የመድሃኒት ጥንቃቄና TB
ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2005በዓለም ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ የTB ህመምተኛ መሆኑን ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም የጤና ድርጅት WHO ያወጣዉ መረጃ ያስረዳል። ከዚህ መካከልም 400 ሺህዎቹ መድሃኒት የተላመደዉ TB ተጠቂዎች ናቸዉ። TB ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ከሰዉ ወደሰዉ በአየር አማካኝነት ይተላለፋል። አብዛኛዉን ጊዜ ሳንባን በመጉዳት የሚታወቀዉ ይህ በሽታ አንጎልና ኩላሊትን ጨምሮ ሌሎች የአካል ክፍሎችንም ይጎዳል። በTB በሽታም በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህይወቱን ያጣል። ለበሽታዉ የሚሰጠዉን ህክምና በአግባቡ ባለመከታተልና ተገቢዉን መድሃኒት በሀኪም ትዕዛዝ መሠረት ባለመዉሰድ በሽታዉ ዓይነቱን ቀይሮና አጠናክሮ መድሃኒት ተላምዶ ዛሬ ከፍተኛ እና አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ እየተነገረዉ።
በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተዉ ደረጃዉን ያልጠበቀ ወይም የሀሰት የTB መድሃኒት የአዳጊ ሀገሮችን የTB ታማሚዎች ችግር እያወሳሰበ ነዉ። በ17 ሀገሮች በ19 ከተሞች ዉስጥ የተካሄደዉ ሙከራና ፍተሻ ያሳያየዉ መድሃኒቶቹ አንድም ተገቢዉ የንጥረ ነገሮች ቅምር ዉጤት አይደሉም፤ አንድም በተገቢዉ ፍጥነት በዉሃ አማካኝነት ዉስጣቸዉ ያለዉ ንጥረነገር አይሰባበርም። ይህ የሀሰት አለያም ደረጃዉን ያልጠበቀ መድሃኒት ተገኘ ከተባለባቸዉ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ናት፤ ዶክተር አንዳርጋቸዉ ግን ይህ በስህተት የተጠቀሰ ሳይሆን እንዳልቀረ ነዉ የሚናገሩት።
የተሳሳተ መድሃኒት መዉሰድ፤ ወይም የታዘዘ መድሃኒትን በአግባቡ አለመከታተል መድሃኒትን ለሚቋቋመዉ የTB ዓይነት እንደሚያጋልጥ ነዉ የሚገለፀዉ። በዓለም በተለይም በአዳጊ ሀገሮች በመስፋፋት ላይ የሚገኘዉ ይኸዉ መድሃኒት የተላመደ TB ነዉ።
መድሃኒት የተላመደዉ TB እጅግ የተስፋፋባቸዉ በዓለም 27 ሀገሮች ሲሆኑ አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ዶክተር አንዳርጋቸዉ እንደሚሉት በሽታዉ የሚያስከትለዉን የጤና እክል ለመከላከል ዋነኛ ችግር የሆነዉ መድሃኒቱን ጀምረዉ የሚያቋርጡ ህሙማን መበራከት ነዉ። መድሃኒት የተላመደዉ TBም እንዲሁ በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ ሁኔታዉን ያከብደዋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ በየዓመቱ ወደአንድ መቶ ሃምሳ ሺ ሰዉ በምርመራ የTB ህመምተኛ መሆኑ ይረጋገጣል። ከእነዚህ መካከልም ወደሁለት ተኩል ወይም ሶስት በመቶ ገደማ የሚሆኑት ህክምናቸዉን በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚቋርጡ ባለሙያዉ አመልክተዋል።
መድሃኒት የተላመደዉ TB በአንድ ዓይነት ደረጃ ላይ ብቻ የሚገታ እንዳልሆነ ነዉ ትናንት የዓለም TB ቀን ሲታሰብ ባለሙያዎች ይፋ ያደረጉት። በከፍተኛ ደረጃ የተፈረጀዉ መድሃኒት የተላመደ TB ህመምተኞች የትኛዉም ዓይነት መድሃኒት ቢሰጣቸዉ ዉጤት እንደማያሳይ ነዉ የተገለፀዉ።
እንዲህ ያለዉ TB 82 ሀገሮች ዉስጥ ተገኝቷል። ዓለም ለዚህ ችግር ትኩረት በመስጠት የተሻለ መድሃኒት የሚገኝበትን ምርምር እንዲያበረታታ፤ ፈጣንና ዘመናዊ የምርመራ ስልቶችም እንዲስፋፉ በቂ ገንዘብ መመደብ እንደሚኖርበት ተጠይቋል። በአዉሮጳና በማዕከላዊ እስያ በተካሄደ ምርመራ ከተገኘዉ የTB ህመምተኛ መካከል 30 በመቶዉ ለዚህ መጋለጡ ተረጋግጧል። እሁድ ዕለት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለTB በሽታ ህክምና ትኩረት እንዲሰጥ ሲጠየቅ፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ መስኮት በመክፈት ንፁህ አየር እንዲገኝ በማድረግ የTBን መተላለፍ ለመግታት ምክሩ የሚል መልዕክት አድርሳለች።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ