1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 09 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 9 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ አርሰናል በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። የዕውቁ ኢትዮጵያዊ ኢጣሊያዊ የእግር ኳስ ተጨዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ዕለት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/4H4On
Bundesliga 7. Spieltag Borussia Mönchengladbach - RB Leipzig
ምስል Federico Gambarini/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ አርሰናል በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። ብሬንትፎርድን በአስተማማኝ ሁኔታ ድል አድርጓል። ዛሬ በፈጸመው የዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ሥርዓተ ቀብር ምክንያት ሊቨርፑል ከቸልሲ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ትናንት ሊያደርጉ የነበረው ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።  የዕውቁ ኢትዮጵያዊ ኢጣሊያዊ የእግር ኳስ ተጨዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ዕለት ተፈጽሟል። ሉቺያኖ እና ወንድሙ ኢታሎን በቅርብ የሚያውቋቸው አንጋፋዉ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔን አነጋግረናል። ሉቺያኖ በ87 ዓመቱ ያረፈው ጣሊያን ውስጥ ሮም ከተማ አቅራቢያ በሚኖርባት ኦስቲያ ከተማ ነው። 

አትሌቲክስ

ትናንት በተከናወነው የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አመርቂ ድል ተቀዳጅተዋል። በዚሁ ውድድር በሴቶች ምድብ ታዱ ተሾመ፣ ጽጌ ገብረ ሰላማ እና ጥሩዬ መስፍን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ሌላ ጣልቃ ሳያስገቡ አሸናፊ መሆን ችለዋል። ታዱ ተሾመ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 1ሰዓት ከ:06: ደቂቃ 13 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ጽጌ ገብረ ሰላማ ከ22 ሰከንድ በኋላ በመግባት የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ሦስተኛ ደረጃን ያገኘችው ጥሩዬ መስፍን ደግሞ 1ሰዓት ከ:06: ደቂቃ 42 ሰከንድ ሮጣለች።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ከአንድ ሰአት በታች በነበረው የወንዶች ተመሳሳይ ፉክክርም ኢትዮጵያውያኑ ድል ቀንቷቸዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ 58 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አምደ ወርቅ ዋለልኝ በ59 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ሦስተኛ ደረጃውን በ2 ሰከንዶች ተበልጦ ኬኒያዊው አትሌት ፌሊክስ ኬፕኮዬች አግኝቷል።

ለጀርመን የሚሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌት አማናል ጴጥሮስ የ23ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አማናል በነሐሴ ወር ሙይንሽን ከተማ ውስጥ የ4ኛ ደረጃን ካገኘበት የአውሮጳ ፍጻሜ የማራቶን ውድድር በኋላ ባደረገው የትናንቱ ፉክክር እስከ አጋማሹ ድረስ ውጤት ለማስመዝገብ ቆርጦ እንደገባ ያስታውቅ ነበር። ሆኖም ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ብዙም ወደፊት መጓዝ ሳይችል ቀርቶ የ23ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። አጠቃላይ ውድድሩ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቋል።

በሌላ የማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ትእግስት ግርማ እና ለተብርሃን ኃይላይ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃውን ይዘው ለድል በቅተዋል። በአውስትራሊያ ሲድኒ ማራቶን ፉክክር ትእግስት አንደኛ የወጣችው 2 ሰአት ከ25 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በዚህ ውድድር ትእግስት የቦታውን ክብረወሰን ለመስበር 37 ሰከንድ ብቻ ነበር የቀራት። ለተብርሃን ከ35 ሰከንድ በኋላ ትእግስትን ተከትላ የ2ኛ ደረጃን ይዛለች። ሦስተኛ ደረጃው በኤርትራዊቷ አትሌት ናዝሬት ወልዱ ነው የተያዘው።

በወንዶች ፉክክር ደግሞ በአውስትራሊያ ምድር እጅግ ፈጣኑ የተባለው ሰአት ክብረወሰን በኬኒያዊው አትሌት ሞሰስ ኪቤት ተሰብሯል። ሞሰስ ክብረወሰኑን የሰበረው 2 ሰአት ከ7 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ቀደም ሲል ክብረወሰኑ በጃፓናዊው ሯጭ ዩታ ሺታራ በ2:07:50 የተያዘ እና ለሦስት ዓመታት የቆየ ነበር።  ሁለተኛ ደረጃውም በሌላኛው ኬንያዊ ሯጭ ኮስማስ ማቶሎ በ2 ሰአት ከ7 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ የተያዘ ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጫሉ ደሶ፣ አበበ ነገዎ እና ኦሊካ አዱኛ ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ በተከታታይ ይዘዋል።

Logo CAF  - Confédération Africaine de Football

ዕዉቁ ኢትዮጵያዊ-ኢጣሊያዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ ጣሊያን ኦስቲያ ከተማ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። የ87 ዓመት ባለጸጋ የነበረው ሉቺያኖ ያረፈው ለረጅም ጊዜ በኖባት እና ሮም አጠገብ በምትገኘዉ የኦስቲያ ከተማ ነው። በ1960ዎቹ ሉቺያኖ ከታናሽ ወንድሙ ኢታሎ ጋር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመመረጣቸው በፊት ለአስመራ ቡድን ይጫወቱ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1963 ዓ.ም የአፍሪቃ ዋንጫን ሲወስድም ሉቺያኖ ቫሳሎ ከአጥቂ ተጨዋችነቱ በተጨማሪ የቡድኑ አምበልም ነበር። አንጋፋዉ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ስለ ሉቺያኖ ማንነት እና ኅልፈት በተለይ ለዶቸ ቬለ (DW) ቀጣዩን ብለዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ትናንት ከብሬንትፎርድ ጋር በድንቅ ሁኔታ ተፋልሞ የሚገባውን አግኝቷል። አርሰናል በዊሊያም ሳሊባ፣ ጋብሪዬል ጄሱስ እና ፋቢዮ ቪዬራ ግቦች 3 ለ0 በማሸነፍ የፕሬሚየር ሊጉ መሪነቱን አስጠብቋል። አርሰናልን ያስተናገደው ብሬንትፎርድ እስካሁን በሜዳው ተሸንፎ ዐያውቅም ነበር።  በዘንድሮ ውድድር ሁለተኛ ሳምንት ግጥሚያ ብሬንትፎርድ ማንቸስተር ዩናይትድን ጭምር 4 ለ0 በሆነ አስደንጋጭ ሁኔታ አሸንፎ ነበር። በዘንድሮ ውድድር አርሰናል የሚጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው ደግሞ በማንቸስተር ዩናይትድ ነው። 18 ነጥብ የሰበሰበው አርሰናል በመቀጠል በኤሚሬት ስታዲየም የሚገጥመው ቶትንሀም ሆትሰፐርን ነው። ቶትንሀም ሆትሰፐር ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን በሰፋ የግብ ልዩነት 6 ለ2 ጉድ አድርጎ ነጥቡን እንደ ማንቸስተር ሲቲ 17 አድርሷል።

Premier League | West Ham United v Manchester City
ምስል David Klein/Newscom/picture alliance

የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ተበልጦ የሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ዎልቨርሀምፕተን ዋንደረርስን 3 ለ0 አሸንፏል። ከሜዳው ውጪ የተጫወተው ማንቸስተር ሲቲ ቀዳሚዋን ግብ በጃክ ግሪሊሽ ለማስቆጠረር ሜዳ ውስጥ የፈጀበት ጊዜ 1 ደቂቃ ብቻ ነበር። ከዚያም ኧርሊንግ ኦላንድ እና ፊል ፎዴን ባስቆጠሯቸው ግቦች ማንቸስተር ሲቲ ለድል በቅቷል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ብራይተን በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከክሪስታል ፓላስ ጋር ቅዳሜ ዕለት የነበረው ግጥሚያ በባቡር ጉዞ አገልግሎት የሥራ ማቆም አድማ የተነሳ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ሌላ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ12 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድም ከሊድስ ጋር ትናንት የነበረው ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ቸልሲ እና ሊቨርፑል ትናንት ሊያደርጉ የነበረው ግጥሚያም በዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ሥርዓተ ቀብር ምክንያት አልተካኼደም። ጨዋታዎቹ ትናንት ሳይከናወኑ የቀሩት በዛሬው ሥርዓተ ቀብር በርካታ ፖሊሶች ስለሚያስፈልጉ ነውም ተብሏል። ቸልሲ እና ሊቨርፑል 10 እና 9 ነጥብ ይዘው 6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፉልሀም ስር ሰፍረዋል። ሁለቱም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል። ያሸነፈ ቡድን የስድስተኛ ደረጃውን ከፉልሃም ይረከባል።

ቡንደስሊጋ

Bundesliga | 1. FC Union Berlin - VfL Wolfsburg
ምስል FABRIZIO BENSCH/REUTERS

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የባየርን ሙይንሽን በአውግስቡርግ 1 ለ0 መሸነፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። 59ኛው ደቂቃ ላይ በሜርጊም ቤሪሻ የተቆጠረችው ብቸኛ ግብ አውግስቡርግን ለፈንጠዚያ ባየርን ሙይንሽንን ለሐዘን ዳርጋለች።  ባየርን ሙይንሽን በ12 ነጥቡ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዑኒዮን ቤርሊን በግስጋሴው ቀጥሎ ቮልፍስቡርግን ትናንት 2 ለ0 ድል አድርጓል። በ17 ነጥቡም በቡንደስሊጋው 1ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 15 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሻልከን ቅዳሜ ዕለት 1 ለ0 አሸንፏል። ፍራይቡርግ እና ሆፈንሀይም 14 እና 13 ነጥብ ይዘው ከባየርን ሙይንሽን በላይ ይገኛሉ።

በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ትናንት ያደረጉት ግጥሚያ በሪያል ማድሪድ የ2 ለ1 ድል ተጠናቋል። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ተከላካይ ማሪዮ ሔርሞሶ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው አንድ ደቂቃ ላይ ከሜዳ በቀይ ተሰናብቷል። ሪያል ማድሪድ ላሊጋውን በ18 ነጥብ ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ10 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባርሴሎና፣ ሪያል ቤቲስ፣ አትሌቲኮ ቢልባዎ፣ ዖሳሱና እና ቪላሪያል ከ2ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ተደርድረዋል።  

የሜዳ ቴኒስ

Tennis | ATP-Turnier in Halle | Roger Federer
ምስል Friso Gentsch/dpa/picture alliance

አንዲ ሙራይ ከስዊዘርላንዳዊው የዓለማችን የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ሮጄር ፌዴሬር ጋር የመጨረሻ የስንብት ግጥሚያ ለማድረግ ተስፋ ሰንቆ እንደነበር ተናገረ። የ41 ዓመቱ ሮጄር ፌዴሬር ከቴኒሱ ዓለም ከውድድር መሰናበቱን ይፋ ያደረገው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር። በዓለም የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድሮች ለ20 ጊዜያት ዋንጫዎችን የሰበሰበው ሮጄር ፌዴሬር ከውድድር ዓለም የተሰናበተው በተደጋጋሚ በደረሰበት ጉዳት መሆኑንን ዐሳውቋል። የብሪታንያው ሌላኛው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች አንዲ ሙራይ የላቨር ከፕ ውድድር ላይ «ልዩ» የሆነ የፍጻሜ ግጥሚያ ከሮጄር ፌዴሬር ጋር ለማድረግ ተስፋ ሰንቆም እንደነበር ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ