የህዋ ሳይንስ በኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2011ወደ ህዋ የምትመጥቀዉ ሳተላይት የምንኖርበትን አካባቢ የምድር ገፅታን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ወደ ምድር ትልካለች። ሳተላይቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላት እንደ ባለሙያዎች አባባል። በመላው ዓለም ስጋት እየሆነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ መላምትንናተፈጥሯዊ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ መረጃ ማግኘት ያስችላል። በዚህም የመሬት ምልከታ ሳተላይት የተፈጥሮ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ለመተንበይም ጠቀሜታው የጎላ ነውም ይሉታል። እንደ ጎርጎሪያን አቆጣጠር በ2014 የጠፈር ሳይንስ በኢትዮጵያ ተጀመረ። ኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ስትጀምር በአፍሪካ ስድስተኛ ሀገር ሆናለች። ኢትዮጵያ የሳተላይት ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ ለመስራት በቂ ቴክኖሎጂና የሰው ሀይል ስለሌለ የበለጸጉ ሀገራትን ማማተር ግድ ነዉ። በዚህም ቴክኖሎጂውን ከምታራምደው ቻይና ጋር ለመስራት ኢትዮጵያ ተስማማች። የጥቂት አመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስ ከቻይና ኢንጅነሮች ጋር በጋራ እየሰራች እንደሚገኝ ዶ/ር ሰለሞን በላይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ነግረውናል። የመሬት ምልከታ ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለማዕድን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ መረጃ የምታመላክት እንደሆነችም ታውቋል። መሰረታዊ የሆነ የሀገሪቱን ችግር ይፈታል ተብላ የምትታሰበው ይህችው ሳተላይት በመጪው ዓመት ወደ ህዋ ትላካለች። «በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት 2020 የመሬት ምልከታ ሳተላይት እናመጥቃለን። የእኛ ኢንጅነሮች ሳተላይት መስራት የምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም የስፔስ ፕሮግራማችን አስተዋውቀናል። ከቻይና ኢንጅነሮች ጋር በመሆን በጋራ እየሰራን ነው ያለነው። የኢትዮጵያ ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገች የኢትዮጵያ ችግር እንድትፈታ ነው ዓላማዋ ያደረግነው።» አብዛኛው ስራ እንደተጠናቀቀ የነገሩን ዶ/ር ሰለሞን በተባለው ጊዜ ትላካለች ይላሉ። «በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ስራ ተጠናቋል» 15 ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ወደህዋ በምትጓዘው ሳተላይት የማምጠቅ ስራ እንደሚሳተፉ ሲገልጹ፤ሳተላይት ለኢትዮጵያ ምን ያደርጋል ሲሉ ቴክኖሎጂውን የማይቀበሉ የህብረተሰብ ክፍል እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ሆኖም ለሀገርን ኢኮኖሚ ማስፈለጉን ያረጋግጣሉ ዶ/ር ሰለሞን። «ለዚህች ደሀ ሀገር ሳተላይት ምን ያደርጋል የሚል ይነሳል። ነገር ግን ሳተላይት ስፔስ ፕሮግራም ያላቸው የአፍሪካ ሀገሮች መካከለኛ ገቢ ገብተዋል። በርካታ ስራ ዕድል የሚፈጥር፤ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ነው» አቶ ይልቃል ሳሚ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት የሳተላይት ምርምር ልማትና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር እና በምርምር ስራው ላይ ተሳታፊም ናቸው። ቴክኖሎጂውን ከማሳደግ አንጻር በገንዘብና በሰው ሀይል አቅም ምክንያት ተጠቃሚ እንዳልሆንን ገልጸው፤ የሚሰጠው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ግን ጠቁመዋል። «ቴክኖሎጂው ወደሀገራችን የማላመድ ሂደት ብዙ እንዳልተሰራበት ቴክኖሎጂውን ለማሳደግ ከሚፈለገው የገንዘብና የሰው ሀይል አቅም አንጻር የዘርፉ ተጠቃሚ አይደለንም። ይሄ ቴክኖሎጂ ለሀገራችን የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የማላመድ ስራ መስራት አለብን» ወደ ህዋ የምትላከው ሳተላይት ማይክሮ ሳተላይት እንደሆነና ክብደትዋም 68 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን አቶ ይልቃል ነግረውናል። «በሚቀጥለው ዓመት ከህዳር እስከ ታህሳስ ባለው ጊዜ ሳተላይት ማምጠቅ እንችላለን ብለን ነው የምናስበው» ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነና፤ በህዋ ዘርፍ ጠንካራ ተወዳዳሪና እኩል ተጽእኖ ፈጣሪ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ባለሙያዎቹ ይስማሙበታል። በእድገት ጎዳና ለምታልመውና ለምትራመደው ኢትዮጵያ፣ የሳተላይት ቁልፍ መረጃ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጡታል።
ነጃት ኢብራሂም
ነጋሽ መሐመድ