“ኢትዮጵያን ከገጠማት ቀውስ እንዴት ማውጣት ይቻላል?” የሚል ውይይት ተካሔደ
እሑድ፣ ጥቅምት 18 2016ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ጉባዔ (ኢትዮጵያዊነት) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባካሄዳቸው የበይነ መረብ ውይይቶች፣ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ ዐማራ ትርክቶች፣ መቼና እንዴት ተጀመሩ? ትርክቶቹ ያስከተሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበረሰባዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች በሚሉ ርዕሶች ላይ መክሯል። የትናንትናው ውይይት ደግሞ፣ ከዚህ ሃገራዊ ቀውስ መውጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ፣ በአራት ምሁራን የመፍትሔ አቅጣጫዎች የተመላከቱበት ነበር።
ጂኦግራፊንና ልማትን መሰረት ያደረገ አስተዳደርና፣ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ሊያካትት በሚችል አስተዳደራዊ አወቃቀር መዘርጋት እንደሚገባ በመፍትሔ ዐሳብነት ተቀምጧል። በኢትዮጵያ አስተዳደራዊ አወቃቀር ላይ ጥናት አቅራቢው ፕሮፌሰር ሙላቱ ናቸው።
ፕሮፌሰር ሙላቱ "የሚዋቀረው መዋቅር ለአስተዳደር ምቹ፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ግብዐት ለመስጠት ነው እንጂ፣እኔ ይሄ ሃገሬ ነው፣ የአንተ አገር አይደለም አንተ መጤ ነህ፣እኔ እዚህ ነዋሪ ነኝ ከሚለው ነገር ኦብጀክት ለማድረግ መሆን የለበትም።" በማለት ተናግረዋል።
የትምህርት ስርዓቱን በተመለከተም፣ ትምህርት ቤቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በየደረጃው ሊጫወቱት በሚችሉት ሚና ላይ ውይይት ተካሄዷል። ከአፍ መፍቻ ቋንቋ በተጨማሪ አንድ ብሄራዊ ቋንቋና አንድ ወይም ሁለት ብዙ ህዝብ የሚናገራቸው ቋንቋዎች፣ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ የሚሉ መፍትሔዎችም ቀርበዋል። ለሃገራዊ ቀውሱ ምን ማድረግ አለብን በሚል በተካሄደው ውይይት፣ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ "ኢትዮጵያን ያዋጣል ብዬ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ መንገድ ያመጣል ብዬ የማስበው፣ አንደኛ ሁላችንም ይህንን ነገር በብዛት ስንቀበለው ይመስለኛል፡ የዘውግ ፖለቲካና ብሄራዊ አንድነትን እንዴት እናስታርቅ የሚለው ላይ ብናተኩር ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
የህግ ባለሙያው ደረጀ ደምሴ ቡልቶ በበኩላቸዉ፣ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ጉዳዮችን በተመለከተ የአሜሪካን ልምድ መነሻ በማድረግ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማዛመድ አብራርተዋል። "ምንድን ነው ሁላችንም ሊስማማን የሚችለው? ዕሳቤዎች ምንድን ናቸው የሚለውን መነጋገር ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ በአንዳንድ አከባቢ በበላይ ጠባቂ ብሔር ሰጥቶ፣ ከዛ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን መብታቸውን ማስከበር የሚችሉበት ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ፣ የሰዎች የመዘዋወርና በተለያየ ቦታ ሄዶ ንብረት አፍርቶ ለመኖር አይችልም። ያ እንዲሆን ወቅራዊ ለውጥ መኖር አለበት፤ ገለልተኛ ግጭቶችን የሚፈታ ፍርድ ቤት መኖር አለበት" ብለዋል።
ዐማርኛ ቋንቋን በአፍሪቃ ደረጃ ለመጠቀም ባለው አቅምና ብቃት ላይ ምሁራዊ ውይይት ተካሄደ
አገር በቀል ባህላዊ ዕውቀቶች፣ ሽምግልና፣ ሃይማኖታዊ ተቋሞች ለሃገር ግንባታ በሚያበረክቱት አዎንታዊ ሚና፣የዘር ጥላቻናክፍፍል ለማስቀረትየሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ደግሞ፣ በፕሮፌሰር ሰሎሞን ጋሻው ጥናት ቀርቧል። እነዚህ ባህላዊ ዕሴቶች በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትና አቅማቸው መዳከሙን ያወሱት ፕሮፌሰር ሰለሞን፣እንደገና ተጠናክረው ሃገራዊ ችግሮችን የሚፈቱበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበትም አመልክተዋል። በቀረቡት በእነዚህ የመፍትሔ ዐሳቦች ላይ፣ምሁራኑና ታዳምያኑ ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደውባቸዋል
ታሪሉ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ