1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘመናዊው ሰው ከኢትዮጵያ ቻይና፥ 80 ሺህ ዓመታት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2008

በሣይንሳዊው መላ ምት ዘመናዊው የሰው ልጅ ምድር ላይ ተገኘ የሚባለው ከዛሬ 200,000 ዓመት በፊት ነው። ይኽ በሣይሳዊ አጠራሩ ሆሞ ሳፒያንስ (Homo Sapiens)፥ በላቲን ትርጓሜው ደግሞ «ጥበበኛው ሰው» አለያም «አዋቂው ሰው»፣ «ብልሁ ሰው» የሚል ስያሜ ያገኘው ዘመናዊ ሰው ምንጩ ከአፍሪቃ ብሎም ከኢትዮጵያ እንደሆነ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/1GsEo
Symbolbild Homo Sapiens Schädel eines Menschen
ምስል picture-alliance/dpa/J. Kalaene

ዘመናዊው ሰው ከኢትዮጵያ ቻይና፥ 80 ሺህ ዓመታት

ዘመናዊው ሰው ከአፍሪቃ ወደ ሌሎቹ ክፍላተ-ዓለማት መቼ ፈለሰ? በቅርቡ ቻይና ውስጥ የተደረገ የቅሪተ-አካል ምርምር «ጥበበኛው ሰው» ከምሥራቅ አፍሪቃ ፈልሶ አውሮጳ ከመድረሱ አስቀድሞ ቻይና መግባቱን ጠቁሟል። ይህ የሰው ዘር ከአፍሪቃ በቅርቡ የምትገኘው አውሮጳን ትቶ ስለምን ወደ ሩቅ ምሥራቋ ቻይና ተሻገረ? ጥያቄዎቹ በዚህ አያከትሙም።

«ጥበበኛው ሰው» አንዳንዴም «ዘመናዊው ሰው» ይሉታል፤ አሁን በምድር ላይ ከሚገኘው የሰው ልጅ የዘር ሐረግ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የሆሞ ሳፒያንስ ዝርያ። ዘመናዊው ሰው ከአፍሪቃ ተነስቶ እስያ ከመድረሱ በፊት አውሮጳ ሰፍሮ ነበር የሚለውን መላ ምት የሚሽር የሰው ልጅ ቅሪተ-አካል ባለፈው ሣምንት ቻይና ውስጥ ተገኝቷል። የቅሪተ-አካል ተመራማሪዎች 80 ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ ጥርሶችን ካገኙ ወዲህ ዘመናዊው ሰው አውሮጳ ከመድረሱ ከእጥፍ ዓመታት በፊት እስያ ውስጥ መገኘቱን ደርሰንበታል ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው ክሊቨላንድ የተፈጥሮ ሣይንስ ቤተ-መዘክር፥ በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ፦ ዘመናዊው ሰው ቻይና ውስጥ መገኘቱ የታወቀው በምንድን ነው?

China Fuyan Höhle Ausgrabung 47 Fossile Zähne Homo Sapiens Archäeogie
ቻይና ፉያን ዋሻ ውስጥ የተገኙት 47 ጥርሶችምስል S. Xing und X-J. Wu

ቻይና ፉያን ከተሰኘው ዋሻ ግራጫማ ከሆነ መረሬ አፈር ውስጥ ከተቀበሩበት የወጡት 47 ጥርሶች «የቅርብ ዘመን የሰው ዘር» የጥርስ አወቃቀርን ይመስላሉ ሲል የቻይና የሣይንስ አካዳሚ በጥናታዊ ጽሑፉ አስነብቧል። ጥርሶቹ ከአፍሪቃ የፈለሱ ሰዎች ቅሪት እንጂ እንደ ሆሞ ኤሬክቱስ ከመሳሰሉ የቅድመ ሰው ዝርያዎች ጋር ተዛምዶ የላቸውም ሲሉ ጥናታዊ ጽሑፍን ያቀረቡት ጸሓፍት ገልጠዋል። የዘመናዊው ሰው ዝርያ ከዛሬ 80 ሺህ እስከ 120 ሺህ ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ እስያ ሳይገባ አይቀርም ተብሎ ተገምቷል። ግኝቱ እስከ ዛሬ ድረስ ሲሰራበት የቆየውን ዘመናዊ ሰው ከአፍሪቃ ፈልሶበታል የተባለበትን መስመር እንደሚያዛባው ተገልጧል። በኬዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት፣ ሕይወት ያላቸው አካላት ጥናት እንዲሁም የአዕምሮ እና የዕውቀት ብቃት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ግን ምንም አያዛባም ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው የጥርሶቹ ዕድሜ እንደተባለው የቆየ ላይሆን መቻሉ ነው።

ቅሪተ-አካላት ላይ የተደረጉ ሐብለ-ዘር ትንታኔዎች (Genetic data ) እንደሚጠቁሙት ከሆነ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ የዘመናዊ ሰው ዝርያዎች አፍሪቃን ለቀው የወጡት ከዛሬ 70,000 እስከ 50,000 ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው። እናም እነዚህ ዝርያዎች እንደ ኒያንደርታል የመሳሰሉ ቀዳማይ ዝርያዎችን እንደተኩ በሣይንሱ ዓለም ይነገራል።

Bdt Hominiden Ausstellung Darwin Jahr Museum für Naturkunde Berlin
ምስል picture-alliance/dpa

ዝርያዎቹ ከአፍሪቃ የወጡት በቀይ ባሕር የላይኛው ክፍል አድርገው ወይንም ደቡባዊ ጫፉን ተከትለው በመቅዘፍ ሳይሆን አይቀርም የሚል መላምትም አለ። ጥቁር ያልሆኑ አፍሪቃውያን በአጠቃላይ ምንጫቸው የተቀዳው ከነዚህ የአፍሪቃ ፈላሲያን ዝርያዎች እንደሆነ ናሽናል ጂኦግራፊክ የተሰኘው በዓለማችን ግዙፉ የሣይንሳዊ እና ትምህርታዊ ግኝቶች ተቋም አትቷል። ዘመናዊው ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኘው አውሮጳ ከመሄድ ይልቅ ለምን ወደ ሩቅ ምሥራቅ መሄድን መረጠ? ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ መልስ አላቸው።

ዘመናዊው ሰው ከምሥራቅ አፍሪቃ ነው የተገኘው፤ እንዲሁም ጥቁር ያልሆኑ የዓለማችን ዘመናዊ ሰው ዝርያዎች መነሻቸው አፍሪቃ ነው ማለት ምን ማለት ነው?ዘመናዊው ሰው ከቀድሞው ሰው የሚለይበት በርካታ ነጥቦች እንዳሉ ይነገራል። ለመሆኑ ዘመናዊው ሰው ማለት ምንድን ነው?

በቅድመ-ታሪክ ጥናት የመስክና የቤተ-መኩራ መስክ ሰፊ ምርም ያደረጉት ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ እስካሁን በተገኙ መረጃዎች እና ጥናቶች መሰረት ኢትዮጵያ የዘመናዊው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ይገልጣሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ