1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያገናኘው የሑመራ-ኦምሓጀር መንገድ መከፈት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2011

ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያገናኘው የሑመራ-ኦምሓጀር መንገድ በይፋ ተከፈተ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ጨምሮ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመርሐ ግብሩ ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/3B898
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed empfängt Eritreas Präsident Isayas Afewerki
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያገናኘው የሑመራ-ኦምሓጀር መንገድ በዛሬው ዕለት በይፋ ተከፈተ። መንገዱ ሲከፈት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ተገኝተዋል።  የኢትዮጵያው ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል እና የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመርሐ-ግብሩ ታድመዋል። በኤርትራ በኩል የውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ኦስማን ሳሌሕ እና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብን ጨምሮ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በቦታው ተገኝተዋል። 

በኤርትራ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ በተላለፈው መርሐ-ግብር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት መጀመር የሚያወድሱ ሙዚቃዎች ሲቀርቡ ታይቷል። በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጩ ምስሎች እንደሚጠቁሙት መንገዱ በተከፈተበት አካባቢ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በመደረግ ላይ ነው።  

ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍልን ከደቡባዊ ኤርትራ የሚያገናኘው የሑመራ-ኦምሓጀር መንገድ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ነው።

የሁለቱ አገሮች መሪዎች በኤርትራ በኩል በተሰነይ እና ገረሰት የሚታዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ይጠቁማል። የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት ግንኙነታቸውን ካደሱ ጀምሮ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች የሚያገናኟቸው መንገዶች እንዲከፈቱ መወሰናቸው አይዘነጋም። ከጥቂት ቀናት በፊት ባለፈው መስከረም አንድ ተከፍቶ በነበረው የዛላምበሳ ድንበር ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገበት ይገኛል።

ከኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት የይለፍ ፈቃድ ካገኙ ውጪ ሌሎች በዛላምበሳ በኩል ወደ ኤርትራ መሻገር መከልከላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን እና ነዋሪዎች ለDW ተናግረዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የጉለመከዳ ኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት የፕሬስ ባለሙያ አቶ የዕብዮ ሙልጌታ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የኤርትራ ጸጥታ አስከባሪዎችን አነጋግረው "ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የይለፍ ወረቀት ይዘው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች እንድናሳልፍ ተነግሮናል። ከዚያ ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ ማለፍ እንደማንችል ከአለቆቻችን ትዕዝዛ የተሰጠን ስለሆነ ማሳለፍ አንችልም" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

የዛላምበሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በረከት ኃይለሚካኤል በበኩላቸው የአካባቢው ሰው "ይዘጋል የሚል መረጃ ስላልነበረው ዝግጅት አላደረገም ነበር። ድንገት መዘጋቱ በነጋዴው እና በአካባቢው ሰው ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል" ሲሉ ለDW አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ