1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እገዳ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2011

ኤርትራውያን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን መጠቀም አይችሉም። ያም በመኾኑ ነዋሪዎች መልእክቶችን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለመለዋወጥ የዙር አዙር መንገዶችን መጠቀም የግድ ይላቸዋል ይላል የማልኮም ኦሀንዌ የዶይቸ ቬለ ቲቪ ዘገባ።  

https://p.dw.com/p/3J34e
Eritrea Straßenszene in Asmara
ምስል Reuters/T. Mukoya

ጀርመን ውስጥ ከሚኖሩ 60,000 ኤርትራውያን አንዱ ነው

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነጻ ሀገር ከኾነች 28 ዓመታትን አስቆጥራለች። ለሦስት ዐሥርተ ዓመታት ደም ካፋሰሰው ጦርነት በኋላ ኤርትራ ነጻነቷን ያገኘችው በ1983 ዓ.ም ነው። የነጻነት ቀኗን ዐርብ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ባከበረችው ኤርትራ የመገናኛ አውታሮች በመንግሥት በኩል ዛሬም ድረስ ጥብቅ ቊጥጥር ይደረግባቸዋል። ኤርትራ ሀገር ከኾነችበት ጊዜ አንስቶ የምትመራው በፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ነው። 20 በመቶ ያኽሉ ኤርትራዊ በስደት ውጭ ሃገራት ይኖራል።  5 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት አነስተኛዋ የአፍሪቃ ሀገር ለምን ያን ያኽል ነዋሪዎቿ ለስደት ተዳረጉ ሲል ይጠይቃል ማልኮም ኦሀንዌ  በዘገባው። ይኽን ጥያቄውን ይዞም ኤርትራውያንን ለማናገር በርሊን ውስጥ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን አቀና። 

ከማለዳው 12 ሰአት። ሙሉ ሐዲሽ በርሊን ውስጥ ወደሚገኘው ቅዱስ ፊሊጶስ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እየገባ ነው። የ29 ዓመቱ ኤርትራዊ ስደተኛ ሙሉ ሐዲሽ ላለፉት 9 ዓመታት ከኤርትራ ርቆ ቆይቷል።

«ሀገር ቤት ልጅ ሳለሁ ከአባቴ እና ከቤተሰቦቼ ጋር በየጊዜው ወደ ቤተክርስቲያን እንሄድ  ነበር። እዚህ የተለያዩ ጓደኞች አሉኝ፤ እዚህ እንገናኛለን። ሳምንቱን ሙሉ በትጋት ስሠራ ቆይቼ በሰንበት ወደዚህ እመጣለሁ። ለእኔ መልካም ነው።»

Libyen Migranten vor der libyschen Küste
ምስል picture-alliance/AP Photo/O. Calvo

ሙሉ ጀርመን ውስጥ ከሚኖሩ 60,000 ኤርትራውያን አንዱ ነው። አብዛኛዎቹ ወታደራዊ አምባገነንነትን በመሸሽ የመጡ ናቸው፤ እንደዚህ አይነት አብያተ-ክርስቲያናት ለእነሱ ወሳኝ መገናኛ ቦታ ነው። ውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ግማሽ ያኽሉ ክርስቲያኖች ናቸው፤ ቀሪዎቹ ሙስሊሞች።

ሙሉ እና ጓደኛው ዘረሰናይ ከቤተክርስቲያን መልስ ወደ መጠለያ ጣቢያቸው ለመመለስ በአውቶቡስ የ2 ሰአት ጉዞ ማድረግ አለባቸው። በጉዞው ወቅት በተለያዩ ሃገራት አቋርጠው እንዴት ጀርመን እንደመጡ ሙሉ እንዲህ ይተርካል።

«መጀመሪያ ከኤርትራ ኢትዮጵያ ሄድኩ። ከዚያ ወደ ሱዳን፤ ከሱዳን ወደ ግብጽ፤ ከግብጽ ደግሞ ወደ እስራኤል። ከዚያ በኋላ ከእስራኤል ወደ ሩዋንዳ፤ ከሩዋንዳ ወደ ኡጋንዳ፤ ከኡጋንዳ ወደ ደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ፤ ከሱዳን ሊቢያ፤ ከሊቢያ ጣልያን፤ እናም ከዚያ ወደ ጀርመን። »

ሙሉ የዓለምን ግማሽ ለመሽከርከር ፍላጎቱ እንዳልነበረው ግልጽ ነው።

«ምርጫ አልነበረኝም፤ ምክንያቱም ኤርትራ የምትመራው በአምባገነን ነው። ሽሽቴ ብዙ አስከፍሎኛል። ትምህርት ቤት መሄድ፤ ሁሉ ነገር ጊዜዬ ባክኖብኛል።»

ከኤርትራ ከወጡ በኋላም የገጠማቸው መከራ ነው። የሙሉ ጓደኛ ዘረሰናይ በትውስታ ወደ ኋላ ይመለሳል።

«ሊቢያኖች በጣም ጨካኞች ናቸው። ቁምስቅል ፈጽመውብን ማጎሪያ ውስጥ ነበር ያጨቊን።»

Hungary Migrants
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Bandic

ከሀገር ርቀው ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት የሚጥሩት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ነው። ኾኖም ኤርትራ ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ በማገዷ ሙሉ እና ዘረሰናይ ቤተሰባቸውን ኤርትራ ውስጥ በየጊዜው ማግኘት ይሳናቸዋል።

«በዳያስፖራ ብዙ ሰልፎች ስለሚደረጉ ነው ኢንተርኔቱን የሚዘጉት። በሰልፎቹ ላይ የሚገኙ ሰዎችንም ማወቅ ይፈልጋሉ።»

«እኔ አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቼ ጋር መደወል እችላለሁ፤ ግን ስለፖለቲካ አለያም ስለ አምባገነንነት አላወራቸውም።»

ሙሉ በኤርትራ የመንግሥት ለውጥ ይኖራል የሚል እምነት የለውም። ጀርመን ግን በሯን እንደማትዘጋበት ተስፋ ሰንቋል።

ማልኮም ኦሀንዌ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ