1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 04 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2013

የደቡብ ሱዳን የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያ በሉሲዎቹ የ11 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሟታል።

https://p.dw.com/p/3rtfQ
Fußball Champions League | FC Bayern - Paris Saint-Germain
ምስል Christof Stache/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የደቡብ ሱዳን የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያ በሉሲዎቹ የ11 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሟታል። 7 ግቦችን አከታትላ ከመረብ ያሳረፈችውን ግብ አዳኚት አነጋግረናል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ሻልከ ከበርካታ ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸንፏል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከ28 ጨዋታ ሲያሸንፍ የትናንቱ ኹለተኛው ነው። ሻልከ አውግስቡርግን ያሸነፈው 1 ለ0 ነበር። እንደሻልከ ኮሎኝም ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን የማሽቆልቆል መከራ ተጋርጦበታል። ባየር ሙይንሽን በዝቅተኛ ቡድን አቻ መውጣቱ አስደምሟል። ነገ በሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ ጋር ያደርጋል። ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ከሁለት ግብ በላይ የግድ ማግባት ይጠበቅበታል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለቀጣይ የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማስጠበቅ የሚደረገው ፉክክር ተጠናክሯል። ቶትንሀም እና ሊቨርፑል አንገት ላንገት ተናንቀዋል። ቸልሲ፣ ዌስትሀም እና ላይስተር ሲቲም ተረጋግተው በፕሬሚየር ሊጉ መቆየት እንዳይችሉ ሌሎቹ በቅርብ ርቀት እየተከተሏቸው ነው።  

Fußball Champions League | Borussia Dortmund - Manchester City
ምስል Michael Regan/Getty Images

ሻምፒዮንስ ሊግ

በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ወሳኝ የመልስ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በመጀመሪያው ጨዋታ በፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ 3 ለ2 የተሸነፈው ባየር ሙይንሽን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሁለት በላይ ግቦችን ማስቆጠር አለበት።  በነገው ዕለት የእንግሊዙ ቸልሲ ከፖርቹጋሉ ፖርቶ ጋር የሚገጥመው በተመሳሳይ ሰአት ነው። ከነገ በስትያም ሁለት የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። በስፔኑ ሪያል ማድሪድ የ3 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ማንቸስተር ሲቲ ወደ ዶርትሙንድ አቅንቶ ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ውስጥ ዶርትሙንድን ይገጥማል። በመጀመሪያው ዙር ውድድር 2 ለ1 በማሸነፉ የተሻለ ዕድል ይዞ ነው ወደ ጀርመን ያቀናው።   

በሻምፒዮንስ ሊጉ በዑኒዮን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ የጣለው መሪው ባየር ሙይንሽን ነገ ፈረንሳይ ውስጥ ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማል።  ባየር ሙይንሽን በቡንደስሊጋው 65 ነጥብ ይዞ በመሪነት ቢገኝም ቅዳሜ ዕለት ነጥብ መጣሉ እንዲሁም የግብ አዳኙ አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በጉዳት አለመሰለፍ ቡድኑ ላይ ብርቱ ተግዳሮት መፍጠሩ አይቀርም።

ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ከደረሰበት ጉዳት በመጠኑ አገግሞ ዛሬ የመጀመሪያ የሩጫ ልምምዱን ማድረጉ ታውቋል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ብሔራዊ ቡድኑ ፖላንድ በነበራት ዓለም አቀፍ ውድድር ወቅት ነው ጉልበቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት። በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ኹለተኛ ዙር ግጥሚያ ላይ ግን መድረስ እንደማይችል ተገልጧል።  የፊት መስመሩን ኤሪክ ማክሲም ቹፖ ሞቲንግ በእነ ኪንግስሌይ ኮማን፣ ቶማስ ሙይለር እና ሌሮይ ሳኔ እየታገዘ እንደሚመራ ይጠበቃል።

Deutschland Bundesliga - Bayern München v VfB Stuttgart | Robert Lewandowski
ምስል Andreas Gebert/REUTERS

ፓሪ ሳንጃርሞ ቀደም ሲል በነበረው ግጥሚያ 3 ለ2 ማሸነፉ ለባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ሐንሲ ዲተር ፍሊክ የመልሱ ግጥሚያ ከባድ ፈተና ነው የሚኾንባቸው። ፓሪ ሳንጃርሞ በፈረንሳይ ሊግ ኦ ፓሪስ ሳን ጃርሞ ቅዳሜ ዕለት ስትራስቦርግን 4 ለ1 አንኮታኩቷል። ቀዳሚዋን ግብ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ኬሊያን እምባፔ ነበር። ፓሪ ሳንጃርሞ በሊጉ ከሊል በ3 ነጥብ ተበልጦ የኹለተኛ ደረጃን ይዟል። 66 ነጥብ አለው።

ባለፈው የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ፓሪ ሳንጃርሞ ወሳኙን ድል ባየርን ሙይንሽን ላይ እንዲቀዳጅ ያደረገው አጥቂው የ22 ዓመቱ ኬሊያን እማባፔ በነገው ግጥሚያ እጅግ ይጠበቃል። እምባፔ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ከፓሪ ሳን ጃርሞ መልቀቅ እንደሚሻ እናም ወደ ሪያል ማድሪድ ሊመጣ እንደሚችል የስፔን ጋዜጦች ዘግበዋል። ምናልባትም ወደ ሊቨርፑል አቅንቶ በጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ስር ይኾናል ሲሉ ግምታቸውን የሰጡም አሉ።

በአንጻሩ የ28 ዓመቱ ግብጻዊ አጥቂ ሞሀመድ ሳላኅን ፒኤስጂ እንደሚፈልገው እየተነገረ ነው። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ ለሊቨርፑል ተሰልፎ የሚጫወተው ሞሐመድ ሳላኅ ለሊቨርፑል በ195 ጨዋታዎች 122 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ከሞሐመድ ሳላኅ በተጨማሪ የቶትንሀሙ የ27 ዓመቱ አጥቂ ሐሪ ኬንንም ፓሪ ሳን ጃርሞ ቡድን ለማስመጣት ፍላጎት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶም ወደ ፓሪ ሳንጃርሞ ሊመጣ ነው እየተባለ ነው። ያ የሚኾነው ግን ኬሊያን እምባፔ ወደ ሪያል ማድሪድ ካቀና ነው ተብሏል። ሪያል ማድሪድ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድን ለማስፈረም ዳር ዳር ማለት መጀመሩን ቶክ ስፖርት ዘግቧል።

Fußball Champions League, Achtelfinale I FC Bayern Muenchen vs. Lazio Rom
ምስል Alexander Hassenstein/Getty Images

ፕሬሚየር ሊግ

በፕሬሚየር ሊጉ 74 ነጥብ ይዞ በመሪነት የሚገሰግሰው ማንቸስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን የሚያከናውነው የፊታችን ረቡዕ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በቀዳሚው ግጥሚያ 2 ለ1 በማሸነፉ የመልሱ ግጥሚያ ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ፈተና ነው። በዚያ ላይ ወሳኝ የሚባሉት ተጨዋቾች፦ ማርኮ ሮይስ እና ማትስ ሑመልስ ባለፈው ቅዳሜ ከሽቱትጋርት ጋር በነበረው ግጥሚያ ከሜዳ በጊዜ መውጣታቸው ስጋት አጭሯል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ማትስ ሑመልስ ሕክምና የሚያሻው የጨጓራ መኮማተር ችግር እንደተፈጠረበት ነው። ማርኮ ሮይስ በበኩሉ የሰውነቱ ዝቅተኛ ክፍል ላይ በደረሰበት ጉዳት 70ኛ ደቂቃ ላይ ነበር ቅዳሜ ዕለት ከሜዳ የወጣው። ይኽ ሁሉ ቢደማመርም አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚች የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በቸልሲ እና ፖርቶ ግጥሚያ ጀርመናዊው የቸልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል ከዲዬጎ ኮስታ ይልቅ ካይ ሐቫርትስን እንደሚያስቀድሙ ይፋ አድርገዋል።  ቸልሲ ክሪስታል ፓላስን  ቅዳሜ 4 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያ ካይ ሐቫርትስ አንድ ግብ አግቦቶ አንድ ኳስ ለግብ አመቻችቷል። በሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ፖርቶን 2 ለ0 ሲያሸንፉ የካይ ሐቫርትስ አቋም አመርቂ አልነበረም። በዚህም ተተችቶ ነበር።

ሉሲዎቹ

የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ባደረጉት የወዳጅነት ግጥሚያ ደቡብ ሱዳንን 11 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርገዋል። ውድድሩ ከትናንት በስትያ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት 81ኛው ደቂቃ ላይ ሳይጠናቀቅ ከመደበኛው ቀሪ 9 ደቂቃዎች የተጠናቀቁት ትናንት ነበር። የትናንቱ 2 ግቦችን ጨምሮ ሉሲዎቹ በአጠቃላይ 11 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል። የደቡብ ሱዳን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር ቡድኑ ዓለም አቀፍ ግጥሚያ ሲያደርግ የኢትዮጵያው የመጀመሪያው መኾኑን ዐሳውቋል። በሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያ ከተቆጠሩ 11 ግቦች 7ቱን ከመረብ ያሳረፈችውን ሎዛ አበራን ከልልምምድ መልስ ረፍት ልታደርግ ባለችበት ሰአት በስልክ አጠር ያለ ቃለመጠይቅ አድርገንላታል።  በውጤቱ ቡድኑ በአጠቃላይ መደሰቱን ገልጣለች።

Fußball | Premier League | Wolverhampton - Southampton
ምስል Actionplus/picture alliance

የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን 2ኛው የአቋም መለኪያ ጨዋታ በነገው እለት እንደሚካኼድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ዐስታውቋል። ጨዋታ ነገ ሚያዚያ 5 ቀን፣ 2013 ዓም ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት የሚከናወነው በአዲስ አበባ ስታዲየም መኾኑንም ፌዴሬሽኑ ገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ