ከድህነት ግብግብ ገጥመው የከሸፉ ህልሞች- ሳዑዲ አረቢያ ደርሶ መልስ
ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2014አብደላ መሐመድ ከሳዑዲ አረቢያ ተመልሶ ደቡብ ክልል አላባ ወረዳ ከእናት እና አባቱ ቤት ከከተመ ገና አስራ አምስት ቀናት ተቆጠሩ። የ31 አመቱ ወጣት "ወላሒ ቢሳካልኝ የእናት እና አባቴን ኑሮ ቀይሬ፤ የተሻለ ኑሮ ላይ እንዲቀመጡ" ለማድረግ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደተጓዘ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ሰለሞን በለጠም በመጀመሪያ ዲግሪው የሚቀጥረው ቢያጣ በወዳጁ ግብዣ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀና። ውጥኑ ከአብደላ የተቀራረበ ነው። "የመጀመሪያው ዓላማዬ ለቤተሰቦቼ ቤት መስራት ነበር። ከዚያ ሲቀጥል ለራሴ ቤት ሰርቼ፤ የምነግድበት ራሴን የምቀይርበት ብር ይዤ ወደ አገሬ መመለስ ነበር" ሲል የጉዞውን ምክንያት ያስረዳል።
" …ግን አይሳካም…አይሳካም"
አብደላ እና ሰለሞን ከኢትዮጵያ ተነስተው ሳዑዲ አረቢያ የተጓዙባቸው ጊዜያት እና የመረጧቸው መንገዶች የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱም የገጠማቸው እምብዛም አይራራቅም። አብደላ ቤተሰብ የመርዳቱ ዓላማ "….አይሳካም…አይሳካም…" እያለ የልብ መሰበሩን በሚያሳብቅ ድምጽ ያስረዳል። ከአብደላ ድምጽ ውስጥ የሚሰማ ተስፋ መቁረጥ ከተደጋጋሚ ሙከራ የተቀዳ ነው። ወጣቱ ለእናቱ የተመኘውን ለአባቱ ያሰበውን ለማሳካት የስደትን እርምጃ እግሩ አንድ ብሎ የቆጠረው 2004 ተገባዶ አዲስ አመት ሊጠባ ሲንደረደር ነበር። "የሔድኩት በጅቡቲ ነበረ። ከአዲስ አበባ ተነስቼ አፋር ክልል ስንገባ በእግር ጀመርን" የሚለው አብደላ ጀልባ እስከ ተሳፈረበት የጅቡቲ ወደብ "በርሐ ለበርሐ አስራ ሰባት ቀናት በእግር ሔደናል" በማለት ተናግሯል።
አብደላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው ከአዲስ አበባ እስከ የመን ለተጓዘበት ለሰዎች አዘዋዋሪዎች አስራ አንድ ሺህ ብር ከፍሏል። የቀይ ባህርን ለማቋረጥ ከሌሎች 80 መንገደኞች ጋር ጀልባ ሲሳፈር "ቀጣይ ሕይወት ይኖረኛል ብዬ አላሰብኩም ነበረ" ሲል ሽው ያለበትን ሥጋት ይገልጸዋል።
የጀልባው ጉዞ " አስፈሪ ነበረ። ነገር ግን በሰላም ተሻግረናል" የሚለው አብደላ የጉዞ አጋሮቹ የገጠማቸው ግን ሌላ ነው። "ከእኛ ኋላ አንድ ላይ በረሐውን የተጓዙ ልጆች ነበሩ። ሳዑዲ አረቢያ ከነበሩ ወንድም እና እህቶቻቸው ጋር ቁጥራቸውን ተቀባብለን ነበረ" የሚለው አብደላ የሰማው መርዶ ነበር። "ስንደውል ´እነሱ ሞተዋል እኮ` አሉን። እንዴት ሆነው ሞቱ? ስንላቸው ´ባህር ላይ እናንተ ከተሻገራችሁ በኋላ ሞተዋል´ አሉን" የሚለው አብደላ የአምስቱ ሕይወት ማለፉን እንደተነገረው ገልጿል።
ጅቡቲ...የመን...ሳዑዲ አረቢያ
ሞት እንዲህ ቢያንዣብብም አብደላ እንደሚለው ወደ ኋላ መመለስ አማራጭ አልነበረም። ቀይ ባህርን ሲሻገሩ የመን ተቀበለቻቸው። የመጀመሪያ ማረፊያቸው ከኢትዮጵያውያን ደላሎች ዘንድ ሆነ። በየመን ባገኟቸው ኢትዮጵያውያን የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር 60 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ መታዘዛቸውን የሚያስረዳው አብደላ መሐመድ ቀጥሎ የገጠመው የከፋ ነበር።
"ጫት [ቅመው] መርቅነው እየመጡ በየደቂቃው እየመቱን አስራ አምስት ቀናት ቆየን" የሚለው አብደላ ከኢትዮጵያ ለደላሎቹ የሚከፈል አስራ አንድ ሺሕ ብር ተላከለት። "ሲላክ ከዚያ እስር ቤት ወጣን" የሚለው ወጣት እግሩ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገሰገሰ።
የአላባው ልጅ ሳዑዲ አረቢያ ሲገባ የጠበቀው የፍየል እረኝነት ነበር። "ያን ጊዜ እኔ የገባሁት ዳየር አካባቢ ነበረ። አል-ዳየር ይባላል። በሶስት መቶ ሪያል ነው የተቀጠርኩት። ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቤት [ፍየሎቹን] ወደ ተራራ አወጣለሁ። አስራ ሁለት ሰዓት ወጥቼ ስድስት ተኩል ሲል አመጣለሁ። ምሳዬን በልቼ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ አርፋለሁ። ከስምንት ሰዓት በኋላ [ፍየሎቹን] ሁለተኛ ዙር አወጣለሁ። ከዚያ እስከ አስራ አንድ ሰዓት ድረስ እሰራለሁ። ከዚያ እመለሳለሁ። ከአስራ አንድ ሰዓት እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ገብስ፣ ሳር ምናምን እሰጣቸዋለሁ። ወተት አልባለሁ" በማለት በሳዑዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠማራበት ሥራ ያስረዳል።
በደቡብ ሳዑዲ አረቢያ በሚገኘው የጂዛን ግዛት አብደላ የጀመረው ሥራ ግን የሚያዘልቀው አልሆነም። "ከእኔ በፊት የሔዱ የሚሰሩትን ሥራ አይቼ ነበር የሔድኩት። ጥሩ ነው ሲባል ነው የሔድንው። ግን እዚያ ደርሼ ሳይ እንዳሰብኩት አልሆነልኝም" ሲል ይናገራል። "ውሻ አህያ እየተባልኩ እየተሰደብኩ ነበር የምሰራው" የሚለው አብደላ ሥራውን ትቶ የተሻለ ፍለጋ ወደ ጂዳ ተጓዘ።
ወጣቱ በጂዳም የጠበቀው የፍየል እረኝነት ሆነ። ደሞዙ ወደ 600 ሪያል ከፍ ሲል የሚንከባከባቸው ፍየሎች ቁጥር 420 ደረሰ። እንደ ቀደመ ሥራው ፍየሎቹን ይዞ ለግጦሽ መውጣት አይጠበቅበትም። ነገር ግን የአገሩን ሙቀት መቋቋም አልሆነለትም። ለጉዞ ያልሰነፈው እግሩ ወደ መካ መራው። የጉልበት ሥራ ተገኘ።
"ቤት ወይም ግቢ ሲሰሩ ስሚንቶ እና አሸዋ እናቦካ ነበረ። የምትሰራው ከፓኪስታናዊ ወይም ከግብጻዊ ጋር ነው። እረፍት የለም። ቀኑን ሙሉ ጸሀይ ላይ ነው የምትውለው። እረፍት ብታገኝ በምሳ ሰዓት ብቻ ነበር። ሌላ ጊዜ የእረፍት ሰዓት የለም። መሐንዲሶቹ የሚሰሩት ሁለት ሶስት ሆነው ነው። አንተ የምትሰራው አንድ ብቻህን ሆነህ ነው። ያ ጊዜ በጣም ይከብዳል" እያለ በሳዑዲ አረቢያ የሁለተኛ ሥራውን ባህሪ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። ይሁንና በመካ ከተማ በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ በግዳጅ ተመለሰ። ይኸ "የእናት እና አባቴን ኑሮ ቀይሬ" የሚል ህልም ለነበረው አብደላ የኋልዮሽ ጉዞ ነበር። ወጣቱ በሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሲገደድ የልቡ አልሞላም።
"ምንም ሥራ የለም" ሰለሞን በለጠ በወልድያ
አብደላ እና በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ በሚቸገሩባቸው አመታት በሰሜን ወሎ ዞን ሰለሞን በለጠ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በመጀመሪያ ዲግሪ ስፖርት የተማረው ሰለሞን ሥራ ፍለጋው ቢሰምር ኖሮ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ወይም የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል መምህር በሆነ ነበር። በ2010 ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለተመረቀው ወጣት ግን ሥራ ማግኘት እንዲህ ቀላል አልሆነም። "ምንም ሥራ የለም በቃ። ግቢ ከፍተኛ ውጤት ያመጣ ከሆነ በመንግሥት ይመደባል። የእኔ ግን ትንሽ ዝቅ ይል ነበር። ከዚያ በመወዳደር ማለፍ አልቻልኩም" በማለት በኢትዮጵያ የገጠመውን መለስ ብሎ ያስታውሳል።
ሥራ ፍለጋ ላደከመው ወጣት ከወደ ሳዑዲ አረቢያ የምሥራች የሚመስል ጥሪ ብቅ አለ። በሳዑዲ አረቢያ የነበረው ጓደኛው "መንጃ ፈቃድ አውጥተህ፣ ደልቶህ የሐብታም መኪና ይዘህ [ሰው] እያመላለስክ [ትሰራለህ።] አንተ ደግሞ የተማርክ ነህ መንጃ ፈቃዱ አይከብድህም" የሚል አጓጊ ጥሪ እንዳቀረበለት ሰለሞን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። የሰለሞን ወዳጅ ሥራ አጥነት በብርቱ ለፈተነው ወጣት ግብዣ በማቅረብ ብቻ ግን አልተወሰነም። ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሚጓዝበት 20,000 ብር ጭምር ልኮለታል። በዚያ ገንዘብ ሰለሞን ወደ ሳዑዲ የሚወስደውን የመጓጓዣ ትኬት ቆረጠ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ተስፋ ወደሰነቀበት ምድር በረረ። በዚያ በረራ "እዚያ ሔጄ እውነት ሥራ አገኝ ይሆን ወይ? ከቤተሰቦቼ ተነጥዬ በሕይወት እመለሳለሁ ወይ?" የሚሉ ጥያቄዎች ሽው ብለውበት ነበር። የሰለሞን ደመ-ነፍስ የጠረጠረው አንዳች ነገር ነበር።
አብደላ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ቤተሰቦቹን የመደገፍ የተጨናገፈ ህልሙን አልዘነጋም። ሥራ ሞከረ-አልተሳካም። በ2008 በሰዎች አሸጋጋሪዎች አማካኝነት ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ተጉዞ ከኤደን ባህረ ሰላጤ ዳርቻ በምትገኘው ቦሳሶ በኩል እንደገና ወደ የመን ተመመ። ጉዞው በየመን አልቆመም ሳዑዲ አረቢያ ገባ።
"አንድ አመት ከግማሽ ሰራሁ። ያ ጊዜ ይሻል ነበረ። የድርጅት ሥራ ነበረ። የብሎኬት ፋብሪካ ነበረ። ዶዘር ነበር የምሰራው። አንድ የመናዊ ዶዘሩን አለማመደኝ። ከዚያ በሱ ስራ አሸዋ ማቅረብ ጀመርኩ። እዚያ አመት ከምናምን ሰራሁ" የሚለው አብደላ አሁንም ድጋሚ በጸጥታ ኃይሎች እጅ ወደቀ። ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተጠረነፈ።
አብደላ ወደ ትውልድ አገሩ ሲመለስ የሚያቆየው ነገር አላገኘም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ግም ሲል የእሱ እግር ዳግም የቦሳሶን ምድር ረገጠ። "ባህር ላይ የምንቆየው ለ36 ሰዓታት ነበረ። ጀልባው ላይ 200 ሰዎች ነበርን" ይላል አብደላ ስለሶስተኛው ጉዞ ሲያስረዳ። ለሰዎች አዘዋዋሪዎች 10, 000 ሪያል ከፍሎ ከቦሳሶ የመን 36 ሰዓታት የወሰደው ጉዞ ግን እንደከዚህ ቀደሙ አልነበረም።"ጀልባው ሳይገለበጥ በሙቀት ምክንያት አራት ሰው ነው የሞተው። ሶስቱን ውኃ ላይ ወረወሩት። አንዱን እዚያው ላይ ሸፋፍነን አስቀረነው። ስንወጣ ከየመኖቹ ጋር ተባብረን ቀበርንው" በማለት ከሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠበትን ሁኔታ አስረድቷል። "ስንሞት ምንም ዋጋ እንደሌለን" አብደላ የተረዳው አስከሬን ወደ ባህር "ሲወረወር" ከተመለከተ በኋላ ነው። "መጀመሪያ ምንም አልመሰለኝም ነበረ። ትልቅ ሐዘን የተሰማኝ በዚያን ጊዜ ነበር" ይላል አብደላ።
ይኸ ስሜት አብረውት መንገድ ከገቡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ዘንድ እንደነበር አብደላ ያስታውሳል። በመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ መካከል የተንሰራፋውን ባህር በድንጋጤ እና በሥጋት የተሻገረ እግራቸው ግን ወደ ኋላ አልተመለሰም። የርስ በርስ ጦርነት ያመሳቀላትን የመን አቋርጠው የሳዑዲ አረቢያን ድንበር ለመሻገር ሲሞክሩ ከድንበር ጠባቂዎች ጋር ተፋጠጡ። የሳዑዲ አረቢያ ጸጥታ አስከባሪዎች ባህር እና በርሐ አቋርጠው ከየመን የሚገሰግሱትን ኢትዮጵያውያን የተቀበሏቸው የጦር መሣሪያዎቻቸው በሚተፉት ጥይት ሆነ። አብደላ እግሩ ላይ በጥይት ተመታ።
"ወላሒ ያን ጊዜ ምን እንደተሰማኝ አላወኩም። በድንጋጤ ወደ ሶስት እና አራት ሰዓት አካባቢ [ራሴን አላውቅም ነበር።] ሰዉ እሱንም እኔንም ጥሎ ሔዷል። ስነሳ ማንም ሰው አጠገባችን አልነበረም። ስነቃ ደላላው ሞቷል፤ እኔ አለሁ-በቃ" ይላል ወጣቱ።
አብደላ በድንበር ጠባቂዎች በጥይት የተመታበት ቦታ ደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ ከሰሜን ምዕራብ የመን በሚጎራበትበት አካባቢ እንደሚገኝ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያውያን ስደትን በተመለከተ ያጠናቀረው ሪፖርት ይጠቁማል። በአካባቢው ሶቁ አል-ራጉ እና ኢዝላት አል ታቢት የተባሉ የየመን ገጠራማ መንደሮች ይገኛሉ። ለሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ቅርብ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን ሶቁ አል-ራጉ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች እና መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች የሚያዘወትሯት "አደገኛ ከተማ" ሲሉ ይጠሯታል። የሳዑዲ አረቢያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚሉት የድንበር ጠባቂዎች ጥብቅ ቁጥጥር ከሚያደርጉባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ይኸው በኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚዘወተር የጉዞ መስመር ነው። በድንበር ጠባቂዎች ጥይት እግሩን ተመቶ ራሱን የሳተው አብደላ ሲነቃ ወደ ኋላ ተመለሰ። እርሱ ራጉ ብሎ ወደሚጠራው ቦታ።
እስር ቤት...ሌላ ፈተና
"ወደ ኋላ ተመልሼ ትንሽ ቀን ቆየሁ። በአስራ አምስተኛው ቀን [ሳዑዲ አረቢያ] ገባን" የሚለው አብደላ መካ ለመድረስ 3500 ሪያል እርሱ ደላላ እያለ ለሚጠራቸው የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍሏል። ወደ "መዲና መስመር" መጓዙን የገለጸው ወጣት ወደ እርሻ ሥራ ገባ። "ማንጎ፣ አቮካዶ ምናንምን ነበር የምንሰራው" ይላል። አንድ አመት ገደማ ከሰራ በኋላ ግን ለሶስተኛ ጊዜ ከጸጥታ አስከባሪዎች እጅ ወደቀ። በቁጥጥር ሥር የዋለው በሥራ ላይ እያለ ነበር። "ስልክ ነበረ፤ ብር ነበር። ያ ሁሉ ተወሰደ። እንደ ድሮው መስሎን ነበረ። ብራችን ይመለሳል ብለን ነበር። አልተመለሰም" የሚለው ወጣት እስር ቤት ገባ።
ይኸ ሰለሞንም አልቀረለትም። ሰለሞን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አሁንም ድረስ በትክክል ከማያውቀው የሳዑዲ አረቢያ ከተማ ሲደርስ የሚቀበለው አልነበረም። አረብኛ ቋንቋ መናገር አይችልም።
ሰለሞን "በቀጥታ ለልጁ ስደውልለት አድራሻው ጠፋ። ምንም ቋንቋ አላውቅም። ኬላዎቹ አነጋገሩኝ። አረብኛ ነው የሚያወሩት። ምንም የማውቀው የለም። አካባቢውንም አላውቅም። ለአገሩም አዲስ ነኝ። በጣም ነው ግራ የገባኝ። ወዲያው አፍነው ነው የወሰዱኝ" በማለት የገጠመውን ይናገራል።
ከአዲስ አበባ በአውሮፕላን ተጉዞ ሳዑዲ አረቢያ የደረሰው ሰለሞን እስር ቤት ገባ። ለ20 ገደማ ወራት የኖረበት እስር ቤት። በዚያ ያገሩን ልጆች አገኛቸው። "በጣም የተጨናነቀ፤ ሐበሻ የሞላበት የተለያዩ አገሮች ዜጎችም ያሉበት ነበር። ምግብ እንደ ፈለክ አታገኝም። ስትታመም መታከም አትችልም። የተላላበ ነው። በጣም ነጻነት የሌለበት ነው" በማለት እስር ቤቱን ይገልጸዋል።
በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የታጎሩ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ኢ-ሰብዓዊ እንደነበር ሒውማን ራይትስ ዎች በተደጋጋሚ ባወጣቸው ዘገባዎች አጋልጧል። ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ጭምር በአገሪቱ ጸጥታ አስከባሪዎች እየተያዙ ወደ ተጨናነቁ እስር ቤቶች ተወርውረዋል። በጂዳ በሚገኘው ሹሜሲ የተባለ ማቆያ ታስረው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዲት ሕጻንን ጨምሮ አስር ሰዎች መሞታቸውን በጅዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በነሐሴ 2013 አስታውቆ ነበር። ይኸ በማጎሪያዎች የሚከሰትን ሞት አብደላም ታዝቧል። የእስር ቤቱ ሁኔታ ራሱንም ተስፋ አስቆርጦት ነበር።
"ወጥቼ ሰው እሆናለሁ ብዬ የማስበው ነገር አልነበረኝም" የሚለው አብደላ "ምግብ እንኳ የለም ነበር። አንዲት ቁርስ ነበር የምንበላው። [የሚሰጠን] ሩዝ አንድ ጊዜ ለመጉረስ እንኳ አይበቃም ነበር። ብር ከውጪ ስናስገባ ዘበኛው ከአንድ ሺሕ ሪያል 200 ይቆርጥብን ነበር። ኤምባሲዎቹ ድረሱልን አምጡልን ስንል በአንድ ወር ውስጥ 500 [ሪያል] ያመጣሉ። እሷ ደግሞ በአንድ ክፍል ውስጥ ለሁለት ሰው ብቻ ነበር የምትደርሰው። አንድ ክፍል ውስጥ የነበረው 200 ሰው ነው። ለማን ይድረሰው?" የሚለው አብደላ በእስር ቤት 13 ወራት ቆይቷል።
ሰለሞን በለጠ ከ20 ገደማ ወራት እስር በኋላ አብደላ ከ13 ወራት እስር በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ሰለሞን ግን ብርቱ የጤና ዕክል ገጥሞታል። "ሰውነቴ በጣም የመንቀጥቀጥ ባህሪ አለው። ሚዛኔን መጠበቅ አልችልም። እንቅልፍ ፍጹም የለኝም። አዕምሮዬን ያመኛል" የሚለው ሰለሞን የጤና ሁኔታውን "በጣም ከባድ" በማለት ይገልጸዋል።
ሰለሞን ከትውልድ ቀዬው ከገባ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት የጤና መድን ዋስትና መርሐ-ግብር በወልድያ ሆስፒታል ሕክምና በመከታተል ላይ ይገኛል። ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ያሳለፈውን መርሳት አልቻለም፤ እግሩን ለስደት ያነሳበት ውሳኔም ያንገበግበዋል። አብደላም ከአባቱ ቤት ነው። ሳዑዲ አረቢያ ለመመላለስ ወደ 380 ሺሕ ብር ገደማ እንዳወጣ ለዶይቼ ቬለ የተናገረው የ31 አመቱ ወጣት ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አያውቀውም። በአንድ ነገር ግን እርግጠኛነው። ለጸሎት ካልሆነ በቀር ከእንግዲህ ፊቱን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደማያዞር።
ከመጋቢት 21 እስከ ግንቦት 29 ቀን ድረስ 33 ሺሕ 336 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ተመልሰዋል። ከሰባት እስከ አስራ አንድ ባሉ ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት 100 ሺሕ ገደማ ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ የመመለስ ዕቅድ አለው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎቹን ለመመለስ አዲስ ብሔራዊ ኮሚቴ ያቋቋመው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሰብሳቢነት የሚመሩት ኮሚቴ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት፣ የፍትኅ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎትን ጨምሮ 16 ተቋማት የተካተቱበት ነው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ዜጎቿን ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለመመለስ ተመሳሳይ ኮሚቴዎች አቋቁማ ታውቃለች።
የድምጽ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ