ዓለም ዓቀፍ ስፖርት
ሰኞ፣ ጥር 28 2004
የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሰንበቱን ወደ ግማቭ ፍጻሜው ቭግግር አድርጓል። ይሄው ትናንትና ከትናንት በስቲያ የተካሄደው ሩብ ፍጻሜ ዙር ግን የሚያሳዝን ሆኖ ለአስተናጋጆቹ ሃገራት ለኤኩዋቶሪያል ጊኒና ለጋቡን የስንብትም ነው የሆነው። ባለፈው ቅዳሜ ተካሂደው በነበሩት ሁለት ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች አይቮሪ ኮስት ኤኩዋቶሪያል ጊኒን 3-0 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ ዛምቢያም በተመሳሳይ ውጤት ሱዳንን ከውድድሩ አስወጥታለች።
ለአይቮሪ ኮስት የቼልሲው ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ሁለቱን ጎሎች ሲያስቆጥር ሶሥተኛዋን በግሩም ቅጣት ምት ያስገባው ደግሞ በዚያው በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሚጫወተው የማንቼስተር ሢቲይ አጥቂ ያያ ቱሬ ነበር። ለድሮግባ በተለይ ፍጹም ቅጣት ምት ከሳተ በኋላ ድሉ መገኘቱ ትልቅ ዕፎይታ ነው የሆነው። ድንቁ ተጫዋች ለዚህም ባልደረቦቹን ሳያወድስ አላለፈም።
<ጎሏን ከሳትኩ በኋላ ጓደኞቼ ስላበረታቱኝ በጣም ነው የማመሰግነው። ዛሬ ማሸነፋችን በጣም ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። አንድ፣ ሁለት ወይም ሶሥት ጎል ማስገባት ያን ያህል ትልቅ ነገር አይደለም። ግን ትልቁ ነገር ከአስተናጋጇ አገር ተጫውቶ ማሸነፉ ነው። እነሱ ቀዳሚ ግጥሚያዎቻቸውን ስላሸነፉ በሙሉ ልብ ነበር ሜዳ የግቡት። እናም በጥቅሉ በኔ ጎሎች ብቻ ሣይሆን በማለፋችን ደስ ብሎኛል>
በዕለቱ ሁለተኛ ግጥሚያ ደግሞ ዛምቢያ ሱዳንን በፍጹም የበላይነት እንዲሁ 3-0 ረትታለች። ጎሎቹን ክሪስቶፍ ካቶንጋና ጀምስ ቻማንጋ ሲያስቆጥሩ ከሁሉም አሳዛኙ ነገር የባታው ስቶፒላ ሱንዙ ስታዲዮም ባዶ ሆኖ መታየቱ ነበር። የዛምቢያው ፈረንሣዊ አሠልጣኝ ሄርቭ ሬናርድ ጨዋታው ከባድ ይሆናል ብሎ ፈርቶ እንደነበር ነው በመጨረሻ የተናገረው።
በትናንቱ ቀሪ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ደግሞ ጋናና ማሊ ወደ ቀጣዩ ዙር መሻገሩ ሰምሮላቸዋል። የጋና ብሄራዊ ቡድን ቱኒዚያን 2-1 ሲያሸንፍ ማሊ ደግሞ ጋቡንን ከሰዓት ጭማሪ በሁዋላ በፍጹም ቅጣት ምት 5-4 ረትታለች። ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ መልሳ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን የተነሳችው ጋናም ለድል የበቃችው በተጨማሪ ሰዓት ውስጥ ወሣኝ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ነው።
ቱኒዚያ በአንጻሩ በረኛዋ አይመን ማትሉቲ ብ 101 ኛዋ ደቂቃ ላይ በሰራት ስህተት ከውድድሩ ስትውጣ የቡድኑ ደጋፊዎች መሪር ሃዘን ላይ ነው የወደቁት። ግማሽ ፍጻሜው ግጥሚያዎች በዚህ ሣምንት አጋማሽ የሚካሄዱ ሲሆን ዛምቢያ ከጋና ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ባታ ላይ፤ እንዲሁም ማሊ ከአይቮሪ ኮስት ጋቡን ሊበርቪል ውስጥ ይገናኛሉ። ከኂያም ለሶሥተኝነት የሚደረገው ጨዋታ በፊታችን ቅዳሜ ከተጠናቀቀ በኋላ የፍጻሜው ግጥሚያ በማግስቱ ዕሑድ ይካሄዳል። ታዛቢዎች በወቅቱ የሚተነብዩት ምናልባት ጋና ወይም አይቮሪ ኮስት የዋንጫ ባለቤት እንደሚሆኑ ነው።
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያዊው አትሌት ደረጀ አሊ ትናንት ሆንግ ኮንግ ላይ ተካሂዶ የነበረው ዓለምአቀፍ የማራቶን ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። በ 16ኛው የሆንግ ኮንግ ማራቶን ስባ ሺህ ሰዎች ሲሳትፉ በሴቶችም ድሉ የአትዮጵያ ነበር። ምስክር ደምሴ አሸንፋለች። በዚሁ ሩጫ ያሳዝናል አንድ የ 26 ዓመት ተሳታፊ መግቢያ መስመሩ ላይ ከደረሰ በኋላ ራሱን ስቶ ወድቆ በመጨርሻ ሆስፒታል ውስጥ ሞቷል።
በጃፓን የቤፑ-ኦኢታ ማራቶን ደግሞ በዚያው ነዋሪ የሆነው ኬንያዊ አትሌት ሀሩን ኞሮጌ የራሱን ጊዜ ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል አሸናፊ ሆኗል። የሞንጎሊያው ኦቺር ሁለተኛ ሲወጣ ኢትዮጵያዊው ያዕቆብ ጃርሶ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።
በአሜሪካ የቦስተን የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ደግሞ የግሬናዳው የዓለም ሻምፒዮን ኪራኒ ጀምስ የዓመቱን ፈጣን የ 400 ጊዜ ሊያስመኀግብ በቅቷል። በወንዶች 3000 ሜትር የኬንያው ካሌብ እንዲኩ ሲያሸንፍ ደጀን ገ/መስቅል ሁለተኛ ወጥቷል። ከቦስተኑ ባለድሎች መካከል የኢትዮጵያ ድንቅ ሴት አትሌቶችም ይገኙበታል። በ 3000 ሜትር የዓለም ክብረ-ወስን ባለቤት መሠረት ደፋር በፍጹም የበላይነት ስታሸንፍ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በሁለት ማይል አንደኛ ሆናለች።
ቡንደስሊጋ/አውሮፓ
በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድር የስፓኙ ሬያል ማድሪድና የእንግሊዙ ማንቼስተር ሢቲይ እንደመሩ ሲቀጥሉ በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ አንደኝነቱን ተነጥቋል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያል ማድሪድ ሴርጆ ራሞስ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ጌታፌን በማሸነፍ በአመራሩ ሲቀጥል በሁለተኝነት የሚከተለው ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ ሬያል ሶሢየዳድን 2-1 ረትቷል። ሬያል ክ 21 ግጥሚያዎች በኋላ በ 55 ነጥቦች ቀደምቱ ሲሆን ባርሣ ሰባት ነጥቦች ወረድ ብሎ ይከተላል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ፉልሃምን 3-0 በመርታት አመራሩን በሁለት ነጥቦች ከፍ አድርጓል። ለዚሁም ምክንያት የሆነው በነጥብ አቻው የነበረው ማንቼስተር ዩናይትድ ከቼልሢይ በእኩል ለእኩል 3-3 በመውስኑ ነው። ከሰንበቱ 24ኛ ግጥሚያ ብኋላ ቶተንሃም ሶሥተኛ ሲሆን ቼልሢይ ደግሞ በአረተኝነት ይከተላል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ሰንበቱ ከዶርትሙንድ በስተቀር ቀድምቱ ክለቦች በሙሉ በእኩል ለእኩል ውጤት የተወሰኑበት ነበር። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ኑርንበርግን 2-0 ሲያሸንፍ በዚሁም ባየርን ሙንሺንን ከአመራሩ ሊፈነቅል ብቅቷል። ባየርን በበኩሉ ግጥሚያ ከሃምቡርግ ክ 1-1 ውጤት ሊያልፍ አልቻለም።
ተከታዮቹ ሻልክ፣ ግላድባህና ብሬመንም በእኩል ለእኩል ውጤት ሲወሰኑ ባሉበት ነው ቆመው የቀሩት። ሻምፒዮናው በመጀመሪያዎቹ አራት ክለቦች መካከል ያለው የአራት ነጥብ ልዩነት ብቻ በመሆኑ ማራኪ እንደሆነ ይቀጥላል። የትናንቱን ውጤት ምናልባት አምሥተኛው ብሬመን ከአመራሩ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ሊጠቀምበት በቻለ ነበር። ግን ሳይሆንለት ቀርቷል። እርግጥ ይህ ደግሞ ሁለት ግቦች ያስቆጠረውን ጎል አግቢ ክላውዲዮ ፒሣሮን ማስቆጣቱ አልቀረም።
<በጣም ነው የተናደድኩት። እንዲህ ዓይነቱን ጨዋታ እርግጠኛ ሆነን ማሸነፍ ነበረብን።ሁለት ጊዜ ከመራን በኋላ ውጤቱን ለመጠበቅ አለመቻላችን በጣም ነው የሚያሳዝነው>
በተቀረ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤሢ ሚላንና ጁቬንቱስ በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰን ቀደምት እንደሆኑ ሲቀጥሉ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን አመራሩን በሶሥት ነጥቦች አስፍቷል። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ቀደምቱ ሲሆን በግሪክ ሊጋ ደግሞ ኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ ይመራል።
ቴኒስ
ባለፈው ሰንበት በተካሄዱት ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፌደሬሺን-ካፕ የመጀመሪያ ዙር የቡድን ግጥሚያዎች ዩኤስ አሜሪካ ቤላሩስን 5-0 ስትረታ ሩሢያ ከስፓኝ 3-2፤ ኢጣሊያ ከኡክራኒያ 3-2፤ ቼክ ሬፑብሊክ ከጀርመን 4-1፤ እንዲሁም ሰርቢያ ከቤልጂግ 3-2 ተለያይተዋል። በተረፈ በሞንትፔሊዬር በተካሄደ ሱድ-ዴ-ፍራንስ-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚዛ አገሬው ተጫዋች ዢል ሞንፊልስ የቼክ ተጋጣሚውን ቶማስ ቡርዲችን 2-1 አሸንፏል። በቡጢ ለማጠቃለል የኩባው ሁዋን-ፓብሎ-ሄርናንዴስ የቀድሞውን ክሩስ ሻምፒዮን ስቲቭ ከኒንግሃምን በዳኞች አንድ ወጥ ብያኔ በማሸነፍ የዓለምአቀፍ ቡጢ ፌደሬሺን ሻምፒዮንነቱን አስከብሯል።
መሥፍን መኮንን
ተክሌ የኋላ