1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 16 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 16 2015

በቤርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸናፊ ኾናለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአቋም መለኪያ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባካኼደው ሁለተኛ ግጥሚያ ከሱዳን አቻው ጋር ሁለለት እኩል ወጥቷል።

https://p.dw.com/p/4HNFw
Tigist Assefa und Eliud Kipchoge gewinnen Berlin Marathon
ምስል Christoph Soeder/AP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቤርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸናፊ ኾናለች። በዚሁ የወንዶች ፉክክር ኬንያዊው አትሌት ኤሊዩድ ኪፕቾጌ እንደዛተው የዓለም ክብረወሰን ማሻሻል ችሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአቋም መለኪያ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባካኼደው ሁለተኛ ግጥሚያ ከሱዳን አቻው ጋር ሁለለት እኩል ወጥቷል።  ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ሲያነሳ ዋነኛ ተፎካካሪው የኢትዮጵያ ቡና የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። የአውሮጳ ኔሽን ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዛሬ እና ነገ ማታም ይከናወናሉ። እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ደካማ ውጤት አስመዝግበዋል። 

አትሌቲክስ
ጀርመን ዋና ከተማ ቤርሊን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የበርሊን ማራቶን የሩጫ ውድድር በሴቶች የቦታው ክብረወሰን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ ተሰብሯል። አትሌት ትእግስት ለድል የበቃችው 2:15.37 በመሮጥ ነው። የ28 ዓመቷ ትዕግስት ለማራቶን ስትሮጥ የበርሊኑ ሦስተኛዋ ሲሆን የገባችበት ሰአትም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ተብሎ ተመዝግቧል።  በዚህ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ትግስት አባይቼው የ3ኛ ደረጃን አግኝታለች። የሮጠችውም 2:18.03 ነው። ኬኒያዊቷ ሮዝሜሪ ዋንጂሩ ከትዕግስት 02:23 ዘግይታ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያውያቱ ወርቅነሽ ኤዴሳ አራተኛ፣ ሲሳይ መሠረት አምስተኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቀዋል።

Eliud Kipchoge gewinnt Berlin Marathon
ምስል imago images

በወንዶች የቤርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር የ37 ዓመቱ ኬንያዊው አትሌት ቀደም ሲል እንደዛተው በራሱ የተያዘውን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ለድል በቅቷል። ኢልዩድ ኪፕቾጌ ለድል የበቃው በ02:01:09 በመሮጥ ነው። ሁለተኛ የወጣውም ኬንያዊ ማርክ ኮሪር ሲሆን ከኢሊውድ በአራት ደቂቃ ከ49 ሰከንዶች ዘግይቶ ነው የገባው። ኢትዮጵያዊው ታዱ አባተ በ02:06:28 ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ኢትዮጵያውያኑ አንድአምላክ በልሁ እና ልመንህ ግዛቸውም አራተኛ እና ስድስተኛ ኾነው አጠናቀዋል። ኪፕቾጌ እስካሁን ከተሳተፈባቸው 17 የማራቶን ሩጫዎች 15ቱን አሸንፏል።  

በትናንቱ የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ብርቱ ተፎካካሪው ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ኢትዮጵያዊው ሯጭ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር  በ2018 በተካሄደው የቤርሊን ማራቶን ከኪፕቾጌ ቀጥሎ ሁለተኛ ሆኖ ቢጨርስም ትናንት ግን ከ35ናው ኪሎ ሜትር በኋላ ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዷል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ጉዬ አዶላ በ2021 በተደረገው የቤርሊን ማራቶን ሩጫ አሸናፊ ነበር። 

Eliud Kipchoge gewinnt Berlin Marathon
ምስል Christoph Soeder/AP

እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአቋም መለኪያ ዛሬ ሰኞ መስከረም 16 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከሱዳን አቻው ጋር በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሁለተኛ ጨዋታውን አከናውኖ ሁለት እኩል ወጥቷል። በዛሬው ጨዋታ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠሩት ዳዋ ሆቴሳ እና ቸርነት ጉግሳ ናቸው። ዋሊድ ኤል ሹዋሊ መሐመድ አብዱራህማን ለሱዳን አስቆጥረዋል። ባለፈው ሳምንት ዓርብ መስከረም 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በነበረው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአቋም መለኪያ ግጥሚያ ሁለቱ ቡድኖች የተለያዩት አንድ እኩል በመውጣት ነበር። ግቦቹንም ሽመልስ በቀለ እና አብዱልራዚቅ ያኩብ ናቸው ያስቆጠሩት።
ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ባሻገር እድሜያቸው ከ23 እና ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች የሚሳተፉባቸው ግጥሚያዎችም እየተከናወኑ ነው። በአፍሪቃ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታውን ለማከናወን የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኪንሻሳ ከተማ ትናንት መድረሱ ተገልጧል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ነው የተለያየው።

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚፎካከሩበት የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ (CECAFA) የእግር ኳስ የማጣርያ ውድድር ተሳታፊ ሃገራት ወደ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከትናንት ጀምሮ እየገቡ ነው። ትናንት የዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ልዑካን አዲስ አበባ ደርሰዋል። የሴካፋ ውድድር ከመስከረም 20 - ጥቅምት 9 ድረስ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ይከናወናል።

Ethiopia’s national football team players train ahead of the AFCON tournament in Cameroon.
ምስል Haimanot Turuneh/DW

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግጥሚያ ትናንት ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ ኾኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀብቶም ገ/እግዚአብሔር ብቸኛ ግብ ተጋጣሚው መቻልን 1 ለ0 ድል አድርጎ ነው ሻምፒዮና መሆኑን ያረጋገጠው። ለደረጃ በነበረው ግጥሚያ ኢትዮጵያ ቡና በአብዱልሀፊስ ቶፊቅ ብቸኛ ግብ ለገጣፎ ለገዳዲን 1-0 አሸንፏል። በግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና አንድ እኩል ተለያይተው በመለያ ምት ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ለ3 አሸንፎ ነው ለፍጻሜ የደረሰው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጻሜው የተሸነፈው መቻል ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው ለገጣፎ ለገዳዲን 3 ለ2 አሸንፎ ነው ለፍጻሜ የደረሰው። 

የአውሮጳ ኔሽን ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ
55ቱም የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ሰሞኑን በኔሽን ሊግ ውድድሮች ተጠምደዋል። ውድድሩ ዛሬም ቀጥሎ፦ ምሽቱን እንግሊዝ ከጀርመን እንዲሁም ሐንጋሪ ከጣሊያን ጋር የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ምድቡን ሐንጋሪ በ10 ነጥብ ትመራለች፣ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፏንም ከወዲሁ አረጋግጣለች። ጣሊያን በ10፣ ጀርመን በ6 ነጥብ ይከተላሉ። በ2 ነጥብ ብቻ የተወሰነችው እንግሊዝ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ትገኛለች። እንግሊዝ፦ በዘንድሮው የኔሽን ሊግ ፉክክር በጣሊያን 1 ለ0፤ በሐንጋሪ በመጀመሪያው 1 ለ0 ከዚያም በመልሱ ግጥሚያ 4 ለ0 ተሸንፋለች። ከጣሊያን ጋር በነበራት የመጀመሪያ ግጥሚያ ያለምንም ግብ ተለያይታለች። ከጀርመን ጋር ደግሞ አንድ እኩል ወጥታለች። እንግሊዝ ዛሬ ማታ ከጀርመን ጋር የምታደርገው ግጥሚያ የሞት ሽረት ነው። 

እንግሊዝ በጣሊያን 1 ለ0 በተሸነፈችበት ዕለት ባለፈው ዐርብ ጀርመንም በሐንጋሪ ተመሳሳይ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ከሐንጋሪ ጋር በመጀመሪያው ግጥሚያ ጀርመን አንድ እኩል ነበር የወጣው። ጀርመን ከእንግሊዝ ከጣሊያን እና ከሐንጋሪም ጋር ቀደም ሲል ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ያጠናቀቀው በአንድ እኩል ውጤት ነው። ከዚያ ውጪ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በሐንጋሪ የ1 ለ0 ሽንፈት ሲገጥመው፤ ጣሊያንን 5 ለ2 ያንኮታኮተበት ድሉም ይጠቀስለታል። 

Fussball-Länderspiel | Deutschland - Ungarn
ምስል Robert Michael/dpa/picture alliance

የዓምናው ኔሽንስ ሊግ አሸናፊ ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ዳግም መሸነፏ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ካታር የምታዘጋጀው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ 55 ቀናት ብቻ ቀርተውታል። በመጨረሻ የኔሺን ሊግ ግጥሚያዋ ፈረንሳይ ትናንት በዴንማርክ የ2 ለ0 ሽንፈት ነው የገጠማት። 

በአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ ደንብ መሰረት በሊግ ኤ አራት ምድብ የተደለደሉ አራት ምርጥ ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፉ ፉክክር ያልፋሉ። አራቱ ምርጥ ቡድኖች ለጥሎ ማለፉ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ለኔሽን ሊግ ጥሎ ማለፍ ፉክክር ማለፋቸውን ያረጋገጡት ቡድኖች፦ ክሮሺያ፤ ፖርቹጋል፤ ሐንጋሪ እና ኔዘርላንድ ናቸው።  በነገው ዕለት፦ ፖርቹጋል ከስፔን፤ ስዊትዘርላንድ ከቼክ ሪፐብሊክ፤ አየርላንድ ከአርሜኒያ፤ ዩክሬን ከስኮትላንድ፤ አልባኒያ ከአይስላንድ፤ ኖርዌይ ከሠርቢያ፤ ስዊድን ከስሎቬኒያ፤ ግሪክ ከሰሜን አይርላንድ እንዲሁም ኮሶቮ ከቆጵሮስ ጋር ይጫወታሉ።

የተጨዋቾች ውልና የዝውውር ዜና
ማንቸስተር ሲቲ አማካዩ ፊል ፎዴንን በ78 ሚሊዮን ፓውንድ ለስድስት ዓመት ውል ማስፈረም መስማማቱን የቡድኑ ውስጥ አዋቂዎች ይፋ አድርገዋል። ይህ ከፍተኛ ውል ለ22 ዓመቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካይ በሳምንት የ250,000 ፓውንድ ክፍያንም ያካትታል ተብሏል። በዚህ ክፍያም ፊል ፎዴን የሚያገኘው ከኬቪን ደ ብሩዬነ እና ኧርሊንግ ኦላንድ ጋር ያቀራርበዋል። በማንቸስተር ሲቲ የወጣቶች የስፖርት አካዳሚ ተኮትኩቶ ያደገው ፊል ፎዴን በቡድኑ ፈጣን ለውጥ እና እድገት ካስመዘገቡ ተጨዋቾች መካከል ዋነኛው ነው።

RB Leipzig - Manchester City | Fußball Champions League
ምስል Annegret Hilse/Reuters

በሌላ በኩል ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ማርኩስ ራሽፎርድን የረዥም ጊዜ ውል ለማስፈረም ላይ እታች እያለ መሆኑ ተሰምቷል። ማርኩስ ራሽፎርድ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የገባው ውል በዚህ የጨዋታ ዘመን ይገባደዳል። እስካሁን ድረስ ግን የማንቸስተር ዩናይትድ ኃላፊዎች የ24 ዓመቱ ወጣት አጥቂን የረዥም ጊዜያት ውል ለማስፈረም ማሳመን አልቻሉም። ማንቸስተር ዩናይትድ የረዥም ጊዜ ውል በቶሎ ለማስፈረም ያልቻለው ማርኩስ ራሽፎርድ ከፓሪ ሳን ጃርሞ ጋር የጀመረው ነገር አለ በሚል እንደሆነም አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ታምራት ዲንሳ