1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ ስፖርት

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2005

ባለፈው ሣምንት ቀደምት የአጭር ርቀት ሯጮች የተከለከሉ አካል አጎልባች መድሃኒቶችን በመውሰድ መጋለጣቸው ዓለምአቀፉን ስፖርት ዝና እንደገና ማጉደፉ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/1980o
ምስል picture-alliance/dpa

በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በአንድ መቶ ሜትር ሩጫ ግሩም ጊዜ በማስመዝገብ ሲያሸንፍ የቆየው የአሜሪካ አትሌት ታይሰን ጌይ እስከ ትናንት ድረስ ምናልባትም የዓለም ሻምፒዮኑን ዩሤይን ቦልትን ሊያስንቅ ይችላል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም በዚህ ዓመት ሶሥቱን የ 100 ሜትር ፈጣን ጊዜ አስመዝግቦ የነበረው ጌይ በፊታችን ወር ሞስኮ ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመሳተፍ ዕድል አይኖረውም።

ታይሰን ጌይ ብቻ አይደለም፤ የአንዴው የመቶ ሜትር የክብረ-ወሰን ባለቤት አሳፋ ፓውልና በዚሁ ርቀት የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረችው ሼሮን ሲምሰንም የተከለከለ መድሃኒት መውሰዳቸው የተደረሰበት መሆኑ ታውቋል። ሁለቱ የጃሜይካ አትሌቶች በወቅቱ ምንም እንኳ እንደማያውቁ ሆነው ጉዳዩን ሊያስተባብሉ ቢሞክሩም የምርመራው ውጤት ፈሩን የሳተ አይመስልም። ጃሜይካን ካነሣን የደሴቲቱ ታዋቂ ሴት አትሌት ቬሮኒካ-ካምፕቤል-ብራውምን በዚሁ ዶፒንግ የተነሣ ባለፈው ወር በብሄራዊው የአትሌቲክስ ፌደሬሺን መታገዷ የሚታወስ ነው።

የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር እንዳስታወቀው ደግሞ ቁጥራቸው እስከ 30 የሚደርስ የቱርክ አትሌቶችም የተከለከለ አካል አጎልባች መድሃኒት በመውሰድ ድርጊት የመታገድ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። በተቀረ በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አትሌቶች በተመሳሳይ ድርጊት በየጊዜው መጋለጣቸው አይዘነጋም።

Asafa Powell und Nesta Carter
ምስል picture alliance / AP Photo

በስፖርቱ ላይ እናተኩርና ባለፈው ቅዳሜ ማድሪድ ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በ 100 ሜትር የጃሜይካው ኔስታ ካርተር ሁለት አሜሪካውያንን ከኋላው በማስቀረት ለማሸነፍ በቅቷል። መቶ ሜትሩን ለማቋረጥ የፈጀበት ጊዜ 9,87 ሤኮንድ ነበር። ይህም ግሩም ጊዜ ነው። በ 400 ሜትር የባሃማሱ ራሞን ሚለር ሲያሸንፍ በ 800 ሜትር ደግሞ ድሉ የአሜሪካዊው አትሌት የብራንደን ጆንሰን ሆኗል። በ 3000 ሜትር ሩጫ ኬንያውያኑ ሣይረስ ሩቶና ጊዴዮን ጋቲምባ በመከታተል ቀደምቱ ነበሩ።

በርዝመት ዝላይ የኩባው ዊልፍሬዶ ማርቲኔዝ አንደኛ ሲወጣ በአሎሎ ውርወራ የቡልጋሪያው ጌኦርጊ ኢቫኖቭ፤ እንዲሁም በዲስክ ውርወራ የስፓኙ ፍራንክ ካዛናስ አሸናፊዎች ሆነዋል። በሴቶች በተለይ የአሜሪካ አትሌቶች አይለው ሲታዩ በ 100፣ በ 800 እና በ 1,500 ሜትር እንዲሁም በከፍታ ዝላይ ቀደምቶቹ ነበሩ። በጦር ውርወራ ጀርመናዊቱ ሊንዳ ሽታል አሸናፊ ሆናለች።

Dawit Beshah
ምስል Fotobiniam

ለመጪው 2014 ኦሬንጅ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ለመድረስ በተጀመረው ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ላይ ባካሄደው የማጣሪያ ግጥሚያ ሩዋንዳን 1-0 ረትቷል። የጨዋታውን ብቸኛ ጎል በ 57ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አስራት መገርሣ ነበር። በሌላ በኩል ያለፈው ውድድር ሻምፒዮን ቱኒዚያ በመጀመሪያው ማጣሪያ ዙር በሞሮኮ ተሸንፋ ከወዲሁ ስንብት ማድረግ ተገዳለች። የቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ከውድድሩ የወጣው በመጀመሪያ በአገሩ 1-0 ከተረታ በኋላ ሞሮኮ ውስጥ ታንጀር ላይ በመልሱ ጨዋታ 0-0 ከተለያየ በኋላ ነው።

16 ሃገራት የሚሳተፉበት ውድድር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሊካሄድ የታቀደው በፊታችን 2014 ዓ-ም የመጀመሪያ ወራት ነው። ደቡብ አፍሪቃ እንደ አስተናጋጅ አገር ለውድድሩ በቀጥታ ስታልፍ ጋናና ሊቢያ ቤኒንና አልጄሪያ ከተሰናበቱ በኋላ ተካፋይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ኡጋንዳም ታንዛኒያን በውጭ 1-0 ረትታ ስትመለስ መልካም የማለፍ ዕድል ነው ያላት።

ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው ከሃያ ዓመት ዕድሜ በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ በፈረንሣይ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ፈረንሣይ በፍጻሜ ግጥሚያው ኡሩጉዋይን 4-1 ስትረታ ብርቱ ትግል የታየበት ጨዋታ በመደበኛና በተጨማሪ ጊዜ 0-0 በማብቃቱ የለየለት በፍጹም ቅጣት ምት ነው። ፈረንሣይ ለፍጻሜ የደረሰችው ቱርክን፣ ኡዝቤኪስታንንና ጋናን አሸንፋ በማለፍ ነበር። የአፍሪቃ ተጠሪ ጋና ለሶሥተኝነት በተደረገ ግጥሚያ ኢራቅን 3-0 ረትታለች።

ከሃያ ዓመት በታቹ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለቱርክ ታላቅ የስፖርት ትዕይንት የማስተናገድ ብቃት መለኪያ ሆኖ መታየቱም አልቀረም። ኢስታምቡል ከማድሪድና ከቶኪዮ ጎን የ 2020 ዓ-ምን ኦሎምፒክ ለማስተናገድ በዕጩነት የቀረበች ሲሆን በጉዳዩ ውሣኔ የሚሰጠው በመጪው መስከረም ውስጥ ነው። የፊፋ ተወካይ ውድድሩ ብዙ ተመልካችን ባለመሳቡ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይሄው የኢስታምቡልን ለኦሎምፒክ አዘጋጅነት የመመረጥ ዕድል ገደብ ሳያደርገው የሚቀር አይመስልም።

በውድድሩ በጠቅላላው 50 ግጥሚያዎች ሲካሄዱ በአማካይ በአንድ ጨወታ ላይ የተገኘው ተመልካች ቁጥር 5,200 ገደማ የሚጠጋ ነበር። ይህም እስካሁን ከነበረው ሁሉ ዝቅተኛው መሆኑ ነው። ከዚህ ሌላ የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች አዲስ የውድድር ወቅት ሊከፈት እየተቃረበ ሳለ በየቦታው በአዳዲስ ተጫዋቾች ለመጠናከር የሚደረገው ጥረት ባለበት ቀጥሏል።

Deutschland Fußball Trainer Pep Guardiola vom FC Bayern München
ምስል picture-alliance/dpa

ያለፈው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤት የጀርመኑ ክለብ ባየርን ሙንሺን የባርሤሎናን ወጣት ኮከብ ቲያጎ አልካንታራን በ 36 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱን ትናንት ይፋ አድርጓል። ቲያጎ የተገዛው በቀድሞው የባርሣ፤ በአሁኑ የባየርን አሠልጣኝ በፔፕ ጉዋርዲዮላ ታላቅ ፍላጎት ሲሆን ጉዳዩ በፔፕና በቀድሞ ክለቡ መካከል ውዝግብን እስከማስከተል ደርሶም ነበር። ይሁንና በመጨረሻ የቃላት ጦርነቱ አብቅቷል።

የ 22 ዓመቱ ቲያጎ ከባርሣ የወጣት አካዳሚ የመነጨ ሲሆን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሻቪን እንደሚተካ ሲነገርለት ነበር የቆየው። ቲያጎ ባለፈው ወር ከ 21 ዓመት በታች ወጣቶች ሻምፒዮና ስፓኝ ኢጣሊያን 4-2 ስታሸንፍ ሶሥቱን ጎሎች በማስቆጠር በፊፋ የውድድሩ ድንቅ ተጫዋች ተብሎ መሰየሙ አይዘነጋም። ቲያጎ አልካንታራ ኢጣሊያ-ባሪ ውስጥ ሲወለድ የብራዚሉ የ1994 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ቡድን የመሃል ሜዳ ተጫዋች የማዚኞ ልጅ ነው። ጥበቡን ጥሩ አድርጎ ወርሷል ለማለት ይቻላል።

ከባየርን ሌላ ቀደምቱ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ክለብ ማንቼስተር ሢቲይም ተሰናባቹን የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ካርሎስ ቴቬዝን የሚተካ አጥቂ ለመተካት በመሯሯጥ ላይ ነው። የቡድኑ መሪ ማኑዌል ፔሌግሪኒ እንዳስታወቁት ፍለጋው ከዚህ ወር ባሻገር የሚያልፍ አይሆንም። ካርሎስ ቴቬዝ እንግሊዝን ለቆ ከኢጣሊያው ሻምፒዮን ከጁቬንቱስ ቱሪን መቀላቀሉ የሚታወቅ ነው።

ስዊድን ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የሴቶች እግር ኳስ የአውሮፓ ሻምፒዮና ውድድር ጀርመን አይስላንድን 3-0 በመርታት ለመጀመሪያ ድሏ በቅታለች። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ፉክክር ከነገ በስቲያ ረቡዕ ከኖርዌይ የሚጋጠም ሲሆን ወደፊት የሚዘልቁት የሶሥቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኛ ቡድኖች እንዲሁም ሁለት ጠንካራ ሶሥተኞች ይሆናሉ።

በምድብ-አንድ ውስጥ አስተናጋጇ ስዊድንና ኢጣሊያ በእኩል አራት ነጥቦች መሪዎቹ ሲሆኑ ነገ እርስበርስ ተጋጣሚዎች ናቸው። ዴንማርክና ፊንላንድ እያንዳንዳቸው አንዲት ነጥብ ይዘው ይከተሏቸዋል። በምድብ-ሁለትም ጀርመንና ኖርዌይ አኩል ሆነው የሚመሩ ሲሆን በፊታችን ረቡዕ እርስበርስ ይጋጠማሉ።

በምድብ-ሶሥት ውስጥ ፈረንሣይና ስፓኝ መሪዎቹ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ሶሥት ነጥብ አላቸው። እንግሊዝና ሩሢያ ገና ያለ ነጥብ የበታቾቹ ናቸው። በዚሁ ምድብ ውስጥ በፊታችን ሐሙስ ሩሢያ ከስፓኝ፤ ፈረንሣይ ከእንግሊዝ ይጫወታሉ። ፍጻሜው ግጥሚያ የፊታችን ዕሑድ ሣምንት ይካሄዳል።

Wimbledon 2013 Finale Herren
ምስል Getty Images

ፈረንሣዊው ኒኮላስ ሜሁት በቀን ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ትናንት በአሜሪካ-ኒውፖርት የዓለምአቀፉ ሆል-ኦፍ-ፌም ነጠላ ባለድል ሆኗል። ሜሁት ለዚህ ክብር የበቃው የአሜሪካ ተጋጣሚዎቹን በግማሽ ፍጻሜው ማይክል ራስልን 6-2,6-2 በመርታትና በመጨረሻም የቀድሞውን የዓለም አንደኛ ሌይተን ሄዊትን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ ነበር። ሜሁት የመጀመሪያ የኤቲፒ ድሉን ባለፈው ወር ኔዘርላንድ ውስጥ ለመጎናጸፍ መብቃቱ የሚታወስ ነው። በጥንድም ፈረንሣዮቹ ኒኮላስ ሜሁትና ኤዶዋርድ ቫሤሊን የብራዚል ተጋጣሚዎቻቸውን ማርሤሎ ዴሞሊነርንና አንድሬ ሣን አሸንፈዋል።

ፓሌርሞ ላይ ትናንት በሁለት የኢጣሊያ ተፎካካሪዎች መካከል ተካሂዶ በነበረው የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ ሮቤርታ ቪንቺ ሣራ ኤራኒን 2-1 አሸንፋለች። ኤራኒ በ 2008 የፓሌርሞ-ኦፕን ባለድል እንደነበረች ይታወሳል። በቡዳፔስት ግራንድ-ፕሪ ደግሞ ሩሜኒያዊቱ ሢሞና ሃሌፕ የአውስትሪያ ተጋጣሚዋን ኢቮን ሞይስቡርገርን ትግል በተመላው ፍጻሜ ጨዋታ ለማሸነፍ በቅታለች። በጀርመን በሽቱትጋርት ኤቲፒ ውድድር ፍጻሜ የኢጣሊያው ፋቢዮ ፎግኒኒ ጀርመናዊውን ፊሊፕ ኮህልሽራይበርን 2-1 ሲረታ በስዊድን-ኦፕን ደግሞ አርጄንቲናዊው ካርሎስ ቤርሎክ የስፓኙን ፌርናንዶ ቫርዳስኮን 7-5,6-1 በማሸነፍ ለመጀመሪያ የኤቲፒ ድሉ በቅቷል።

Tour de France 2013 15. Etappe Christopher Froome
ምስል picture-alliance/dpa

በፈረንሣይ ቱውር-ዴ-ፍራንስ ውድድር ትናንት በተካሄደው15ኛ ደረጃ እሽቅድድም የእንግሊዙ ክሪስ ፍሮም 242,5 ኪሎሜትር ርዝመት ያለውን ኮረብታማ መንገድ አቋርጦ በማሸነፍ ለአጠቃላይ ድል ተቃርቧል። ርቀቱ የ 100ኛው ቱውር ረጅም ክፍል ሲሆን ቢጫ ሸሚዙንና በአጠቃላይ ነጥብ አመራሩን እንደያዘ የቀጠለውን ፍሮምን ዘንድሮ የሚያሸንፍ መገኘቱ የሚያጠያይቅ ነው።

ፍሮም በወቅቱ በአጠቃላይ በ 4 ደቂቃ ከ 11 ሤኮንድ ጊዜ የሚመራ ሲሆን የኔዘርላንዱ ባውከ ሞሌማ ሁለተኛና የስፓኙ አልቤርቶ ኮንታዶርም ሶሥተኛ ነው። የዛሬው ዕለት የዕረፍት ቀን ሲሆን ውድድሩ ነገ የመጨረሻ ሣምንቱን በመያዝ ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ