1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝክረ-ሥዩም አባተ

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2011

አንጋፋው የእግር ኳስ የአሠልጣኝ ሥዩም አባተ የቀብር ስነ–ስርዓት በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9:00 ሰዓት ላይ ተፈጸመ። አስክሬኑ ካደረበት ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን ተወስዶ ሳሪስ በሚገኘው የሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ መደረጉን የአንጋፋው አሰልጣኝ ቤተሰብ የቅርብ ሰዎች ለDW ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/36RzQ
Kerze Kerzenlicht Symbolbild Energiearmut
ምስል Colourbox

የአሠልጣኝ ሥዩም አባተ የቀብር ስነ–ስርዓት ተፈጸመ

አንጋፋው የእግር ኳስ የአሠልጣኝ ሥዩም አባተ የቀብር ስነ–ስርዓት በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9:00 ሰዓት ላይ ተፈጸመ። አስክሬኑ ካደረበት ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን ተወስዶ ሳሪስ በሚገኘው የሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ መደረጉን የአንጋፋው አሰልጣኝ ቤተሰብ የቅርብ ሰዎች ለDW ተናግረዋል። 

ሥዩም አባተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጨዋችነት እና አሠልጣኝ ታላቅ አስተዋጽዖ ያበረከተ ባለሞያ ነው። ሥዩም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን ከተቀላቀለበት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ወርቃማው ከሚባልበት ዘመን አንስቶ ስሙ በተደጋጋሚ ከፍ ብሎ ተጠርቷል። ሥዩም አባተ  በ3ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍልሚያ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ካስገኙ ኃያል ተጨዋቾች መካከልም ይመደባል። 

ሥዩም ስመ-ገናና ከነበሩት ከእነ መንግሥቱ ወርቁ ዘመነኞች ቀጥሎ በመጣው ሁለተኛው ትውልድ ቡድን ውስጥ ተጫውቷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ኃያልነትን በዘመኑ ከፍ ካደረጉት እነ ፍስሐ ወልደአማኑኤል፣ ነፀረ ወልደ ሥላሴ፣ ዓለማየሁ ፊኛ፣ ጌታቸው ቡላ፣ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙን ከመሳሰሉ የያኔዎቹ ታዋቂ ተጨዋቾች ጋር አብሮ ተሰልፏል። በተለይም «በመሀል ሜዳ ተጫዋችነት በግብ አስቆጣሪነት፣ በቴክኒሺያንነት በጣም ትልቅ አስተዋጽዖ የነበረው ነው» ሲል የሥዩምን ላቅ ያለ አስተዋጽዖ ፍቅር ይልቃል ይገልጣል። 

ሥዩም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን መልካም ስም በተጎናጸፈበት በ1969ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ጀምሮ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርግም ነበር። አሰልጣኝ ሥዩም አባተ «በአሰልጣኝነት ትልቁ ሚናው የኢትዮ ቡና የአሰልጣኝነት ጊዜው ነው» ያለው ፍቅር የኢትዮጵያ ቡና ካገኛቸው ወደ 14 የሚጠጉ ዋንጫዎች መካከል «9ኙን ያሳካው እሱ» በመኾኑ አድናቆት የሚገባው መኾኑን ጠቅሷል። ሥዩም የኢትዮጵያ ቡናን እየተመላለሰ ለአምስት ጊዜያት አሰልጥኗል። 

የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ኳስ መስርቶ በመያዝ ማራኪ የእግር ኳስ እንዲጫወትም የአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ሚና ላቅ ያለ እንደኾነ ይነገራል። የኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድን አሁን ያለውን ድጋፍ እንዲያገኝ በማስቻልም የሥዩም ሚና የጎላ መኾኑን ብዙዎች ይመሠክራሉ። 

አንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ለህመም ተዳርጎ  የህክምና ክትትል ለማግኘት ጥረት ቢደረግለትም አመርቂ እንዳልነበር ፍቅር ተናግሯል። «ባለቁ ሰአት የተደረጉ ርብርቦች በተናጠል የተደረጉ እንጂ ያን ያህል በተደራጀ መንገድ በየዘርፉ ያሉ ባለሞያተኞቻችንን የሚያከብር አሠራር እንደሌለ የሚያሳብቁ ናቸው» ብሏል። በእርግጥ የቀድሞ አሰልጣኞች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ጥረት ቢደረግም ስኬታማ አለመኾኑን አክሏል። «አንዳንዶች እንደውም ዛሬም ቁጭታቸውን ሲገልጡ ሕክምናው ቀድሞ ቢደረግ ኖሮ በስልጠናው ላይ ለተጨማሪ ዓመታት ልናየው የምንችልበት ዕድል ይኖር ነበር ብለው ይከራከራሉ» ሲል ፍቅር የብዙዎችን ቁጭት አስታውሷል።  «ብዙ ጥሯል፣ ብዙ በእግር ኳስ ውስጥ ለፍቷል ግን በእግር ኳሱ ተገቢውን ክፍያ አግኝቷል ብዬ አላምንም» ሲልም ተናግሯል።  አንጋፋው የእግር ኳስ የአሠልጣኝ ሥዩም አባተ በ70 ዓመቱ ከዚህ ዓለም የተለየው ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 10 ሰዓት ግድም ነበር። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ