1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ/ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 4 2014

በፈረንሳይ ፓሪስ ሲካሄድ በሰነበተው የዓለም የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የተሳተፉ እና ኑሯቸውን በፈረንሳይ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ወክለው ባደረጉት ውድድር እስከ ሩብ ፍጻሜ ድረስ መጓዝ ችለዋል። በውድድሩ ላይ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የተወከሉ ታዳጊዎች በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት መሳተፍ አለመቻለቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4DySc

ሳምንታዊ ስፖርታዊ ዝግጅቶች

ሰላም ጤና ይስጥልን የተወደዳችሁ የስፖርት ዝግጅታችን ታዳሚዎች ፤ ሳምንታዊ አበይት ስፖርታዊ ክንውኖችን የምንዳስስበት የዛሬው መሰናዷችን ተጀምሯል፤ እግር ኳስ   ፣ ትኩረት የሳቡ ዓለማቀፍ የተጫዋቾች የዝውውር ጭምጭምታዎች ፣ የሜዳ ቴኒስ እንዲሁም በፓሪስ የኢትዮጵያውያን ታዲጊዎች በዓለማቀፍ ውድድር ላይ ያስመዘገቡትን አበረታች ውጤት  የተመለከተ አጭር ዘገባን ጨምሮ በዝግጅቱ ተካተዋል።


እግር ኳስ ፤ ከሳምንት በፊት ፍጻሜውን ባገኘው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጫወታቸውን ሲያደርጉ ያልተገባ ድርጊት ፈጽመዋል በተባሉ የፋሲል ከነማ እና የድሬዳዋ የድሬ ዳዋ ከተማ የእግር ኳስ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ። በክለቦቹ ላይ የቅጣት ዉሳኔ የተላለፈው የሊጉ የውድድር አመራር እና የሥነ ስረዓት ኮሚቴ ጫወታው በተደረገበት ዕለት የስነ ምግባር ግድፈት ሪፖርት የሊግ ኩባንያው ተቀብሎ ከተመረመረ በኋላ ነው። 


በዚህም የፋሲል ከነማ ከድሬ ዳዋ ከተማ ጋር በሰላሳኛው ሳምንት ባኬደው እና ለሁለቱም እጅግ ወሳኝ በነበረው ጫወታ ፤ ጫወታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃዎች ገደማ ሲቀሩት ፋሲል ከነማ ለድሬዳዋ ከተማ ስፖርታዊ ጨዋነትን ያልተከተለ ድጋፍ ስለመስጠቱ ማስረጃ እንደቀረበበት ሊግ ኩባንያው በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ ባወጣው  መግለጫ አመልክቷል። በተጨማሪም የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች  ወደ መጫወቻ ሜዳ ጥሰው ስለመግባታቸውና ሁከት ስለመቀስቀሳቸውም ሪፖርት መቅረቡን ኮሚቴው አስታውቋል። ይህንኑ ተከትሎም በፌዴሬሽኑ መመሪያ መሰረት የፋሲል ከነማ 100 ሺ ብር እንዲቀጣ መወሰኑን አስታውቋል። በተጨማሪም በቀጣይ ክለቡ በሜዳው የሚያደርጋቸውን የመጀመሪያ ሁለት ጫወታዎች ያለደጋፊ እንዲያከናውን ውሳኔ ተላልፎበታል። የድሬዳዋ ከተማ የእግር ኳስ ክለብም በ28ኛው ሳምንት የውድድር መርኃ ግብር  ከባህርዳር ከተማ በነበረው ጫወታ ደጋፊዎቹ በፈጠሩት ያልተገባ ድርጊት ክለቡ 75 ሺ ብር መቀጣቱን የሊግ ኩባንያው ገልጿል።
በፈረንሳይ ፓሪስ ሲካሄድ በሰነበተው የዓለም የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የተሳተፉ እና ኑሯቸውን በፈረንሳይ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ወክለው ባደረጉት ውድድር እስከ ሩብ ፍጻሜ ድረስ መጓዝ ችለዋል። በውድድሩ ላይ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የተወከሉ ታዳጊዎች በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት መሳተፍ አለመቻለቸው ተገልጿል። በውድድሩ ላይ በቀጥታ የተሳተፉትን እንዲሁም በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ታዳጊዎችን ያስተባበሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማሕበር በፓሪስ ተወካዮችን   የፓሪሷ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ አነጋግራለች። 

Frankreich | World Game in Paris | Äthiopische Kinder
ምስል Haimanot Tiruneh/DW
Frankreich | World Game in Paris | Äthiopische Kinder
ምስል Haimanot Tiruneh/DW


ከእግር ኳስ ሳንወጣ በዓለም  አቀፍ ደረጃ ስም እና ዝናቸው የገነነ በተለይ በአውሮጳ ሀገራት ሊጎች ውስጥ የሚታወቁ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የዝውውር ጭምጭምታዎች ይዘናል። ቀዳሚያችን ክርስቲያኖ ሮናልዶን የተመለከተ ዘገባ ነው። የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ተጨዋቹ የአዲሱ የውድድር ዘመን ዕቅዳቸው አካል እንጂ ለሽያጭ እንማይቀርብ አስረግጠው ተናግረዋል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ የቅድመ የውድድር ዘመን ዝግጅት ለማድረግ ወደ ታይላንድ ካቀናው የማንችስተር ዩናይትድ ክለብ ጋር  ሳይጓዝ ከቀረ በኋላ ሊለቅ እንደሚችል በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።  አሰልጣኙ ይህንኑ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት «እርሱ የውድድር ዘመኑ ዕቅዳችን አካል ነው፤ ከእርሱ ጋር ስኬትን እንጎናጸፋለን» ሲሉ ለጭምጭምታዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል። 

Fußball | Premier League | Manchester United - Tottenham Hotspur | Cristiano Ronaldo
ምስል Naomi Baker/Getty Images


የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም የፊት አውራሪው ሃሪ ኬን ስሙ ከጀርመን ኃያል ክለብ ባየር ሙኒሽን ጋር መያያዙን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ባየርን ሙንሽን የጎል አዳኙን ሮበርት ሉዋንዶውስኪን ለመተካት ሲል ሃሪኬንን የማስፈረም ፍላጎት እንዳሳየ ነው የተገለጸው። ባየርኖች ፊታቸውን ወደ ሃሪ ኬን ያዞሩት ሉዋንዶውስኪ ክለቡን ለመልቀቅ ከድምዳሜ ላይ መድረሱን ተከትሎ ነው ተብሏል። ሉዋንዶውስኪ  የዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ አስቀድሞ የስፔይኑን ኃያል ክለብ ባርሴሎናን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል። ነገር ግን የሉዋንዶውስኪ ወደ ባርሴሎና ማቅናት ምናልባት እክል ቢገጥመው የእንግሊዙ ቼልሲ እና የፈረንሳዩ ፓሪሰን ዣርሜ ተጫዋቹን የራሳቸው ለማድረግ ፍክክር ውስጥ መግባታቸውም ተያይዘው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። የሆነ ሆኖ ሙኒክ ኬንን የራሱ ለማድረግ ስላደረገው ከማጤን ያለፈ ስለተደረገ ጥረት አልፎም ከተጫዋቹም ሆነ ወኪሉ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም። 

Länderspiel England v Deutschland Harry Kane
ምስል Catherine Ivill/Getty Images


በሌላ የዝውውር ጭምጭምታዎች 
የጣሊያኑ ዩቬንቱስ እና የእንግሊዙ ቼልሲ ሴኔጋላዊውን የናፖሊ ተከላካይ ካሊዱ ኩሊባሊን የግላቸው ለማድረግ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል። ነገር ግን ሩሲያዊው ባለሃብት ሮማን አብርሃሞቪች ክለቡን ከለቀቁ ወዲህ ቀውስ ውስጥ የቆየው ቼልሲ የ31 ዓመቱን ተጫዋች ለማስፈረም ናፖሊ የጠየቀውን የ34 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል መስማማቱን ዘ ሰን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በሌላ በኩል ደግሞ ቱቶ ስፖርት አሮጊቷ ዩቬ ከኩሊባሊ በተጨማሪ ለሆላንዳዊውን ተከላካይ ማቲያስ ዲ ሊግትን ለማስፈረም የ90 ሚሊዮን ፓውንድ ማቅረባቸውን በገጹ ላይ ይዞ በወጣው መረጃ አመልክቷል ። ወሳኙን የተከላካይ ክፍል ተጫዋች ለማስፈረም ከዩቬንቱስ በተጨማሪ ባየርን ሙንሽን እና ቼልሲም ፉክክር ውስጥ እንደገቡ ተጠቅሷል። 

Africa Cup of Nations Malawi vs Senegal
ምስል Pius Utomi Ekpei/Getty Images/AFP

አትሌቲክስ 
የኦለማችን የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮናው ኤሉድ ኪፕቾጌ በመጪው ዓመት መስከረም በበርሊን በሚካሄደው የማራቶን ውድድር  እንደሚሳተፍ አስታወቀ። ኪፕቾጌ የማራቶን ክብረወሰን ባስመዘገበባት በርሊን በአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በስፍራው ተይዞ የቆየውን ርቀቱን ለአራት ጊዜያት ክብረ ወሰን መሰባበር ለመድገም እንደሚሻ አስታውቋል። ኪፕቾጎ ከአሁን አስቀድሞ ለሶስት ጊዜያት ያህል የበርሊን ማራቶን ክብረ ወሰኖችን የሰባበረ ሲሆን አሁን በእጁ የሚገኘውን የርቀቱን ክብረ ወሰን  በጎርጎርሳውያኑ 2018 2 ሰዓት ከ 1  ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በመግባት የግሉ አድርጎታል። ከዚያ በኋላ እዚያው በርሊን ውስጥ ከአንድ ኦመት በኋላ ተደርጎ በነበረው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ 2 ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት ለሁለት ሰከንዶች ክብረወሰኑን ለጥቂት ማጣቱ ይታወሳል። ሰዓቱም  የምንጊዜም ሁለተኛ ሰዓት ሆኖ ለቀነኒሳ በቀለ ተመዝግቦለታል። ኪፕ ቾጌ ከተሳተፈባቸው 16 የማራቶን ውድድሮች 14ቱን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሁለት የኦሎምፒክ ውድድሮች ይገኙበታል።  

Tokio 2020 | Leichtathletik | Goldmedaille | Eliud Kipchoge aus Kenia
ምስል Shuji Kajiyama/AP Photo/picture alliance


የሜዳ ቴኒስ 
የዊበልደኑ የሜዳ ቴኒስ አሸናፊ ሰርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች አውስትራሊያዊውን ኒክ ኪርጊዮስን በማሸነፍ በወንዶች የግራንድ ስላም የነጠላ ውድድር ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። የ35 ዓመቱ ጆኮቪች የመጀመሪያውን ዙር 4 ለ 6 በሆነ ውጤት ሽንፈት ገጥሞት የነበረ ቢሆንም ቀጥለው የተደረጉትን ጫወታዎች 6 ለ 3 ፣ 6 ለ 4 ፣ 7 ለ 6 በአጠቃላይ 3 ለ 1 በሆነ ድምር ውጤት ማሸነፍ የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል። ጆኮቪች አሸናፊነቱን ተከትሎ ለ19ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።ይህም ውጤት ለ22 ጊዜ ካሸነፈው ራፋኤል ናዳል ቀጥሎ ሁለተኛው ሰው ያደርገዋል። 

Großbritannien |  Wimbledon Tennis Novak Djokovic
ምስል Kirsty Wigglesworth/AP Photo/picture alliance

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ