የሚያዝያ 5 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2012ለመኾኑ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ከአንድ ሜትር ከግማሽ እስከ ኹለት ሜትር ርቀት በኮሮና ተሐዋሲ ላለመጠቃት በቂ ነው? በቅርቡ የተደረገ ጥናት በቂ ቅንዳልኾነ ነው የሚናገረው። ብስክሌት መጋለብም ኾነ በጎዳና ላይ መሮጥ በኹለት ሜትር ርቀት ልዩነት ከተከወነ ተሐዋሲውን የያዘው ከሰውነት የሚወጣው ርጥብ ፈሳሽ ወደ መሬት ሳይወርድ ወደ ጤነኛው ሰው ሊተላለፍ ይችላል። በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ርቀቱ ምን ያኽል መኾን አለበት? ምን አይነትስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል?
ኮሮና እና ስፖርት
ኮሮና ተሐዋሲ ላይ የተደረገ አዲስ ጥናት፦ ተሐዋሲው ከአንዱ ወደ አንዱ እንዳይተላለፍ በስፖርተኞች መካከል የኹለት ሜትር ርቀት ብቻ አይበቃም ብሏል። በኹለት ሜትር ርቀት ተሐዋሲው ካለበት ሰው አፍ እና አፍንጫ በትንፋሽ ወቅት የሚወጡ ፈሳሾች ጤነኛውን ሰው ሊያጠቊ እንደሚችሉ ጥናቱ ጠቅሷል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሳርስ ኮቪድ 2 ተሐዋሲ ከተጠቃ ሰው የሚወጡ ረቂቅ ተሐዋሲያን በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ላይ ያርፋሉ። ተሐዋሲው ያለበት ፈሳሽ አለያም ርጥበት ወደ መተንፈሻ አካላቸው እንዳይገባ ለመከላከል ሰዎች ከአንድ ተኩል እስከ ኹለት ሜትር ርቀት ጠብቀው መጓዝ እንዳለባቸው ይመከራል። በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ይኽ ርቀት በእርግጥ በቂ ነው? የሎይቨን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቤርት ብሮከን ያን ለመመለስ ጥናት ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
«በጥናታችን ወቅት የተመለከትነው፦ ሰዎች ቆመው ሲያወሩ 1 ነጥብ 5 ሜትር ይጠብቁ የተባለው ርቀት ሲንቀሳቀሱ ማለትም ሲራመዱ፤ ሲሮጡ እና ብስክሌት ሲጋልቡ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ነው። በእንቅስቃሴ ወቅት የሚቀዝፉት አየር ችግርን ነው ያጤንነው።»
በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ሰዉ ተረጋግቶ ሳይኾን የሚጓዘው ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። እናም በተባለው ርቀት በተሐዋሲው ላለመያዝ ርቀቱ ምን ያኽል መኾን ይገባዋል በሚል ባለሞያዎች እየተወያዩ ነው። በተለይ ጀርመን ውስጥ ሰዎች ከኹለት በላይ ሳይኾኑ ወደ የጎዳናዎቹ ወጥተው ስፖርት በጋራ መሥራት ይፈቀድላቸዋል። ቤልጂየም ሎይቨን ከተማ ውስጥ የሚገኘው የሎይቨን ዩኒቨርሲቲ እና የኔዘርላንዱ አይንድሆቨን ዩኒቨርሲቲ በጋራ ይዘው ብቅ ያሉት ይኽ ጥናት እንደሚለው የተባለው ርቀት በምናደርገው እንቅስቃሴ አንጻር ሊቃኝ ይገባል።
«በዚህ የአንድ ነጥብ ከግማሽ ሜትር ርቀት ውስጥ ሰዎች ቆመው ሲያወሩ ተሐዋሲው ካለበት ሰው በመተንፈስ፤ በማስነጠስ ወይን በማሳል የሚወጣው ፈሳሽ ሌላኛው ሰው ጋር አይደርስም። ኾኖም ተሐዋሲው ካለበት ሰው ኋላ የምትራመዱ ከኾነ እና ከፊት ያለው ሰው ካስነጠሰ ወይንም ካሳለ ከአፍና አፍንጫው የሚወጣው ደመናማ ፍሳሽ ወደ መሬት ከመውረዱ በፊት ወደዚያ ደመና ውስጥ ትገባላችሁ ማለት ነው። ይኽም ማለት በፍጥነት የምትጓዙ ከኾነ በማስነጠስ፤ በመተንፈስ ወይንም በማሳል አይር ላይ ወደተንሳፈፈው ርጥብ ደማና በፍጥነት ትገባላችሁ። በዚያም መጠኑ ከፍ ያለ ከሌላ ሰው የተተነፈሰ ርጥብ ደመናማ አየር ስባችሁ ወደሰውነታችሁ ታስገባላችሁ።»
በፕሮፌሰር ቤርት ብሎከን መሪነት ጥናቱን የሚያካሂደው የኹለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ቡድን ይዞት የመጣው አዲስ ግኝት የበርካቶች መወያያ ኾኗል። የጥናት ቡድኑ በተለያየ ፍጥነት እና በተለያየ እንቅስቃሴ ወቅት ከአፍ እና አፍንጫ ስለሚወጡ ፈሳሾች ነው ጥናቱን ያከናወነው። በርምጃ እና በሩጫ ወቅት ስለሚወጡ ፈሳሾች እና አብረው ስለሚሮጡ ሰዎች የተለያዩ ጥናቶችን አከናውነዋል። ከኋላ፤ ከጎን በሰያፍ አቅጣጫ ተጠጋግተው ወይንም ተራርቀው ስለሚሮጡ ወይንም ስለሚራመዱ ሰዎች ነው ጥናቱ የተከናወነው።
«ተሐዋሲውን ከርጥብ ደመናው ላለመሳብ ስታወሩ የአንድ ነጥብ ከግማሽ ሜትሩን ጠብቊ። ርጥባማ ደመናው አየር ላይ ፊታችሁን እንዳያገኘው ከሰው ኋላ ስትራመዱ ከአራት እስከ አምስት ሜትር ርቀት ጠብቊ። እናም ስትቆሙ በጠበቃችሁት የአንድ ነጥብ ከግማሽ ሜትር ርቀት ልክ ውጤት ይኖረዋል። ስለዚህ በእንቅስቃሴ ወቅት ስለሚቀዘፈው አየር ሲቆም ከተባለው የአንድ ሜትር ከግማሹ አንጻር ማጤን ያሻል።»
በጥናቱ መሠረት፦ በዝግታ ብስክሌት በሚጋለብበት ወይ በሶምሶማ ሩጫ ወቅት ደግሞ በተሐዋሲው ላለመጠቃት ቢያንስ የ10 ሜትር ርቀት ያስፈልጋል። ፈጣን እንቅስቃሴ በሚያሻ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ቢያንስ የ20 ሜትር ርቀት ወሳኝ ነው ተብሏል። ምክንያቱም በዚያ ፈጣን እንቅስቃሴ ወቅት መጠነ ሰፊ ተሐዋሲያንን በአተነፋፈስ ወቅት አብሮ ወደ ውስጥ ሊሳብ ይችላል ይላል ጥናቱ። ተመራማሪዎቹ ጥናታቸውን ሲያጠቃልሉ ቆማችሁ ስታወሩ ከአንድ ነጥብ አምስት ሜትር እስከ ኹለት ሜትር ራቊ፤ እንቅስቃሴ ላይ ከኾናችሁ ከአራት እስከ አምስት ሜትር ጠብቊ ይላል። ወደ ውጪ ተወጥቶ ለብቻ ከሰው ጋር ከኾነ ለኹለት ከዚያ ሳይበልጥ አየር መውሰዱንም አበረታትተዋል።
ሌሎች ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በተዘጋ ቤት ወይንም አዳራሽ ውስጥ መስኮቶች ሳይከፈቱ መተፋፈግ ተሐዋሲው ያለበት ርጥብ ደመና አየር ላይ ተንሳፎ ጤነኛውን ሰው ሊያጠቃ እንደሚችል ያመላክታሉ። ስለዚህም በተደጋጋሚ ጊዜ የቤትም ኾነ የታክሲ ወይንም የአውቶቡስ መስኮቶችን እየከፈቱ ማናፈስ ይጠቅማል።
ከዚሁ ከኮሮና ተሐዋሲ ጋር በተገናኘ የፈረንሳይ የጁዶ ባለድል የነበረው የ37 ዓመቱ ተፋላሚ ሲሪል ቡላንዠር ባለፈው ሳምንት ሕይወቱ ማለፉ ተገልጧል። ፈረንሳዊው የጁዶ ተፋላሚ የኮቪድ 19 ሰለባ የኾነው ባለፈው ሳምንት እሁድ ነበር። ሲሪል ከ19 ዓመት በፊት ለስድስት ዓመት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችም ነበር። የኹለት ልጆች አባቱ ፈረንሳዊ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በኮሮና ተሐዋሲ ከተጠቃ በኋላ በጠና ታሞ በቆየበት ሊል ዩኒቨርሲቲ ሐኪም ቤት ውስጥ ነው። ሲሪል ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ የባቡር አገልግሎት የደኅንነት ሠራተኛም ነበር። ባለፈው ዓመት የብራዚላውያን ጂ ጂትሱ ትግል ፍልሚያ ማሰልጠንም ጀምሮ ነበር።
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም «ዘውድ ያልደፋው ባለድል» የሚል ቅጽል የተሰጠው ብሪታንያዊ አሽከርካሪ በ90 ዓመቱ አርፏል። ሰር ስቲርሊንግ ሞስ 16 ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ላይ ተሳታፊ ኾኖ ለአራት ጊዜያት ኹለተኛ ለሦስት ጊዜያት ሦስተኛ በመውጣት ይታወቃል። አንድም ጊዜ በዓለም የመኪና ሽቅድምድም ፉክክር አንደኛ ወጥቶ ግን ዐያውቅም።
የዝውውር ዜና
የቦሩስያ ዶርትሙንድ እግር ኳስ ቡድን የክንፍ ተጨዋች ጃዶን ሳንቾ ወደ ቸልሲ ለመሄድ ፍላጎት እንደሌለው የስፔኑ ዲያሪዮ ማድሪዲስታ ጋዜጣ ዘግቧል። ያም በመኾኑ እንግሊዛዊው የ20 ዓመት የክንፍ ተጨዋች ምናልባት ወደ ሪያል ማድሪድ ወይንም ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ያቀናል ተብሏል። በተለይ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የመዛወሩ ነገር የጎላ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር ከባልደረቦቻቸው ጋር ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን በማፈላለግ ገበያውን እያጠኑ መኾናቸውን ገልጠዋል። ሳንቾ የዶርትሙንድን ስታዲየም ለቆ የሚሄድ ከኾነ፦ የእነ ኦስማኔ ዴምቤሌ፤ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ፤ ክርስቲያን ፑሊሲች እና ሌሎችን ፈለግ ይከተላል ማለት ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ