ኮኖናና የቻይና ኤኮኖሚ
ሰኞ፣ ግንቦት 17 2012የቻይና መንግሥት ኤኮኖሚውን የሚያነቃቁ ርምጃዎችን ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ነው። ኮሮና ወረርሽኝ የቻይና ምርት ቀጥታ ለገበያ የሚቀርብባቸው የዩናይትድ ስቴትስና አውሮጳ ኤኮኖሚ በማዳከሙ ምክንያት የቻይናን የሀገር ውስጥ ምርትና ፍላጎት ክፉኛ ጎድቶታል። በወረርሽኙ ምክንያትም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ሥራቸውን አጥተዋል። ቲያን ሻኑዋ ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ ቤጂንግ ሲመጣ ወዲያው ነበር ሥራ ያገኘው። ሆኖም ወረርሽኑ በሀገሪቱ በተከሰተ ጊዜ ማተሚያ ቤት ውስጥ አግኝቶት ከነበረው ሥራ ተፈናቀለ።
«እውነት ለመናገር ራሴን እንኳ በሕይወት ለማቆየት ብችል ደስ ይለኛል። ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ሁለት ቦታ ነበር የምሥራው አሁን ግን አንዱንም አጣሁ። ኑሮዬን የምገፋው በርሃብ ነው።»
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይታይ የነበረው የቻይና ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት ዛሬ ላይ ተገትቷል። ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸርም በዚህ በዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወር ላይ በሰባት በመቶ መቀነሱ ተመዝግቧል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት ይህ በአስር ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ለውጥ ነው። አሁን የቻይና መንግሥት የሀገሪቱ የተዳከመ ኤኮኖሚ እንዲያንሰራራ የሚረዱ ርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል። የወለድ መጠን በመቀነስ፣ የግብር ክፍያን በማቋረጥ እንዲሁም ድጎማ እያደረገ ቢሆንም ሌሎች ተጨማሪ ርምጃዎች እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ቤጂንግ የሚገኘው ሩሺ የፋይናንስ ተቋም ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያ ዙ ቻንሺ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት የተካሄደው የቻይና ብሔራዊ የህዝቦች ምክር ቤት ጉባኤ የኮሮና ወረርሽኝ ያሽመደመደውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ የሚያነቃቃበት አዲስ ስልት ይዞ እንደሚመጣ አስቀድመው ገምተዋል።
«ምክር ቤቱ ጎልተው የሚወጡ ተጨማሪ የማነቃቂያ ርምጃዎችን ለመውሰድ ይወስናል ብዬ አስባለሁ። ርምጃዎቹም ለየት ያለ የመንግሥት ብድሮች እንዲሁም የተለዩ ቦንዶችን የሚያካትቱ ይሆናሉ።»
ከምክር ቤቱ ጉባኤ በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም የኤኮኖሚ ባለሙያው ግምት እውነትነት አለው። የቻይና መንግሥት በዚህ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ትኩረቱን ጠቅላላ የሀገሪቱ ዓመታዊ ገቢ ላይ ማድረጉን ወደጎን አድርጎ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ፣ በሀገሪቱም ያለውን የድህነት መጠን ይቀንሳሉ ያላቸውን ዕቅዶች ለመተግበር ተስማምቷል። በዚህም መሠት ከዘጠኝ ሚሊየን የሚበልጡ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር፣ በአሁኑ ወቅት በቻይና ገጠር ውስጥ ያለውን ኑሮ በሀገሪቱም ሆነ በሌሎች ደሀ ሃገራት ከሚታየው የድህነት ጠገግ ማውጣት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ኮሮና ተሐዋሲ በኤኮኖሚው ላይ የፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ባለፈው ዓመት በዓመታዊ በጀቱ ላይ የታየውን ክፍተት በአንድ ትሪሊየን የን ማለትም 143 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ከፍ ለማድረግ ወስኗል። ይህ ደግሞ የኤኮኖሚ ባለሙያው እንደጠቆሙት የግብር ቅነሳን፣ የንግድ ተቋማት ኪራይና ክፍያዎችን በመቀነስ ፤ ፍጆታው ና መዋዕለ ንዋይ ፍሰቱ በቀጣይ ወራት እንዲጠናከር ማድረግን ያጠቃልላል። እስከመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በርካታ ሃገራት የኤኮኖሚ ክስረት እንደሚያጋጥባቸው በሚጠብቁበት በዚህ ወቅት የቻይና መሪዎች ግን የሀገራቸው ኤኮኖሚ ዘንድሮ መጠነኛ ዕድገት ከማሳየት ባለፈ ኮሮና ካሳረፈበት ተፅዕኖ ፈጥኖ ይወጣል የሚል አዎንታዊ ግምት ይዘዋል።
ሸዋዬ ለገሠ /ሃርማን አንዲ
ነጋሽ መሐመድ