የሚያዝያ 19 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2012በጀርመን ቡንደስሊጋውን ለማስጀመር ዳር ዳር እየተባለ ነው። ኾኖም የስፖርት ሐኪሞች ተጨዋቾች ወደ ቀድሞ ብቃታቸው ለመመለስ ቢያንስ የአራት ሳምንት ጠንካራ ልምምድ ያሻቸዋል እያሉ ነው። ባየር ሙይንሽን የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ምርጡ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየርን ውል አራዝሞ የሻልከውን ወጣት ግብ ጠባቂም ለማስመጣት ወስኗል። ማኑዌል ኖየር ከወራት በፊት የሻልከው ግብ ጠባቂ ሊመጣ ነው ሲባል ቅሬታ ተሰምቶ ነበር። የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሐምሌ ወር ላይ ዳግም ይጀምራል ተብሏል። ፊፋ በ90 ደቂቃ የእግር ኳስ ግጥሚያ አምስተተጨዋቾች ቅያሪ ሊፈቅድ ነው፤ መደበኛ ጨዋታ ሲራዘም ስድስት ተጨዋቾችን መቀየር ይቻላል ብሏል።
የተለያዩ ሃገራት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዜጎች ጥንቃቄ አድርገው ከቤት ውጪ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ጊዜያዊ መመሪያዎቻቸውን ለዘብ ለማድረግ ዳር ዳር እያሉ ነው። ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም በቀጣይ ሳምንታት ሊጀምሩ እንደሚችሉ ነው የተገለጠው። የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ይበልጥ ጉዳት እንዳያመጣም ውድድሮቹ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መከናወን እንዳለባቸው እየተነገረ ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ቡድኖች ውድድሮችን ዳግም ሲያስጀምሩ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስም የተለያዩ ዕቅዶችን እያስተዋወቊ ነው።
በኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት ምክንያት መጨናነቅ እና ጉዳት እንዳይፈጠር ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ላይ አምስት ተጨዋቾችን መቀየር ማቀዱን ዛሬ ዐስታውቋል። ቀደም ሲል የነበረው በ90 ደቂቃ ሦስት ተጨዋቾችን መቀየር የሚቻልበትን ሕግ በመቀየር መደበኛ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተራዘመ ስድስት ተጨዋቾችን መቀየር እንደሚቻል ነው ፊፋ ያስታወቀው። ዕቅዱ ለቀጣይ አንድ ዓመት ከስምንት ወር በጊዜያዊነት እንደሚያገለግልም ተገልጧል።
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ደግሞ ሰኔ 1 ቀን ዳግም እንጀምር መታቀዱን ቢቢሲ ዛሬ ዘግቧል። አርሰናል እና ብራይተን የእግር ኳስ ቡድኖች ተጨዋቾቻቸው የልምምድ ሜዳዎቻቸውን ለተጨዋቾቻቸው ከወዲሁ ክፍት ማድረጋቸውን ዛሬ ዐሳውቀዋል። ተጨዋቾቹ መለማመድ የሚችሉት ግን በግል ብቻ ነው ተብሏል።
በኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ምክንያት የተቋረጠው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግን ነሐሴ ወር ላይ ለማጠናቀቅም ታቅዷል። በዚያም የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ ዕቅዶች ጋር ለማጣጣም ነው የታሰበው። ይኽን ለማሳካት ታዲያ ሙሉ ልምምዶች ከሰኞ ግንቦት 10 ቀን፣ 2012 አንስቶ ሊጀምሩ ይገባል ተብሏል።
የጣሊያን ሴሪ ኣ በበኩሉ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ይጀምራል በተባለበት ተመሳሳይ ቀን ግንቦት 10 ልምምድ መጀመር እንደሚቻል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንሥትር ጁሴፔ ኮንቴ ዛሬ ዐስታውቀዋል። ከፊታችን ሰኞ አንስቶ ደግሞ ጣሊያን ውስጥ ተጨዋቾች በግል ልምምድ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል። በዚህም መሰረት ለሰባት ሳምንታት ያኽል የተቋረጠው የእግር ኳስ ግጥሚያ ዳግም የሚጀምረው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ይኾናል። በውድድሮቹ ወቅት ግን ስታዲየሞቹ ውስጥ ታዳሚያን መግባት አይችሉም። ከፊታችን ሰኞ አንስቶ ማናቸውም የስፖርት አይነቶች ስለሚጀምሩበት መንገድ የሀገሪቱ የስፖርት ሚንሥትር ቪንሴንትሶ ስፓዳፎራ በትጋት ሠርተው ፍኖተ ካርታ እንዲያበጁ ጠቅላይ ሚንሥትሩ ፈቅደዋል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ተፎካካሪ የኾነው ቬርደር ብሬመን የእግር ኳስ ውድድሮች ዳግም የሚጀምሩ ከኾነ ከብሬመን ከተማ ውጪ ለመጫወት እያሰበበት መኾኑን ዐሳውቋል። ቡድኑ ይኽን ዛሬ ያስታወቀው የብሬመን ግዛት የውስጥ ሚንስትር ዑልሪሽ ማውሬር ብሬመን ቬሰር ስታዲየም ውስጥ በዝግ እግር ኳስ እንዲካሄድ ፈቃደኛ አለመኾናቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው። የቬርደር ብሬመን ሊቀመንበር ክላውስ ፊልብሪ ከራዲዮ ብሬመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ አስፈላጊ ከኾነ ቡድናቸው «አማራጭ ስታዲየሞችን መቃኘት እንደሚገባው» ተናግረዋል።
ቬርደር ብሬመን ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር የመጋቢት መጀመሪያ ሳምንት ላይ በዝግ ስታዲየም ሊያደርግ የነበረውን ግጥሚያ የብሬመን ባለሥልጣናት መከልከላቸው የሚታወስ ነው። በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት መጋቢት ወር ላይ የተቋረጠው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት የንጽህና አጠባበቅ በመታገዝ በዝግ ስታዲየሞች የመጀመር ተስፋ እንዳለው እየተነገረ ነው።
በሌላ ዜና በጀርመን የስፖርት አካዳሚ የስፖርት ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ኢንጎ ፍሮቦይዘ የቡንደስሊጋ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋቾች ለውድድር ለመዘጋጀት ቢያንስ የአራት ሳምንት ስልጠና ያሻቸዋል ብለዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጣ፦ ተጨዋቾቹ ቢያንስ ለአራት ሳምንታ ያኽል ተደጋጋሚ ብርቱ ስልጠና ካልተሰጣቸው ወደ ሜዳ ሲገቡ ድክመት ሊስተዋልባቸው ይችላል። የተቋረጠው የጀርመን ቡንደስሊጋ እግር ኳስ ዳግም መቼ እንደሚጀምር በውል ባይታወቅም የቅዳሜ ሳምንት ግንቦት 1 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ግን ዳግም ማስጀመሪያው ሳይኾን አይቀርም እየተባለ ነው።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ ቡንደስሊጋው ምንም አይነት ጥንቃቄ እንኳን ተደርጎበት መጀመር የለበትም፤ ተጨዋቾችን ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ሲሉ አንድ ጀርመናዊ የተሐዋሲያን ጥናት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተናግረዋል። ነዋሪነታቸውን ላይፕሲሽ ውስጥ ያደረጉት ፕሮፌሰር ዑቬ ጂ ሊይበርት ሚተልዶቸ ለተሰኘው ጋዜጣ ዛሬ እንደተናገሩት፦ ምንም እንኳን በባዶ ስታዲየሞች ብርቱ የንጽህና አጠባበቅ ተደርጎ እንኳን ጨዋታው ቢከናወን በቂ አይደለም። «በኮቪድ 19 የተነሳ የሚፈጠረው ኅመም ተጽእኖው ምን ያኽል ዐናውቅም» ብለዋል። «ገና በለጋ ወጣትነት በጸና መታመም ወይንም መሞት ሊኖር ይችላል ብለዋል» የተሐዋሲውን ግራ አጋቢነት በመጥቀስ። የበሽታው አንዳችም ምልክት ሳያሳይ በኮቪድ 19 ለኅልፈተ ሕይወት ስለተዳረገ የ31 ዓመት ወጣት በማውሳትም አስጠንቅቀዋል። በላይፕሲሽ ዩኒቨርሲቲ የተሐዋሲ ጥናት ክፍል ኃላፊው ፕሮፌሰር ቡንደስሊጋው በኮሮና ተሐዋሲ የሚጠቊ ተጨዋቾች ካሉ ለኹለት ሳምንት ለይቼ አስቀምጣላሁ ማለቱም የተሳሳተ ነው ብለዋል።
የባየር ሙይንሽን የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ የቡድናቸው የረዥም ጊዜ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ውል እንዲራዘም እንዲሁም የአዲሱ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኑይበል ዝውውር እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፉ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር ውል የተራዘመው ለአንድ ዓመት ያኽል ነው።
በአሌክሳንደር መምጣት ዜና በወቅቱ ማኑዌል ኖየር ደስተኛ እንዳልነበረም ተዘግቦ ነበር። ዘንድሮ የባየር ሙይንሽን አመራር አባል የኾነው ኦሊቨር ካን ከኹለት ወር ቢፊት በቴሌቪዥን የእግር ኳስ ሥርጭት ትንተና ወቅት ስለ ሻልከው ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኑይብልን የሰጠው አስተያየት መነጋገሪያ ኾኖም ነበር።
አሌክሳንደር ኑይንብል ወደ ባየር ሙይንሽን የመምጣቱ ነገር እርግጥ ከኾነበት ጊዜ አንስቶ ማኑዌል ኖየር ከቡድኑ ጋር ስለሚቆይበት ኹኔታ ሲነጋገር ነበር። የቡድኑ የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ ኪከር ከተሰኘው በጀርመንኛ የሚታተም መጽሄት ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ «ማኑዌል ኖየር በሚቀጥለው ዓመትም በባየር ሙይንሽን ቢቆይ በደስታ ነው የምቀበለው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም እንደነበረው አኹንም ምርጡ የዓለማችን ግብ ጠባቂ ነውና» ብለዋል። አያይዘውም፦ «በዛው ልክ ታዲያ አሌክሳንደር ኑይብልን ለማስመጣት የተወጣነው ተግባር መቶ በመቶ ልክ ነው» ሲሉ አክለዋል።
ጥር ወር መንደርደሪያ ላይ ባየርን ሙይሽን የ23 ዓመቱ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደርን በበጋው ወራት የ5 ዓመት ውል እንደሚያስፈርመው በገለጠበት ወቅት ማኑዌል ምንጊዜም የቡድኑ ዋና ግብ ጠባቂ ኾኖ መቆየት እንደሚሻ ተናግሮ ነበር።
የታላቊ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በኮሮና ወቅት ሰዉ እቤት ውስጥ በሚቆይበት ወቅት የሰውነት ማጎልመሻ እንዲሠራ በኢሜል የቪዲዮ ማገኛኛ ልኳል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እቤት ውስጥ ከተቻለ በየቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ያኽል መሥራት እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎቹን በቪዲዮ አስደግፎ አቅርቧል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴው እቤት ውስጥ ብዙም ቦታ ሳያስፈልግ በቀላሉ መሥራት የሚቻል ነው። ቪዲዮውን የታላቊ ሩጫ በኢትዮጵያ በቴሌግራም እና ዩቲዩብ ላይ አስፍሮታል። በተቻለ አጋጣሚ ማናቸውንም መንገዶች በመጠቀም እቤት ውስጥ በምትቆዩበት ወቅት አካላዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ እናበረታታለን።
የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሰኔ 28 ቀን፣ 2012 ዓ.ም አውስትሪያ ውስጥ ዳግም ይጀምራል ተባለ። የፎርሙላ አንድ ውድድር ኃላፊ ቻዜ ካሪ የፈረንሳይ የፍጻሜ ሽቅድምድም ከተሰረዘ እና የብሪታንያው ከተከለከለ በኋላ አውስትሪያ እንደሚጀምር የተናገሩት ዛሬ ነው። የፈረንሳይ የፍጻሜ ሽቅድምድም ሊካሄድ የነበረው በሰኔ 21 ቀን ነበር። በውድድር ዘመኑ ከተሰረዙ አለያም ለሌላ ጊዜ ከተላለፉ ፉክክሮች የፈረንሳዩ ዐሥረኛው ነበር። ቀሪ ውድድሮች ጥቅምት እና ኅዳር ወር ላይ ተከናውነው ከታኅሣስ ወር የባሕሪን ሽቅድምድም በኋላ እንደተለመደው ፍጻሜውን አቡዳቢ ውስጥ ለማድረግም ታቅዷል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ