ኤርትራ ለተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ያቀረበችዉ ጥያቄ
ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2007
ለኤርትራውያኑ በብዛት መሰደድ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ባለፈዉ ወር ዘገባዉ የሃገሪቱ መንግሥት ይፈፅመዋል ያለውን የመብት ጥሰት ተጠያቂ ያደረገበትን ምክንያት የኤርትራ መንግሥት ሀሰት ሲል አጣጥሎታል። እንደ መንግሥት ገለጻ፣ ዜጎቹ ሃገሪቱን ጥለው ለሚወጡበት ድርጊት ተጠያቂዎቹ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እንጂ ተፈፀመ የሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይደለም።
ባለፈዉ ሳምንት የኤርትራ መንግሥት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገዉ መግለጫ፤ በርካታ ዜጎች ከኤርትራ ወደ አዉሮጳ የመሰደዳቸዉ ምክንያት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች መሆናቸዉና ስለወንጀሉ የማያሻማ መረጃን እንደሚሰጥ ገልጾአል። በስዊድን ወላጆች የሌላቸዉ ስደተኛ ሕፃናትን በሚረዳዉ ድርጅት ዉስጥ የሚያገለግሉት አቶ ዓለም ዘሞ፤ ሕገ- ወጥ አዘዋዋሪዎች ተገቢዉን ቅጣት እንዲያገኙ የኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠየቀዉን መግለጫ ይደግፋሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ባለፈዉ ወር ባወጣዉ ዘገባ የኤርትራ መንግሥት ዜጎችን በግዳጅ እንደሚያሰር ቁም ስቅል እንደሚያሳይና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደሚፈፅም መግለፁ ይታወቃል። የተመድን ዘገባ የማይቀበሉት አቶ ዓለም ዘሞ እንደሚሉት የኤርትራ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ነዉ የሚሰራዉ። የተባበሩት መንግሥታት ኢርትራዉያን እንዲሰደዱ የዳረጋቸዉን መሠረታዊ ምክንያት መመርመር እንደሚኖርበት ነዉ፤ አቶ ዓለም ዘሞ የተናገሩት።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ