1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እምብዛም ያልተራመደዉ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2011

ኢትዮጵያና ኤርትራ 20 ዓመት ያስቆጠረውን ፍጥጫና ኩርፊያ ለማስወገድ ቢስማሙም ሠላምን ለማፅናት የታሰበዉን ያህል እርምጃ አልተራመደም። የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አስመራን ለመጀመሪያ ጊዜ ከጎበኙ በዚህ ሳምንት አንድ ዓመት ሆናቸዉ። «የአስመራ መግለጫ» የተባለዉን ውል የፈረሙት ዐቢይ አስመራን በረገጡ በነጋታዉ እንደነበር ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/3M0aB
Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

የኤርትራ መንግሥት ግልፅነት ይጎድለዋል

ኢትዮጵያና ኤርትራ 20 ዓመት ያስቆጠረውን ፍጥጫ እና ኩርፊያ ለማስወገድ ቢስማሙም ሠላምን ለማፅናት የታሰበዉን ያህል እርምጃ አለመወሰዱን አንዲት የኤርትራ ጉዳይ አጥኚ አስታወቁ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አስመራን ለመጀመሪያ ጊዜ ከጎበኙ በዚህ ሳምንት መጀመርያ አንድ ዓመት ሆናቸዉ። ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ «የአስመራ መግለጫ» የተባለዉን ውል የፈረሙት ዐቢይ አስመራን በረገጡ በነጋታዉ እንደነበር ይታወሳል። የአስመራና የአዲስ አበባ መንግሥታት ጦራቸዉን ካዋሳኝ ድንበሮች ማንሳት፣ የየብስና የአየር መስመሮችን መክፈት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መቀጠልን ጨምሮ ስር የሰደደዉን ጠብ ለማስወገድ የሚረዱ በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል። ብሪታንያዊቱ የኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ አጥኚና ደራሲ ሚሻኤላ ሮንግ እንደሚሉት ግን የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት አጀማማሩ ላይ የነበረዉ ዓይነት ተስፋ አልቀጠለም። «ድንበርን የማካለል ምልክት እስካሁን የለም። ነገሮች ተስፋ እንዳደረግነዉ አይደሉም። በጣም አሳሳቢዉ ኤርትራዉያን ወጣቶች ለብሔራዊ ውትድርና መመልመላቸዉ ነዉ። ክፍት የነበረዉ ድንበርም ዳግም ተዘግቶአል። 
«እንደተባለዉ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለዉ ድንበር ዳግም ተዘግቷል። በሃገራቱ መካከል ድንበር የማካለል ፍንጭም እስካሁን አልታየም። ነገሮችም በተፈለጉበት እና ተስፋ በተጣለባቸዉ መንገድ አልተሻሻሉም። ዋናዉ ነገር በኤርትራ አሁንም  የብሔራዊ ውትድርናዉ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። በዚህም ዋናዉ እና አሳሳቢው ነገር ኤርትራዉያን ሃገራቸዉን እየጣሉ መሰደዳቸዉ ነዉ።»  
ሃገራቱ ለዓመታቶች ዘግተዉ የቆዩትን ድንበር ከፍተዉ መልሰዉ የዘጉበት ምክንያት ምን እንደሆን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም ያሉት ብሪታንያዊቱ የኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ አጥኚ ሚሻኤላ ሮንግ ፤ የኤርትራ መንግሥት ለምን እንደዘጋ በግል ይፋ ያደረገዉ ነገር የለም የአስመራዉ መንግሥት ግልፅ እንዳልሆነ ይታወቃል ሲሉ ገልፀዋል። እንድያም ሆኖ በሁለቱ ሃገራት መካከል የንግድ እና የመገበያያ ገንዘብ ጉዳይ በሁለቱም መንግሥታት ስላልተቋጨ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።  

Äthiopien Rückkehrer am Flughafen Asmara
ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

«እንደምገምተዉ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ ሸቀጦቻቸዉን ይዘዉ ወደ ኤርትራ መግባታቸዉና አብዛኛዉ ኤርትራዉያ ሸቀጡን መግዛት ባለመቻላቸዉ ይመስለኛል። በርካታ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ኤርትራ ዉስጥ ንግድ መጀመራቸዉ ለሀገሪቱ የንግድ ባለሥልጣንም አላመቸ ይሆናል። የድንበር መዘጋቱ ምክንያት ይህን እና የመሳሰሉት ነገሮችን ለመቆጣጠር ያደረጉት ርምጃ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ሃገራቱ የመገበያያ ገንዘብን በተመለከተ ምንም የተስማሙበት ነገር የላቸዉም። የብር ዋጋዉ ምን ያህል ነዉ? የኤርትራዉ ናቅፋስ ምን ያህል ዋጋ አለዉ? የሚለዉ ጥያቄ መቋጫ አልተሰጠዉም። የኤርትራ መንግሥት ግን ስለድንበር መዘጋትም ሆነ በአጠቃላይ ምንም በግልፅ የሚናገረዉ ጉዳይ የለም። ግልፅነት ይጎድለዋል።» 
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸዉ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የማውቀው ነገር የለም ሲሉ የተናገሩት ሚሻኤላ ሮንግ፤ አዲስ አበባ የሚገኘው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ስለ ኤርትራ የሚያነሳበት ጊዜ ሳይሆን በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩትን ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ቅድምያ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ መስጠቱ ግልፅ ነዉ።   
«በርግጥ ስለሁለቱ ሃገራት ወቅታዊዉ ግንኙነት ምንም የማዉቀዉ ነገር የለም። እንደሚመስለኝ ግን አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የሚያሳስበዉ አይመስለኝም በአማራ ክልል ተደረገ ስለተባለዉ መፈንቅለ መንግሥት ጉዳይና ስለተገደሉት የባለስልጣን ሁኔታ ነዉ። ሃገሪቱን በማረጋጋት ፤ በዉስጥ ፖለቲካዊ ጉዳይ ስለተጠመደ በወቅቱ የኤርትራ ጉዳይ እጅግም አሳሳቢ አይመስለኝም። ቢያንስ አሁን ስለኤርትራ የሚያነሳበት ጊዜ አይደለም ብዬ አስባለሁ።»
ሮንግ ኤርትራን በተመለከተ አንደኛ በውትድርና የሰለጠኑ ወጣቶች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ይኖርባቸዋል፤  ሁለቱ አጎራባች ሃገራት የድንበር ኮሚሽኑ የወሰነዉን የድንበር መስመር ማካለል አሳሳቢ የሚሉዋቸዉ ሁለት ጉዳዮች መሆናቸዉን ተናግረዋል።  
« ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችውን ሰላምና የድንበር መከፈት ርምጃን ተከትሎ ለዓመታት ያሰለጠነቻቸዉን ወታደራዊ ኃይላት ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ብቻኛ ዕድል ባለመጠቀምዋ የሚያሳዝን ነዉ። የኤርትራ መንግሥት አሁን ይህን ያህል ግዙፍ የሆን ወታደራዊ ኃይልን ለመያዝ ይሄ ነዉ የሚባል ምንም ምክንያት የለዉም። መንግሥት ይህን ርምጃ የማይወስድ ከሆነ ወጣት ኤርትራዉያን በሕገ-ወጥ ድንበርን እየተሻገሩ ኢትዮጵያ ወደሚገኘዉ የስደተኛ ጣብያ ያመራሉ። በረሃ አቋርጠዉ እስራኤል  ይገባሉ። ወደ አዉሮጳ ለመሻገር በጀልባ ሜዲተራንያን ባሕርን ሲቀዝፉ በመቶዎች የሚቆጠሩት ሰምጠዉ ይሞታሉ። ይህ ሁሉ በጣም የሚያሳዝን ነዉ። የኤርትራ መንግሥት ይህን የመሰለ እድልን ማየት አልቻለም ማለት ይቻላል። ወጣቱን በዚህ መልክ የሚይዘዉ፤ ወታደራዊ ስልጠናዉ ወጣቱን በቁጥጥር ስር ሰለሚይዝለት የአረብ አብዮት የመሰለ አይነት ንቅናቄ ኤርትራ ዉስጥ እንደማይከሰት ጠንቅቆ ያዉቃል። ወጣቱ በሳዋ ጦር ማሰልጠኛ ዉትድርና ልምምድ ያደርጋል እንጂ አብዮት ሊያስነሳ ጎዳና አይወጣም። » ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸዉ የነበረዉን ጠብ በሰላም ለመፍታት ያደረጉት ስምምነት ከምዕራባዉያን መንግሥታት  ከፍተኛ ድጋፍና አድናቆት አትርፏል። ብሪታንያዊትዋ የኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ አጥኚ ሚሻኤላ ሮንግ  በኤርትራ ስለሚካሄደዉ ብሔራዊ ዉትድርና ጉዳይ መንግሥት የሚያካሂደዉን ለዉጥ ማየት እንፈልጋለን። በሌላ በኩል ሁለቱ ሃገራት ጦርነት ዉስጥ ገብተዉ የነበሩት በድንበር ዉዝግብ ጉዳይ በመሆኑ ሃገራቱ ወደፊት ይህን የድንበር ጉዳይ መቋጫ ካላበጁለት አደጋ ሊያመጣ ይችላል ሲሉ አሳስበዋል። የድንበር መስመሩ የት ጋ እንደሚዉል የድንበር አካላይ ኮሚሽኑ በግልፅ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። እናም በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ላይ የሚነሳዉ ግዙፍ ጥያቄ ፤ የግዳጅ ብሔራዊ ዉትድርና የተመለመሉት ወጣቶች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ እና፤ የኤርትራና ኢትዮጵያን እና ድንበር ማካለል የሚሉት ርዕሶች ናቸዉ፤ ሲሉ ከ ዶይቼ ቬለ «DW» ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ቋጭተዋል።          

Äthiopien und Eritrea Frieden Logo
ምስል DW/S. Fekade

አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ