የሐምሌ 25 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 25 2014የኦሬገኑ ድል በኮሎምቢያ ካሌም ይደገም ይኾን? እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምሽቱን የተለያዩ ግጥሚያዎችን ያከናውናሉ። ከወዲሁ ድል እየተመኘን ስለ ቀጣዩ ውድድር እና ቀደም ሲል ስለተቀዳጀነው ድል እንዲያወጋን የስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል። የእንግሊዝ ብሔራዊ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን የጀርመን አቻውን ባለቀ ሰአት ድል አድርጎ ታሪክ አስመዝግቧል። ሊቨርፑል በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነ የኮሙኒቲ ሺልድ የፍጻሜ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲን ድል አድርጎ የፕሬሚየር ሊግ ቁጭቱን ተወጥቶበታል። የአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)ቀጣይ የማጣሪያ ውድድሮች እንዲራዘሙ ውሳኔ አሳልፏል። ካታር የምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ 111 ቀናት ቀርተውታል።
የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ፉክክር የመጀመሪያ ቀን ውድድር ኮሎምቢያ ካሊ ውስጥ ዛሬ ማታ ይጀምራል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ቀናት በሚካኼደው ውድድር ተሳታፊ ነው። በዛሬው ምሽት ፉክክር ኢትዮጵያ በወንዶች 1500 ሜ. ማጣሪያ፤ በሴቶች 3000ሜ.መሰናከል ማጣሪያ፤ በሴቶች 800ሜ. ማጣሪያ፤ በሴቶች 3000ሜ. ፍፃሜ እንዲሁም በወንዶች 5000ሜ. ፍፃሜ የሚደረጉ ውጤቶችን ትጠብቃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዋናው ቡድን በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ባለፈው ሳምንት መላ ዓለምን ባስደመመ መልኩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ ይታወሳል። በውድድሩ የኢትዮጵያ ቡድን 4 የወርቅ ፣ 4 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን ከአፍሪቃ በአንደኛነት ከዓለም ደግሞ ከአሜሪካ ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ማጠናቀቁ የፈጠረው ደስታ ዛሬም ድረስ ከብዙዎች ዘንድ አልጠፋም። በቀጣይ ውድድሮች ውጤቶችን ለማስጠበቅ ምን መደረግ ይገባል? የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ፦ ኢትዮጵያ በኦሬገኑ ፉክክር እንዲያ ለየት ያለ እጅግ አስደሳች ውጤት ያገኘችበት ምክንያቱ ምን እንደነበር እንዲህ በማብራራት ይጀምራል።
የሴቶች የአውሮጳ ዋንጫ
በአውሮጳ ዋንጫ የወንዶችም ኾነ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው የቲኬት ሽያጭ በተመዘገበበት የዌምብሌ ስታዲየም የእንግሊዝ የሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ትናንት የጀርመን አቻውን በተራዘመ ሰአት ድል ድርጎ ዋንጫውን አንስቷል። በትናንቱ ግጥሚያ 87.192 ታዳሚዎች ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ተከታትለዋል። መደበኛ 90 ደቂቃው አብቅቶ በተራዘመው ግጥሚያ እንግሊዝ ጀርመንን 2 ለ1 ስታሸነፍ፤ የማሸነፊያዋን ግብ በ111ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረችው የ24 ዓመቷ አጥቂ ክሎዌ ማጂ ኬሊ ናት።
በፍጻሜ ግጥሚያው የእንግሊዝ ቡድን በ62ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚውን ግብ በኤላ ቱን ያስቆጠረበት መንገድ ማራኪ ነበር። ቤት ሜአድ በተጎዳችበት እና የእንግሊዝ አናብስት የተሰኘው ቡድን ሜዳ ውስጥ 10 በነበረበት ወቅት ነበር ግቡ የተቆጠረው። ዎልሽ 56ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ለገባችው አማካዩዋ ኤላ ቶን በርቀት መጥና የላከችላትን ኳስ ኤላ ከሁለት ተከላካዮች መሀል አልፋ ከግብ ጠባቂዋ አናት ላይ ሰቅስቃ የመታቻት ኳስ ከመረብ ማረፍ ችላለች። 79ኛው ደቂቃ ላይም ሊና ማጉል ጀርመንን አቻ የምታደርገውን ግብ በግሩም ኹኔታ ነበር ያስቆጠረችው።
የእንግሊዝ አናብስት የመጀመሪያቸው የኾነውን ዋንጫ ያነሱት በሩብ እና ግማሽ ፍጻሜው አመርቂ ድሎችን ካስመዘገቡ በኋላ ነበር። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሣሪና ቪግማን አንድም ባልተሸነፉበት ውድድር 12ቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ተሳክቶላቸዋል። አናብስቱ ድራማዊ በኾነ መልኩ ስፔንን 2 ለ1 አሸንፈው ነበር ለግማሽ ፍጻሜው የበቁት። በግማሽ ፍጻሜው ስዊድንን 4 ለ0 አንኮታኩተው ደጋፊዎቻቸውን ማስፈንደቅ ችለዋል። በፍጻሜው ደግሞ ጀርመንን ባለቀ ሰአት ድል አድርገው ታሪክ ሠርተዋል። የአሰልጣኝ ሣሪና ቡድን በዚህ ዓመት ውድድሮች 20 ኳሶችን ከመረብ ሲያሳርፍ የተቆጠረበት ሁለት ግቦች ብቻ ናቸው።
የእንግሊዝ ኮሙኒቲ ሺልድ የዋንጫ ፉክክር
ሊቨርፑል በሳምንቱ መጨረሻ ኪንግ ፓወር ስታዲየም ውስጥ በኮሙኒቲ ሺልድ የፍጻሜ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲን 3 ለ1 በመርታት የፕሬሚየር ሊግ ቁጭቱን መወጣት ችሏል። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕም በሊቨርፑል ቆይታቸው አንድ የቀራቸው የነበረውን የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫ ማንሳት ችለዋል። በዚህም ከፕሬሚየር ሊግ እስከ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ ከኤፍ ኤ ካፕ እስከ ኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችለዋል። በእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር አዘጋጅነት በእየ ዓመቱ የሚከናወነው የኮሙኒቲ ሺልድ የፍጻሜ ውድድር በፕሬሚየር ሊግ አሸናፊ እና በኤፍ ኤ ካፕ ባለድል መካከል የሚደረግ ነው። ዘንድሮ ሊቨርፑል የኤፍ ኤካፕ ዋንጫ ባለድል በመሆኑ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ በልጦ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳቱ ነበር የተገናኙት። በምሽቱ ግጥሚያ እድል ከሊቨርፑል ጋር ነበረች።
ሊቨርፑል በቅዳሜው ግጥሚያ ከመከላከል እስከ አስጨንቆ ማጥቃት ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል። ሊቨርፑል ከወሳኝ አጥቂዎቹ ሳዲዮ ማኔ ወደ ጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ቢያቀናበትም እሱን በተካው አዲስ አጥቂ አዲስ ተስፋ ሰንቋል። ከቤኔፊካ ሊዛቦን ዘንድሮ የተዛወረው ዳርዊን ኑኒዬዝ ለሊቨርፑል የመጀመሪያው የሆነችውን ሦስተኛዋን ግብ ተወርውሮ በጭንቅላቱ በመግጨት በድንቅ ኹኔታ አስቆጥሯል። ከጀርመኑ ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለማንቸስተር ሲቲ የፈረመው ኧርሊንግ ኦላንድ ግን በመጀመሪያ ግጥሚያው የመጀመሪያ የግብ አግዳሚውን ነቅንቋል፤ ግብ ግን አላስቆጠረም። የ19 ዓመቱ ፋቢዮ ካራባሎም በ90ኛው ደቂቃ ላይ በሉዊስ ዲያዝ ተቀይሮ ለሊቨርፑል የመሰለፍ እድል አግኝቷል።
በእንግሊዝ ኮሙኒቲ ሺልድ የሚሰኘው የሱፐር ካፕ ፍጻሜ ለሊቨርፑል ቀዳሚዋን ግብ በ21ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ነው። ሞሐመድ ሳላኅ በፍጹም ቅጣት ምት 83ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል። ለፍጹም ቅጣት ምቷ ምክንያት የኾነው ዘንድሮ ወደ ሊቨርፑል የመጣው ዳርዊን ኑኔዝ መደበኛ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው 4ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ለማንቸስተር ሲቲ ብቸኛዋን ግብ 70ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ጁሊያን አልቫሬዝ ነው። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ከቤኔፊካ ሊዛቦን ወደ 100 ሚሊዮን ዩሮ ግድም የተዘዋወረው አጥቂን በተመለከተ «ገና ምን ዐይታችሁ» ሲሉ ምርጥ አጥቂ ሲሉ አወድሰውታል። ከኡራጋያዊው የ23 ዓመት አጥቂ ወደፊት በፕሪሚየር ሊጉ እና ሌሎች ግጥሚያዎች ብዙ ይጠበቃል። ሳዲዮ ማኔ ባስቆጠረበት የጀርመን ሱፐር ካፕ የዋንጫ ግጥሚያ ደግሞ ባየርን ሙይንሽን ኤር ቤ ላይፕትሲሽን ቅዳሜ ዕለት 5 ለ3 ድል አድርጓል።
የአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን
የአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) በመስከረም ወራት ውስጥ ይካኼዱ የነበሩ ቀጣይ የአፍሪቃ ሃገራት የማጣሪያ ውድድሮች በካታሩ የዓለም ዋንጫ ምክንያት እንዲራዘሙ ውሳኔ አስተላልፏል። ከአፍሪቃ ሴኒጋል፣ ካሜሩን፣ ጋና፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊዎች ናቸው። ሴኔጋል በመስከረም ወር ውስጥ ከሞዛምቢክ ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ የደርሶ መልስ ውድድር ነበራት። በዓለም ዋንጫ መዳረሺያ ለፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የሚደረጉ ግጥሚያዎችን በማማረር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ካሰሙ አሰልጣኞች መካከል የሴኔጋሉ አሊዩ ሲሴ ዋነኛው ነበሩ። ካታር ውስጥ የሚከናወነው ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ 111 ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ካፍ ትናንት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የ3ኛ እና 4ኛ ዙር የምድብ ጨዋታዎች ከመጋቢት 11 ቀን እስከ 19 2015 ዓ.ም እንዲሁም አምስተኛ ዙር ግጥሚያዎች ከሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 13 ይከናወናሉ። 6ኛ ዙር ውድድሮች ደግሞ የሚከናወኑት ከነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋሊያዎቹ ቀጣይ 3ኛ እና 4ኛ የምድብ ጨዋታቸውን ከመጋቢት 11 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ያከናውናሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ