብብር የሚንስትሮች ባሉት ስብሰባ የሶስቱ ሐገራት ትብብር፣ የሱዳን ሁኔታ፣ የሶማሊያ ፀጥታ ያሉትን ሐሳብ አንስተዋል።ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት ግን የሶስቱ ሐገራት መሪዎችና ባለሥልጣናት ከዚሕ ቀደምም ሆነ አሁን ያደረጉና የሚያደርጉት ዉይይት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ ታደርገዋለች ያሉትን ጫና መቋቋም ነዉ።
«አልቲሜትሊ ሥለ አፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ፣ ሥለሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ምናምን የሚሉ እንትኖች አሉት ግን በአብዛኛዉ የሶስቱ የዉይይት ቁልፍ ጭብጥ አላማ፣ ሶማሊያ ላይ በነሱ እምነት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየተደረገ ያለዉን ጫና ቻሌንጅ ማድረግ ነዉ።አልተዉትም ይኽን።
ሶስቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የሶማሊያን ፀጥታ ለመጠበቅ ያሉትን ስምምነት አድርገዋል።ግብፅ ጦር አዲስ የተመሰረተዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት አባል እንዲሆንም ፈቅደዋል።ዶክተር አብዲ ስብሰባ ዉይይቱ የኢትዮጵያና የሶማሊያ አለመተማመን መኖሩን አመልካች ነዉ ይላሉ።
«የፀጥታ ሁኔታ፣ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ዉስጥ (የግብፅ ጦር) ተሳትፎ ምን ያሕል ይሆናል።የት አካባቢ ይሰፍራሉ።የሶማሌ መከላከያና ፀጥታ ሁኔታና እንደዚሕ ዓይነት ትብብሮች ላይ መሠረት ያደረገ ነዉ የሚል ነዉ።እና አሁንም ፍራቻዉ፣የባሕር በር ጥያቄና መተማመን ያልተፈጠረበት ሁኔታ (መኖሩን) የሚያሳይ ነዉ»
የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች የማይተማመኑ ወዳጆች፣ ጠላቶች ወይስ መነጣጠል ለማይችለዉ ሕዝባቸዉ አሳቢዎች? ድሮ ተጠይቋል፣ አምና ተደግሟል ዘንድሮም።ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ