1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራ፦ «በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል»

ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2008

በኤርትራ የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ሲል የኤርትራን የሠብአዊ መብት ይዞታን የሚያጠናዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል ። የኮሚሽኑ ሁለተኛ የጥናት ዉጤትን በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት ተቀባይነት የሌለው ብሎታል።

https://p.dw.com/p/1J2il
Eritrea Präsident Isayas Afewerki
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ራሷን የቻለች ሀገር የሆነችበትን 25ኛ ዓመት ባከበረች ማግስት ይፋ የወጣ ዘገባ ሀገሪቱ ውስጥ «በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል» መስፈኑን ይፋ አደረገ። ስለ ዘገባው ዛሬ ጄኔቭ ስዊትዘርላንድ ውስጥ መግለጫ የሰጡት የኤርትራን የሠብአዊ መብት ይዞታ የሚያጠናዉ የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማይክ ስሚዝ ይኽንኑ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«በመጀመሪያው ዝርዝር ዘገባችን ወቅት አሳሳቢ የሰብአዊ ጥሰት መኖሩን ለይተን መዝግበናል። የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እኛ የደረስንበት በደል በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል የሚያካትት መሆን አለመሆኑን እንድናጣራ ጠይቆን ነበር። እናም በሁለተኛው ዘገባችን ላይ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ ያለንን እይታ በተጨማሪ መረጃ ከማጠናቀራችን ባሻገር፤ በዚህ ጥያቄ ላይ አትኩረን በእርግጥም አብዛኛዎቹ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያካተቱ ከድምዳሜ ላይ ደርሰናል።»

ስለ ኤርትራ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያተተው ዘገባ በሀገሪቱ ለ25 ዓመታት «ስልታዊ እና መጠነ ሰፊ» የሰብአዊ መብት ጥሰት መድረሱን ገልጧል ። እስከ 400,000 የሚደርሱ ኤርትራውያን በሀገሪቱ ግልጽ ባልሆነ «ብሔራዊ አገልግሎት» ስም ላለፉት 25 ዓመታት ለባርነት ተጋልጠዋል ሲል ዘገባው አክሏል። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ዘገባው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።

«በመሠረቱ ይኽ 500 ግድም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ያገኘውን መረጃ ሳያጣራ ይፋ ያደረገ አካል ነው። የሙያ ስነምግባርን ያልተከተለ፣ ገለልተኝነት የጎደለው፤ ትርጉም አልባ የፖለቲካ ሰነድ ነው።»

በኤርትራ መንግሥት የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ስም ከአስመራ ይፋ የሆነው መግለጫ የአጣሪ ኮሚሽኑ ዘገባን «ባዶ እና ተቀባይነት» የሌለው ብሎታል። በሦስት ሰዎች የተዋቀረው «አጣሪ ኮሚሽን» ተብየው ኤርትራን ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ለማቅረብ ዘመቻ እያካሄደ ነው ለአንድ ወገን አድልቷልም ሲል አክሏል ። አጣሪ ኮሚሽኑ ለዘገባው የተጠቀመባቸውን መረጃዎች የሰበሰበው ከኤርትራ ውጪ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፤ በዋናነትም በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ ከሚገኙ ኤርትራውያን መሆኑን ተናግሯል። ያም ሆኖ ዝርዝር እና ጥልቅ ምርመራ ማድረጉን ገልጧል።

የመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማይክ ስሚዝ በዛሬው መግለጫቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በአስመራ ጎዳናዎች ብቻ ይፈጸማል ብላችሁ አትጠብቁ ብለዋል። ይልቁንስ ጥሰቱ የውጭ ሃገራት ሰዎች ሊመለከቷቸው በማይችሏቸው ራቅ ባሉ የሀገሪቱ ሥፍራዎች ማለትም በማጎሪያ ጣቢያዎች፣ በጦር ሰፈሮች፣ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በኤርትራ «በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል» ተጠያቂ ያሏቸው ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ይገልጡ እንደሆን በዶይቸ ቬለ ተጠይቀው ሊቀመንበሩ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል፤ ሆኖም ከፍተኛ ባሥልጣናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

Eritrea Architektur in Asmara
ምስል Reuters/T. Mukoya

«እነዚህ ሰዎች በሰብአዊነት ላይ ለተፈጸመው ወንጀል መሠረት ለሆነው ፖሊሲ ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው። ከእዚህ በላይ ብዙ ማለት ያለብኝ አይመስለኝም፤ ግን በዘገባችን ከፍተኛ የጦር አመራሮች እና በአመራሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ይካተታሉ ብለናል።»

አጣሪ ቡድኑ የምርመራ ውጤቱን ከሁለት ሳምንት በኋላ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሲያቀርብ ተልዕኮው እንደሚጠናቀቅ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ