የመረጃ እጦት በኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 19 2014የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች በቂ መረጃ ባለመስጠታቸዉ ማረጃ የማግኘትና የማሰራጨትን መብት እየተጋፉ መሆናቸዉን ጋዜጠኞች አስታወቁ።በተለይ ለዉጪና ለግል መገናኛ ዘዴዎች የሚሰሩ ጋዜጠኞች እንደሚሉት በየደረጃዉ የሚገኙ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ለየሥጣናቸዉ ይጠቅማል ከሚሉት ዉጪ ጋዜጠኛዉ የሚፈልጋቸዉን መረጃዎች አይሰጡም።ለመገናኛ ዘዴዎች መረጃ የሚከለክሉ፣ በየሰበብ አስባቡ ጋዜጠኞችን የሚያሸሹና በጋዜጠኞች ሲፈለጉ የሚጠፉ ባለስልጣን ተጠያቂ አለመሆናቸዉንም ጋዜጠኞቹ ገልፀዋል።
ህዝብ የሚፈለገውን መረጃ የማግኘት መብቱ እየተጠበቀ አይደለም ሲሉ ጋዜጠኞቹ አመልክተዋል፣ አንድ የሙያው ምሁር ደግሞ “ባለስልጣናት መረጃ የማይሰጡት በራስ ካለመተማመን፣ ሚዲያን ከመፍራትና ተጠያቂነት አለመኖር ነው” ብለዋል፣
አሁን አሁን ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ መረጃን አሰባስቦና አጠናቅሮ ለህዝብ ማድረስ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ጋዜጠኞች ይናገራሉ፡፡ የመንግስት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ለመረጃ ግን በራቸውን ዝግ የሆኑት ብዙዎች ናቸው፡፡ ኃላፊዎች በተለይ የመረጃ ምንጭ ላለመሆን የተለያዩ ሰበቦችን እንደሚያቀርቡ ጋዜጠኞቹ ይገልፃሉ፡፡
አንድ በመንግስት ሚዲያ ተቋም የሚሰራ ጋዜጠኛ እንዳለው “መረጃ ለማግኘት ወደ አንድ ኃላፊ ቢሮ ስትሄድ የኃላፊው ፀሐፊ ገና ከበር እንዴት? ለምን? በሚሉ ጥያቄዎች ታጣድፍሀለች፣ ጥያቄዎችህ ምንድን ናቸው በሚል ካለ ስራዋም ገብታ አጥር ትሆንብሀለች፣ በመጨረሻም ስብሰባ ናቸው ወይም የሉም በሚል ትመልስሀለች” ብሏል፡፡
መረጃ ላለመስጠት ለጋዘየጠኛው የሚሰጡ ምክንያቶች ተደጋጋሚና የሰለቹ እንደሆኑ ሌላዋ በግል የሚዲያ ተቋም የምትሰራ ጋዜጠኛ ነግራናለች፡፡ “ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ አሁን ወጥተዋል፣ አይመቸኝም፣ ደውይልኝ” የሚሉ ምላሶች እንደሚሰጣት አመልክታ በተባለችበት ሰዓትና ስልክ ቁጥር ስትደውል ግን ስልኩ ዝግ ይሆናል ወይም አይነሳም፡፡
አንዳንድ ባለስልጣናት ሲፈልጉ እንጂ ሲፈለጉ መረጃ የማይሰጡት ግልፅነት ያለው ተጠያቂነት ባለመኖሩና በብልሹ አሰራር ውስጥ ስለሚዘፈቁ፣ ህዝብን አለማክበርና ኃላፊነትን ለመወጣት አቅም ማጣት ሊሆን እንደሚችል ብዙዎቹ ጋዘየጠኞች ይናገራሉ፡፡
“ አንደኛ ተጠያቂ አይደሉም፣ ሁለተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ስለሚኖርባቸው መረጃ መስጠት እነሱንም ስለሚያስጠይቸው ይፈራሉ፣ ህዝብን መናቅና አለማክበር፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነትንም አለማወቅ ነው”
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶ/ር አደም ጫኔ አንዳንድ ባለስልጣናት መረጃ ለመስጠት የማይፈልጉባቸው ምክንያቶች፣ ” በራስ አለመተማመን፣ ሚዲያን መፍራትና አሁን አሁን ደግሞ ሚዲያዎችን የእኛና የነሱ ብሎ በመክፈል ለፖለቲካ ስርኣቱ የተጠጉትን ማቅረብና ሌሎችን ማቅረብ ናቸው” ብለዋል፡፡
አንድ ኃላፊ መረጃ ለአንድ ጋዜጠኛ አልስጥም ማለቱ፣ ጋዜጠኛውን ሳይሆን የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት እንደነፈገ ማወቅ እንዳለበት ባለሙያው ገልጠዋል፤ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንዳለበት አመልክተዋል፣ አለዚያ ግን ብልሹ አሰራር እንደስርዓት ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ህገመንግስት በአንቀጽ 29 ቁጥር 3 ላይ የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብትን ደንግጓል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ