ከወደ ቻይና የሚጠበቀው የብድር ማስተካከያ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 30 2010ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የተሳተፉበት የቻይና አፍሪቃ የትብብር ጉባኤ ሲጠናቀቅ ሁለቱ ወገኖች ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ማቀዳቸውን ገልጸዋል። በጉባኤው መክፈቻ 60 ቢሊዮን ዶላር በእርዳታ፣ በመዋዕለ-ንዋይ እና በብድር መልክ ለአፍሪቃ ለማቅረብ ቻይና መዘጋጀቷን ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ዢ ሺንፒንግ በመዝጊያውም "ቻይና እና አፍሪቃ ኃላፊነትን በጋራ በመወጣት፣ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ትብብር፣ ለሁሉም ደስታን የሚያጎናፅፍ፤ የጋራ ባሕላዊ ብልጽግና እና የጋራ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ የጋራ ርዕይ ያለው የቻይና-አፍሪቃ ማኅበረሰብ ለመመሥረት እጅ ለእጅ ይያያዛሉ" ሲሉ ተናግረዋል። የቻይናን እገዛዎች ያደነቁት የመድረኩ ተባባሪ ፕሬዝዳንት እና የደቡብ አፍሪቃው መሪ ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ቻይና ከአፍሪቃ ከጥሬ ዕቃ ይልቅ እሴት የተጨመረባቸው ሸቀጦች ለመሸመት መሥማማቷን ገልጸዋል። ጭብጨባ እና ሙገሳ የበረታበት የቻይና እና የአፍሪቃ የትብብር ጉባኤ ተስፋ በሚያጭር መግለጫ መጠናቀቁ ቢገለፅም ግንኙነቱ ግን ለሁሉም ወገኖች ዕኩል ፋይዳ የለውም። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪቃ አገሮች የዕዳ ጫና በርትቶባቸዋል።
ለባቡር እና የመንገድ ግንባታዎች፣ ለቴሌኮም ማስፋፊያዎች፣ ለኃይል ማመንጫ እና ማሸጋገሪያ ዕቅዶች ጠቀም ያለ ገንዘብ ከቻይና የተበደረችው እና የዕዳ ጫና ውስጥ የወደቀችው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር እንኳ አማራጭ ማማተር የያዙ ይመስላል። በርካታ ተንታኞች ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን እንደያዙ ወደ ቻይና ይጓዛሉ ብለው ቢጠብቁም እርሳቸው ግን መካከለኛው ምሥራቅ እና አሜሪካን አስቀድመዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም "ጠቅላይ ምኒስትሩ እና አዲሱ አመራር ሊከተለው የፈለገው ፖሊሲ" ጠቋሚ አድርገው ይቆጥሩታል። አቶ ጌታቸው "ገዢው ፓርቲም መንግሥትም እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኛውን የልማት ፋይናንስ ከቻይና የማግኘት አቅጣጫ ነው ሲከተሉ የነበረው። ይኸ ከገዢው ፓርቲ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ አንፃር የተቃኘ ነው። የአገሪቱ ውጪ ብድር ክምችት ውስጥ አብዛኛው ከቻይና የሚመጣ ነው። ለብዙ ዓመት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችም፣ ባለሙያዎችም ሁሉንም እንቁላል በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስገባት ኤኮኖሚያዊ ዋጋው ውድ ነው። ዋጋ ያስከፍላል፤ ቅርጫቱ የሆነ ነገር በሆነ ሰዓት የሚናጋው ጠቅላላ ኤኮኖሚው ነው። ስለዚህ የልማት ፋይናንስንም ከቻይና ብቻ መውሰድ ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ እውነታዎቹ የሚደግፉት ቢሆንም ምንጩ ዳይቨርሲፋይ መደረግ አለበት እያሉ ሲወተውቱ ነበረ። በአዲሱ አስተዳደር እሱ በተወሰነ መልኩ ተሰሚነት ያገኘ ይመስላል። በቅርብ ጊዜም እንደተመለከትንው የልማት ፋይናንስን ለማግኘት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በአንድ በኩል በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ባለሐብቶች ለማዘዋወር የተወሰደ እርምጃ አለ። ከዛ ውጪ ደግሞ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተገኘ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት እና የውጭ ምንዛሪ አለ። እሱ በተወሰነ መልኩ አመላካች ነው" ሲሉ ለዲ ደብሊው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ዕርቅ ከፍ ያለ ሚና ተጫውታለች የሚባልላት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመዋዕለ-ንዋይ እና በጥሬው ለመስጠት ቃል ከገባችው ሶስት ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ፈቃደኝነት ማሳየቱን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትክክለኛውን ጊዜ ባይናገሩም የዓለም ባንክ "በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀጥታ በጀታችንን ይደግፋል" ብለው ነበር።
ጠቅላይ ምኒስትሩ የተካፈሉበት የትብብር ጉባኤ የቻይናን ዕገዛ አጥብቀው ለሚሹት ነገር ግን የዕዳ ጫና ለበረታባቸው የአፍሪቃ አገራት ሁለት አበይት ውሳኔዎችን ይዞ መጥቷል። የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ዢ ሺንፒንግ እንዳሉት የቻይና ብድር ከእንግዲህ ለአፍሪቃውያኑ አገሮች እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ እንዳልሆነ ጠቁሟል። የቻይና አፍሪቃ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ቻይና አገሪቱ አቋም መቀየሯን ታዝበዋል። "ከዚህ በፊት ቻይና ለአፍሪቃ አገሮች ዝም ብሎ ገንዘብ ትሰጣለች የሚል አመለካከት አለ። ቻይና ውስጥም ሌላው ዓለምም እንደዚህ ነው የሚያየው። አሁን ግን ቻይና የምትለው እኛ ከአፍሪቃ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ማድረግ እንፈልጋለን። በዚህ ጥብቅ ግንኙነት ውስጥ ግን የምንሰጣቸውን ፕሮጀክቶች መቆጣጠር መቻል አለብን። ጥቅም አላቸው የላቸውም የሚለውን ይዘን መከተል አለብን። እዚህ ስብሰባ ላይ እንደዚያ እንዲሆን ነው የምንፈልገው ብለው በግልጽ ተናግረዋል። ይኸ ማለት ምንድነው አፍሪቃውያን አገሮች ወደ ፊት ለማይረቡ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ከቻይና አይሰጣቸውም። ከዚህ በፊት ትልቁ ችግር እሱ ነበር" ይላሉ አቶ አሌክሳንደር።
የአዋጭነት ጉዳይ ከተነሳ በቻይና ብድር በኢትዮጵያ የተገነቡ መሠረተ-ልማቶች በልሒቃኑ ዘንድ ጥያቄ ውስጥ መግባታቸው እየተሰማ ነው። ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የምርት መጠን 59 በመቶ የደረሰው የዕዳ ክፍያ ጫና መጨመር ባለወረቶችን ሐሳብ ላይ እንደጣላቸው ባለፈው ሐምሌ በአፍሪቃ ኅብረት የቻይና ተልዕኮ በድረ-ገጹ አስታውቋል። የቻይና ልሒቃንን በማሰልጠን የሚታወቀው እና መቀመጫውን በቤጂንግ ያደረገው የፓርቲ ማዕከላዊ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ዛሆ ሌይ በኢትዮጵያ የተገነቡ መሠረተ-ልማቶች ዘላቂ አይደሉም ሲሉ የኮምኒስት ፓርቲው ልሳን በሆነ ጋዜጣ ላይ መፃፋቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። አቶ ጌታቸው ግን "ቻይና እስከ ዛሬ ስትከተለው የነበረዉ የፋይናንስ አጠቃቀም በኤኮኖሚው ውስጥ የራሱ የሆነ ሥጋት እያመጣባት እንደሆነ ገብቷታል። ስለዚህ ካለፉት ሁለት ሶስት አመታት ወዲህ ጥንቃቄ የተሞላበት የውጭ ፋይናንስ አቅርቦት ነው እየተከተሉ ያሉት። ለኢትዮጵያ የልማት ፋይናንስ ከመስጠት አንፃር የታየው ቁጥብነት ከጠቅላላ የኤኮኖሚ ፖሊሲው የሚመነጭ ነው። እኔ ባለኝ መረጃ አብዛኛው የቻይና ብድር በኢትዮጵያ የሚውለው መንገድ፤ የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች፤ የኃይል ማጓጓዣ እና ማሰራጫ መስመሮች የቴሌኮም ማስፋፊያዎች በመሳሰሉ የኤኮኖሚ መሠረተ-ልማቶች ላይ ነው። የሚሰጡትንም ብድር ለገንዘቡ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ በሚችል ዘርፍ እናውለዋለን ነው የሚሉት። እንግዲህ ብድሩ በሚሰጥባቸው ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያክል ትርጉም ያለው ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም" ይላሉ።
ቻይና ከውስጥ በሚነሱባት ጥያቄዎች እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት የገንዘብ አቅርቦቷን ለመፈተሽ መገደዷን አቶ አሌክሳንደር ያስረዳሉ። ባለሙያው የኢትዮጵያ ዕቅዶች እንከን ቢበረታባቸው እንኳ ቻይና ለዘላቂ ጥቅሟ ስትል ገሸሽ ልታደርጋት አትችልም የሚል ክርክር አላቸው። "የቻይና አስተያየት ወደ አፍሪቃ ሲመጣ እየተለወጠ እየመጣ ነው። ይኸ ማለት እነ ማን ናቸው ጠቃሚ አገሮች የሚል ጥያቄ ተነስቷል። ለቻይና እድገት ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ማን ነው የሚል ትልቅ ጥያቄ አለ። ቻይና የሚጠቅሟትን አገሮች የበለጠ ለመርዳት ትፈልጋለች። ከዛ ውስጥም አንዷ ኢትዮጵያ ነች። አንዳንዶቹ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ችግር ገጥሟቸዋል። የስኳር ፕሮጀክቶችን ብናይ ችግር አለ። የባቡር ፕሮጀክቶቹ በሥነ-ሥርዓቱ ብድራቸውን መክፈል አይችሉም። ሆኖም ግን ቻይና ይኸን እያወቀች ኢትዮጵያን ወደ ጎን መግፋት አትፈልግም"
በአሜሪካው ጆን ሖፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ይፋ ያደረገው ሰነድ እንደሚጠቁመው ባለፉት 18 ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ ከቻይና 12.1 ቢሊዮን ዶላር ተበድራለች። እንደ ተቋሙ ጥናት ከሆነ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎች የተበደረችውን ጨምሮ በአጠቃላይ 29 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት። ቻይና ታዲያ ከፍተኛ እዳ ላለባቸው ደሐ፤ ወደብ አልባ አገሮች እና ትንንሽ ደሴቶች የብድር ማስተካከያ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
ወደ ቤጂንግ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ዢ ሺንፒንግ እና ጠቅላይ ምኒስትር ሊ ኬጊያንግ ጋር የመከሩት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ታዲያ አገራቸው ያጎበጣትን የዕዳ ጉዳይ ማንሳታቸው አልቀረም። ለበርካታ የኢትዮጵያ የግንባታ ዕቅዶች ብድር በማቅረብ ከሚታወቀው የኤክዚም ባንክ ሊቀ-መንበሪት ሑ ዢያዖሊያን ጋር ተገናኝተው አገራቸው ያለባትን ዕዳ አከፋፈል ስለ ማስተካከል መምከራቸውን የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ አስታውቀዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም "ኢትዮጵያ ከቻይና የወሰደቻቸውን ዋና ዋና የሚባሉትን ብድሮች የመክፈያ ጊዜ የማስተካከል እርምጃ ይወሰዳል ብዬ እገምታለሁኝ። የልማት ፋይናንስ ማዕቀፋቸውን በማያውክ መልኩ የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። አንዳንዶቹ በጥሬ ገንዘብ ነው የሚከፈሉት። ኤክስፖርት ክሬዲት በምንለው ነው። ስለዚህ ምን አልባት የአከፋፈል ለውጦችም ሊኖሩ ይችላሉ" ሲሉ በቀጣይነት ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎች ያስረዳሉ።
የታሰበው ተሳክቶ የብድር ማስተካከያ ከተደረገ በጫና ውስጥ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን አቶ ጌታቸው ያምናሉ። "ኤኮኖሚው በአመት ለብድር ክፍያ የሚያወጣው ወጪ እጅግ ብዙ ነው። በዚህም አመት በበጀቱ ውስጥ ለብድር ክፍያ የያዘው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው። ከዚያ ውጪ ኤኮኖሚው የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት ባልቻለበት እና እጥረት ገጥሞት ባለበት በዚህ ሰዓት ክፍያው በውጭ ምንዛሪ እንዲሆን ነው የሚጠበቀው። ካሉብን ተደራራቢ ነገሮች ኤኮኖሚውም ካለፉት ሶስት አመታት የአለመረጋጋት ጊዜያቶች ለመውጣት ጥረት የሚያደርግበት ጊዜ ነው። በፖሊሲ እና በፖለቲካ ምኅዳሩ ያሉ ያለ መረጋጋቶች የፈጠሩት የኤኮኖሚ ጫና አለ። በዚህ ወሳኝ ሰዓት ውስጥ መጠኑ ምንም ይሁን ማንኛውም የብድር ማስተካከያ እርምጃ በጣም ትልቅ ፋታ ነው" ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ