ኤርትራ፤ የፕረስ ነፃነትና ምስራቅ አፍሪቃ
ሰኞ፣ የካቲት 5 1999ስለኤርትራም አዎንታዊ የሆነ ዘገባ በተለይ ከፕረስ ነፃነት ጋ ተያይዞ ብዙም አይሰማም። ከወራት በፊት በቁም እስር ላይ የከረመዉ የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ከአገር የመዉጣቱ ዜና ተሰምቷል። ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ በእስር ላይ የነበረዉ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ፍስሃዬ ዮሃንስ ህልፈተ ህይወት ተሰምቷል። የኤርትራዉ ተጠባባቂ የማስታወቂያ ምኒስትር አቶ አሊ አብዶ ደግሞ ይህን አስመልክቶ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ከስራ ሃላፊነቴ ጋ አይየናኝም በማለት ምንም እንደማያዉቁ ነዉ ለዶቼ ቬለ የገለፁት።
ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ባለፈዉ ዓመት የገመገመዉን የፕሬስ ነፃነት ይዞታ ባቀረበበት ዘገባ ከ168ሀገራት መካከል ለኤርትራ በዚህ ረገድ የሰጣት ደረጃ 166ኛ ነዉ። የኤርትራ የፕረስ ነፃነትም የተሻለ የተባለዉ በዘገባዉ መሰረት 168ኛ ደረጃ ከያዘችዉ ከቻይና እንዲሁም 167ኛ ደረጃ ላይ ከሰፈረችዉ ቱርክሜኒስታን ጋ ተነፃፅሮ መሆኑ ነዉ።
ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ዕለት ደግሞ ይኸዉ ቡድን ይፋ ያደረገዉ ዘገባ በድብቅ ለስድስት ዓመታት ታስሮ የነበረዉ ኤርትራዊ ገጣሚና ጋዜጠኛ ፍርስሃዬ ዮሃንስ በከረመበት የተወሳሰበና ሰብዓዊነት የጎደለዉ ይዞታ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ገልጿል።
ለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የሚሟገቱ የተለያዩ ድርጅቶች ነፃ ፕረስ የለባትም በሚሏት ኤርትራ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች መኖራቸዉን ደጋግመዉ በስም በመጥቀስ ይናገራሉ።
የፕረስ ነፃነት በአገራችን ያወጅነዉ በሌላ ታዞልን ሳይሆን በመሰረታዊ ሃሳቡ ስለምናምን ነዉ የሚሉት የኤርትራ ተጠባባቂ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ከፕሬስ ነፃነት ጋ በተያያዘ ኤርትራ በዓለም ያላት ገፅታ ያሳሰባቸዉ እንደሆነ ተጠይቀዉ ነበር፣
«የራሳችን የሆነ ተመክሮ አለን፤ ነፃ ፕሬስም አለን። ይህን ያደረግነዉ በመሰረተ ሃሳቡ ስለምናምን እንጂ ማንም ከዉጪ አዞልን ወይም ጭኖብን አይደለም። እንዳለመታደል ሆኖ መጥፎ የሆነ ተመክሮ ነዉ በዚህ ረገድ ያለን። ይህን ተመክሮ እንደገና ልናየዉና ለአገራችን ጥቅም በሚዉልበት መልኩ ለማድረግ እየሞከርን ነዉ።»
የተባበሩት መንግስታት በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰፍር ያሳለፈዉን ዉሳኔ በይፋ ከተቃወሙት ሀገራት መካከል ሱዳንና ኤርትራ ይገኙበታል። በተለይ ኤርትራ ወደሶማሊያ ወታደሮችን አስገብታለች የሚል የቀረበባትን ክስ ስታስተባብል፣ ሶማሊያዉን የራሳቸዉን ችግር ያለማንም ጣልቃ ገብነት ይፍቱ የሚል አቋሟን በመደጋገም ስታስተጋባ ሰንብታለች።
በሶማሊያ የተደላደለ መንግስት የለም ለአገሪቱ ዘላዊ መፍትሄ የሚያመጣዉ ምን ይመስሎታል፣ አሁን ካለበትስ ደረጃ ወዴት መሄድ ይቻላልም ተብለዉ ነበር፣ እሳቸዉም ሲመልሱ
«በሶማሊያ ፌደረላዊ የሽግግር መንግስት ነዉ ያለዉ። በእኛ በኩል በሶማሊያ ከራሱ ከህዝቡ የሚመጣ መፍትሄ ብቻ ነዉ ችግሩን የሚፈታዉ የሚል ጠንካራ እምነት ነዉ ያለን። ብቸኛዉ መፍትሄም ሶማሊያዉያን ከሶማሊያዉያን ጋር የሚያደርጉት ዉይይት ነዉ። በዚያም ላይ ለፖለቲካ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ መገኘት አለበት። ከዉጪ የሚደረግ ድጋፍ ካለም ሰላማዊዉን መፍትሄ ለማምጣት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብቻ መሆን ይኖርበታል።»
የአፍሪቃ ህብረትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ወደሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት የመላኩን ሃሳብ አቶ አሊ ሁሉም ወገኖች ተስማምዉ እንፈልጋለን ሲሉ ነዉ እንጂ በዉጪ ግፊት መደረግ የለበትም የሚል አቋም ነዉ ያላቸዉ።
ተንታኞች የሶማሊያ ሰላም ማጣትና አለመረጋጋት ለአጎራባች ሀገራትም አስጊ መሆኑን ደጋግመዉ ተናግረዋል። ወታደሮች ወደሶማሊያ እንዳላስገባች ደጋግማ የገለፀችዉ ኤርትራ አለመረጋጋቱ አያሰጋት ይሆን?
«በእርግጥ በየትኛዉም የዓለም ክፍልም ሆነ በተለይ ደግሞ በአካባቢያችን በሚፈጠር ያልተረጋጋ ሁኔታ መስጋታችን አይቀርም። ሆኖም መረጋጋት ለመፍጠር ጫና መደረግ የለበትም። በጋራ ስምምነት ነዉ። በዚህ ጉዳይ ከምንም ነገር በፊት ስለሶማሊያ ህዝብ ማሰብ አለብን። የራሳቸዉን እድል ራሳቸዉ መወሰን አለባቸዉ። በተጨማሪም የመፍትሄያቸዉም ባለቤቶች ራሳቸዉ መሆን አለባቸዉ።»
ዶቼ ቬለን ባለፈዉ ዓርብ የጎበኙት አቶ አሊ አብዶ በሶማሊያ ይህን መሰሉ ችግር በቅርቡ ሳይከሰትና ከኢትዮጵያ ጋርም በድንበር ዉዝግብ ጦርነት ዉስጥ ሳትገባ በፊት አገራቸዉ አግኝታ የነበረዉን ዓለም ዓቀፍ አዎንታዊ እይታ በማሻሻል ለቱሪስት መስህብም ሆነ በኢንቬስትመንት ዘርፍ የተጀመረዉ እንዲያንሰራራ የሚደረገዉን ጥረትም ገልፀዋል
«ከ1984ዓ.ም በኋላ ከዜሮ ተነስተን ነዉ በ30ዓመታት የትጥቅ ትግልና በ60ዓመትቱ ቅኝ ግዛት የተጎዳችዉን አገራችንን ለማስተካከል እየታገልን የነበረዉ። በዚያን ጊዜ በተለይ ከ1984እስከ 1987 ድረስ ምጣኔ ሃብታችን ሰባትና ስምንት በመቶ ከፍ ብሎ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ጥርነቱ በኢትዮጵያ ተጫነብን። እኛምበሰላማዊ መንገድ ልንፈታዉ ታገልን። የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ኢትዮጵያ ጦርነት እንዳወጀችብን በኃይል ከመጠቀም ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ችግሩን ለመፍታት ጠይቆ ነበር። ያ ግን ሊሆን አልቻለም። ከሶስት ከባድ ዓመታት በኋላ አልጀርስ ላይ ተስማማን። ከዚያም በ1994 የመጨረሻና አሳሪ ዉሳኔ ተላለፈ። አሁን የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ትኩረታቸዉንና አቅማቸዉን ልማት ላይ ያደርጋሉ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይህ ከሆነ በጣም እርግጠኛ ነኝ ያለንን አቅም ሁሉ አገራችንን ለመገንባት እናዉለዋለን።»