የሚያዝያ 11 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 11 201312 ቡድኖች ከአውሮጳ እግር ኳስ ተገንጥለው የአውሮጳ ሱፐር ሊግን ለመጀመር መወሰናቸው ውዝግብ ፈጥሯል። የጀርመን ቡድኖች በሱፐር ካፑ አይካፈሉም ተብሏል። በዚሁ አዲስ ውድድር እንደሚሳተፉ ከገለጡ የእንግሊዝ ስድስት ታላላቅ ቡድኖች አንዱ ቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣኙ ሆዜ ሞሪኞን ከ17 ወራት ቆይታ በኋላ አሰናብቷል። በቡንደስሊጋው መሪ የኾነው ባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ አሰናባቱኝ ብለዋል። የባየርን ሙይንሽን ፈላጭ ቆራጭ አንጋፋ ባለሥልጣናት ግን እንዲህ በቀላሉ አይኾንም ብለዋል። ሐንሲ ፍሊክ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝነት ቦታ ላይ ዐይናቸውን ጥለዋል። ኪፕቾጌ ለኦሎምፒክ መዳረሻ የመጨረሻ ውድድሩ በኔዘርላንድ ማራቶን ድል አስመዝግቧል።
ሱፐር ሊግ
የአውሮጳ ሱፐር ሊግ ሊጀመር እንደኾነ 12 ቡድኖች ይፋ አድርገዋል። የጀርመን ቡድኖች ባየርን ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ አዲስ ይቋቋማል በተባለው ውድድር የቀረበላቸውን ጥሪ እስካሁን አልተቀበሉትም። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር «ሱፐር ሊግ» የሚባል ውድድርን እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA)ሐሳቡን «መስገብገብ» ብሎ ሲተቸው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) «ተቀባይነት የሌለው» ብሎታል። የጀርመን እግር ኳስ ደጋፊዎች ስብስብ የሀገራቸው እና የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ውሳኔን ደግፈዋል።
ምንም እንኳን 12ቱ ቡድኖች ከጀርመን ቡድኖች ጥሪ ያስተላለፉት ለባየርን ሙይንሽን እና ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ቢሆንም በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ሁለተኛ የኾነው ላይፕትሲሽ በመሰል ውድድር እንደማይሳተፍ ዐስታውቋል። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት የሻምፒዮንስ ሊግ ላይ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ለውጥ ለማድረግ ይፈልጋል። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊዎችንም ከ32 ወደ 36 ከፍ ማድረግ ይሻል። «የስዊስ ሞዴል» በሚባለው የሻምፒዮንስ ሊግ ለውጥ መሠረት 36 ቡድኖች የሚሳተፉት 12ቱ አፈንጋጭ ቡድኖች በአቋማቸው ጸንተው የአውሮጳ ሱፐር ሊግን ካልጀመሩ ነው።
ሱፐር ሊግን ለማቋቋም 12ቱ ቡድኖች መስማማታቸውን ትናንት ይፋ ማድረጋቸው የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረትን የቀውስ አረንቋ ውስጥ ዘፍቆታል። 12ቱ ቡድኖች፦ ሊቨርፑል፣ ቸልሲ፣ አርሰናል፣ ቶትንሀም ሆትስፐር፤ ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፤ ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ ናቸው። ከእንግሊዝ ስድስት፤ ከስፔን እና ከጣሊያን ከእያንዳንዳቸው ሦስት ቡድኖች ናቸው። በእቅዳቸው መሠረት ሁለቱ የጀርመን ቡድኖች እና የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞን አስገብተው 15 ቡድን ማሰባሰብ ይሻሉ። ከዚያም ወደፊት በሚወጣ መስፈርት ሌሎች አምስት ቡድኖችን ጨምሮ በ20 ቡድኖች ነው ውድድሩን ለማስጀመር የፈለጉት። 20 ቡድኖች ለሁለት ተከፍለው ደርሶ መልስ ይጋጠማሉ። ከእየ ምድቦቹ ሦስቱ ምርጦች ወደ ጥሎ ማለፉ ይሻገራሉ። አራተኛ እና አምስተኛ የወጡት ደግሞ የሩብ ፍጻሜው ሁለቱ ተሳታፊ ቡድኖች ለመሆን ይፎካከራሉ። የጥሎ ማለፉ ውድድር በደርሶ መልስ ይሆንና የፍጻሜ ግጥሚያው ከሁሉም ቡድኖች ውጪ በሆነ ቦታ ይከናወናል እንደእቅዳቸው።
12ቱ ቡድኖች ይህን ይፋ ያደረጉት በኮሮና ወቅት የእንቅስቃሴ ገደብ በመኖሩ ቡድኖች ከፍተኛ ኪሣራ ስለደረሰባቸው እና የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ስለወደቁ እንደኾነ ተገልጧል። 12ቱ መስራች ቡድኖች የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕቅዶቻቸውን ለማደራጀት ይረዳቸው ዘንድ እያንዳንዳቸው $4.2 ቢሊዮን ዶላር ይመደብላቸዋል ተብሏል።
የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ይህን ሐሳብ፦ «ስግብግብነት የወለደው» ብሎታል። ቡድኖቹ በአውሮጳ እና በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ሕግጋት እና ደንቦች ሊመሩ ይገባል ሲልም አስጠንቅቋል። «የሚመለከታቸው ቡድኖች በአውሮጳ የሀገር ውስጥም ኾነ በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳይሳተፉ፤ ተጨዋቾቻቸውም ለሀገራቸው ብሔራዊ ቡድኖች እንዳይሰለፉ ይታገዳሉ» ሲልም ዝቷል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር፣ የስፔን ላ ሊጋ እና የጣሊያን ሴሪ ኣ የሱፐር ሊግ ምሥረታን «በጥቂት ቡድኖች ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ስግብግብ ፕሮጀክት» ሲሉ ኮንነውታል።
ፊፋ በበኩሉ፦ «በብሔራዊ፤ ክፍለ ሀገራዊ አለያም ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የሚከናወን ማንኛውም የእግር ኳስ ጨዋታ የገንዘብ ክፍፍሉ የአለኝታነት፣ አካታችነት፣ አቃፊነት እና እኩልነት መርኆችን ሊያንጸባርቅ ያሻዋል» ብሏል። ከዚህ መርኅ ውጪ ያለውን እንቅስቃሴ ፊፋ «እንደማይቀበለው»ም ዐስታውቋል።
ዛሬ ማታ ሊቨርፑል ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ወሳኝ ጨዋታውን ያከናውናል። ከሻምፒዮንስ ሊግ በሪያል ማድሪድ የደርሶ መልስ 3 ለ1 ውጤት በሩብ ፍጻሜው የተሰናበተው ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ከእንግዲህ መሸነፉ አደጋ ውስጥ ይጥለዋል። በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር ተካፋይ ለመኾን ቀጣይ ጨዋታዎቹን በድል ማጠናቀቅ ይገባዋል። ከምንም በላይ ግን የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ስለ አወዛጋቢው የሻምፒዮንስ ሊግ ለውጥ በዋና ሥራ አስፈጻሚዎቹ በኩል ለመወያየት 9 ሰአታት ሲቀሩት ነበር ትናንት 12ቱ ቡድኖች ስለ ሱፐር ሊግ ይፋ ያደረጉት። እናም ዩኤፋ 12ቱ ቡድኖች ተገንጥለውበትም ቢሆን የሻምፒዮንስ ሊግ ለውጡን ያደርግ ይሆን ወይንስ ይተወው ወደፊት የሚታይ ነው።
አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ለመሰናበት ጥያቄ አቅርበዋል። በአጭር ጊዜያት ድንቅ ድል ያስመዘገቡት የባየርን ሙይንሽን አሠልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ከባየር ሙይንሽን ለምን መልቀቅ ፈለጉ? ባየር ሙይንሽን ለ21 ሰአታት ያህል የቆየ ዝምታውን ትናንት ሰብሯል። በአሰልጣኙ በኩል በአንድ ወገን ብቻ የሚሰጥ አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለው አጠር ባለ መግለጫቸውም ይፋ አድርጓል።
አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ከባየርን ሙይንሽን አሰናብቱን ማለታቸው
አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ቅዳሜ ዕለት ቡድናቸው ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 ካሸነፈ በኋላ በሰጡት አስተያየት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ ከባየር ሙይንሽን ጋራ ያላቸው ግንኙነት እንደሚያከትም ይፋ አድርገዋል። የአሰልጣኝነት ዘመናቸው ግን ገና እስከ ሁለት ዓመት የሚዘልቅ ነው። ቡንደስ ሊጋውም ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ነው የሚጠናቀቀው።
ባየርን ሙይንሽን አጠር ባለው መግለጫው፦ «ባየርን ሙይንሽን ቡድን በሐንሲ ፍሊክ በአንድ ወገን የሚሰጠውን አስተያየት አይቀበልም፤ በስምምነቱ መሰረት ከማይንትስ ጨዋታ በኋላም ንግግሩ ይቀጥላል» ብሏል። ባየርን ሙይንሽን፦ ነገ ከባየር ሌቨርኩሰን፤ ቅዳሜ ደግሞ ከማይንትስ ጋር ይጋጠማል።
አሠልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ዝርዝር ጉዳዩን ከመግለጥ ቢቆጠቡም ከቡድኑ እንዲወጡ ያስወሰናቸው ግን ከባየር ሙይንሽን የቦርድ አባል ሐሳን ሳሊሀምዲች ጋር የገቡት እሰጥ አገባ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ትንሽ ወራት ቆየት ያለ ሲሆን፤ አዲስ ተጨዋቾችን በማስመጣት ጉዳይ መሆኑ ይነገራል። ZDF ቴሌቪዥን ላይ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ አሰልጣኙ የባየርን ሙይንሽን ሊቀ መንበር ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ፣ ፕሬዚደንቱ ሔርበርት ሐይነር እና የቀድሞው የቡድኑ ፕሬዚደንት በአሁኑ ወቅት የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆይኔስን ስም ጠርተው አመስግነዋል። በባየርን ሙይንሽን የአንድ ዓመት ከመንፈቅ ቆይታቸው ያመሰገኗቸውን ሰዎች ስም ሲጠሩ የሐሳን ሳሊሀምዲችን ስም ግን አልጠሩም። ኪከር የተባለው በጀርመንኛ የሚታተመው ታዋቂው የስፖርት መጽሄት በዚሁ የዝውውር ጉዳይ የተከፉት ሐንሲ ፍሊክ ቀደም ሲል በበልግ ወቅት ቡድኑን ጥለው ለመኼድ ጠይቀው ነበር ሲል ጽፏል።
የባየርን ሙይንሽን የቀድሞው አምበል ሎታር ማቴዎስ እሁድ ዕለት፦ «ሌላ ምንም መፍትኄ አልነበረም። አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ሲወተውት ቆይቷል፤ ሰሚ ግን አልነበረውም» ብሏል።
የኪከር መጽሄት እንደጠቆመው ከኾነ፦ ሐንሲ ፍሊክ ቡድናቸው ባየርን ሙይንሽን ከአሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን ጋር በደሞዝ ጉዳይ ሳይቀር ተነጋግሯል ብለው ያምናሉ። የ33 ዓመቱ የላይፕትሲሽ አሰልጣኝ ከቡድናቸው ጋር የገቡት ውል የሚጠናቀቀው ገና ከሁለት ዓመት በኋላ ነው። አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን፦ «ምንም አይነት ንግግርም ኾነ ጥሪ የለም አልነበረም» ሲሉ ትናንት የሐንሲ ፍሊክን ጥርጣሬ አስተባብለዋል። እንዲህ ያለ ነገር ይከሰታል ብለው የሚያስቡት እንዳልኾነም ጠቅሰዋል።
ከጁሊያን ናግልስማን በተጨማሪ የአያክስ አምስተርዳሙ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግም ላይ ዐይኖች ያረፉ ይመስላል። ኤሪክ ቴን ሐግ የባየርን ሙይንሽን ቡድን ተጠባባቂ አሰልጣኝ ነበሩ። ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ከጁሊያን ናግልስማን በሁለተኛነት የሚፈለጉ ናቸው። ከሁለቱ አሰልጣኞች በተጨማሪ የቮልፍስቡርጉ ኦሊቨር ግላስነር እንደሌሎቹ ባይሆንም ሐንሲ ፍሊክን ሊተኩ ይችላሉ የሚሉም አሉ።
ከጁቬንቱስ ቱሪን የተሰናበቱት ማሲሚሊያኖ አሌግሪም ዝግጁ ናቸው። ከእኔ በላይ ላሳር የሚሉት እና ከቶትንሀም ሆትስፐር ከብርቱ ትችት በኋላ ዛሬ የተሰናበቱት ሆዜ ሞሪኝሆን የባየርን ሙይንሽን ፈላጭ ቆራጮች የሚታገሱ አይመስሉም። ስለዚህ እሳቸውን የማስመጣቱ ነገር ብዙም የሚሆን አይመስልም።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከዓመት ከመንፈቅ በፊት ማውሪሲዮ ፖቼቲኖን ከተኩ በኋላ ባለፈው የውድድር ዘመን ቡድኑ ስድስተኛ ኾኖ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ 50 ነጥብ ይዞ ከሊቨርፑል በታች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዛሬ ማታ ከሊድስ ጋር የሚጋጠመው ሊቨርፑል 52 ነጥብ አለው።
ዲተር ሐንሲ ፍሊክ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክፍት ቦታ ስላለ ወደዚያ ማቅናት ይሻሉ። አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ ከቡድኑ እንደሚለቁ ይፋ አድርገዋል። ሐንሲ ፍሊክ ከ2006 እስከ 2014 የዓለም ዋንጫ ድል ድረስ የዮአኺም ሎይቭ ረዳት ነበሩ። ሐንሲ ፍሊክ ባየርን ሙይንሽንን ባለፉት 12 ወራት የስድስት ዋንጫዎች ባለቤት አድርገውታል። በቡንደስሊጋው በሰባት ነጥብ ልዩነት ቡድናቸው መሪ ነው። ላይፕትሲሽ በ61 ነጥብ ይከተለዋል።
የ56 ዓመቱ አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭን የመተካት ከፍተኛ ዕድል አላቸው። የሐንሲ ፍሊክ ውሳኔን ተጨዋቾቹ አሳዝኖናል ብለዋል። ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር፦ «እንደ ቡንድ ለእኛ የሚያሳዝን ነው። በዚያ ላይ ለብዙዎቹ ተጨዋቾች የጠበቁት አልነበረም» ብለዋል። ከሐንሲ ፍሊክ ጋር ባየርን ሙይንሽን ድንቅ ስኬት ማስመዝገቡንም ተናግሯል። «የዓለማችን ምርጥ አሰልጣኝ» ሲልም አወድሷቸዋል።
በዚህም አለበዚያ ቀጣዩን ሐንሲ ፍሊክን የሚተካ አሰልጣኝን ወደ ባየርን ሙይንሽን ለማስመጣት የቡድኑ ፈላጭ ቆራጮች መወሰን አለባቸው። እነሱም፦ ኦሊቨር ካን፣ ሳሊሐምዲች እና ከጀርባ ኾነው ቡድኑን የሚዘውሩት የክብር ፕሬዚደንቱ ዑሊ ሆኔስ ናቸው። የእነዚህ አንጋፋዎች ይኹንታ ያስፈልጋል። ጁሊያን ናግልስማንን ለማስመጣት ከፈለጉ ለላይፕትሲሽ አንድ ሚሊዮን መክፈል ይኖርባቸዋል አሰልጣኙ ውሉን በማፍረሳቸው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተሳካለት ግን የብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊ ኦሊቨር ቤርሆፍ ነው። ቢያንስ የዮአኺም ሎይቭ ተተኪን በቅርቡ ማግኘት እንደሚችሉ ዐውቀዋል።
በ2014 ኦሊቨር ቤርሆፍ እና ሐንሲ ፍሊክ አብረው ሠርተዋል። ፍሊክ ብሔራዊ ቡድኑ እንዳላናገራቸው ገልጠዋል። «የወደፊቱ ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣንነትን በተመለከተም እስካሁን ንግግር የለም» ብለዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ግን እንደማንኛውም አሰልጣኝ እንደ አማራጭ የሚያዩት መኾኑን አልሸሸጉም። የሐንሲ ፍሊክ የረዥም ጊዜ ጓደኛ እና የረጅም ዘመን ባልደረባ ዮአኺም ሎይቭ ራሳቸው እሳቸውን ስለሚተካ አሰልጣኝ ተጠይቀው፦ «ያን ይፈልግ አለያም አይፈልግ ሐንሲ ራሱ መወሰን አለበት» ብለዋል።
አትሌቲክስ
ኬኒያዊው የ36 ዓመቱ አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ለቶኪዮ ማራቶን መዳረሻ ባደረገው የኔዘርላንድ ኤንሼዴ ማራቶን አሸናፊ ኾነ። ባለፈው የለንደን ማራቶን አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠመው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሁለት ሰአት፣ ከአራት ደቂቃ፣ ከ30 ሰከንድ ነው። የሀገሩ ሯጭ ዮናታን ኮሪር በ2 ደቂቃ ከ10 ሰከንዶች ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በሦስተኛነት ያጠናቀቀው የኤርትራው ሯጭ ጎይቶም ክፍሌ ነው። ውድድሩ ከሳምንት በፊት ሐምቡርግ ከተማ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ኾኖም በኮሮና የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ ጀርመን ውስጥ ሊከናወን አልቻለም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ