የአዲስ አበባና የመቀሌ ፖለቲከኞች ጣጣ
ሰኞ፣ የካቲት 23 2012ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ለዛሬዉ ዉይይት የኢትዮጵዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትና የትግራይ መስተዳድር ግንኙነት የሚል ርዕሥ ሰጥተነዋል።ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ይመራዋል የሚባለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕደዴድ) መራሽ መንግስት ከተቀየረ ከመጋቢት 2010 ወዲሕ በአዲስ አበባና በመቀሌ ፖለቲከኞች መካከል ያለዉ ልዩነት እየተካረረ፣የቃላት እንኪሰላንቲያዉ እየተጠናከረ መጥቶ የእስከ ቅርብ ጊዜዉ ገዢ ፓርቲ የኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና ፓርቲ እስከማስቀየር፣የግንባሩ መስራች ሕወሓትን ከግንባሩ እስከ ማስወጣት ደርሷል።ሕወሓት ርዕሠ-መንበሩን አዲስ አበባ ያደረገዉን አዲሱን የብልፅግና ፓርቲን ለመፎካከር በሚመስል መንገድ «ሐገርን ለማዳን ይታገላል» ያለዉን «የሕብረ ብሔር ፌደራሊስቶች» የተባለ የ40 ፓርቲዎች ጥምረት መቀሌ ላይ መስርቷል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ባንፃሩ በፌደራሉ መንግሥትና በአዲስ አበባ መስተዳድር ሥልጣን ላይ የነበሩ የሕወሓት ሹማምንታትን ሽሯል።ጠቅላይ ሚንስትሩ በየአጋጣሚዉ ሕወሓትንና ባለስልጣናቱን በተደጋጋሚ በቃላት ይሸነቁጣሉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኤርትራዉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የመሰረቱት «ወዳጅነትም» የመቀሌ ፖለቲከኞችን ሲበዛ እያስከፋ ነዉ።ከጥቂት ወራት በፊት «ሐገርን ለማዳን ይታገላል» የተባለ ጥምረት የተመሠረተባት መቀሌ፣ ባለፈዉ ሳምንት የሕወሓት 45ኛ ዓመት በዓል ሲከበርባት ደግሞ ወታደራዊ የሚመስል ትርዒት፣የሰልፈኞች ፉከራና ቀረርቶ በተለይ የፓርቲዉ ሊቀመንበር ነፃነት የሚያዉጅ የሚመስል መልዕክት ተሰምቶባታል።«ሐገር የማዳን» ና የነፃነቱ ማስፈራሪያ የፈጠረዉ ተቃርኖ በብዙዎች ዘንድ ሕወሓት ትግራይን ወዴት እየገፋት ነዉ? ድፍን ኢትዮጵያስ ወዴት እየሔደች ነዉ የሚል ጥያቄ አጭሯል።በዛሬዉ ዉይይታችን ለጥያቄዉ መልስ ለመሻት እንሞክራለን።
ነጋሽ መሐመድ