1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 9 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2015

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ዋንጫ የማግኝት ሰፊ እድሉን እያጠበበ ነው ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተን በስምምነት ማሰናበቱን ይፋ አድርጓል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሆላንድ የሮተርዳም ማራቶን ውጤት አልቀናቸውም ። በወንዶች ፉክክር የኤርትራ ሯጭ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል ። ተጨማሪ ዘገባ አካተናል ።

https://p.dw.com/p/4QCOQ
UEFA Champions League | Viertelfinale | AC Mailand gegen Neapel
ምስል Gabriel Bouys/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ዘንድሮ ዋንጫ የማግኝት ሰፊ እድሉን እያጠበበ ነው ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋሊያዎቹን ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ውበቱ አባተን በስምምነት ማሰናበቱን ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ይፋ አድርጓል ።  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሆላንድ የሮተርዳም ማራቶን ውጤት አልቀናቸውም ። በወንዶች ፉክክር የኤርትራ ሯጭ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል ። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ብሪታንያዊው ተፋላሚ ጆ ጆይስ ቀኝ ዐይኑ ተነርቶ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል ።

አትሌቲክስ

ሮተርዳም ኔዘርላንድ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ፉክክር የቤልጂየሙ አትሌት ባሽር አብዲ እና የባሕሬኗ ዩኒስ ቹምባ አሸናፊ ሆነዋል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ውድድር ድል አልቀናቸውም ። በወንዶች ፉክክር፦ የኦሎምፒክ ሩጫ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚው ባሽር አብዲ ያሸነፈው 2:03:47 በመሮጥ ነው ። ያጠናቀቀበት ሰአትም በ2021 ሆላንድ ውስጥ ካሸነፈበት በ11 ሰከንድ የዘገየ ነበር ። ለጥቂት በሁለት ሰከንድ የተበለጠው ኬኒያዊው ቲሞቲ ኪፕላጋት እና ትውልደ ሶማሌያ ሆላንዳዊው አብዲ ናጊዬ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል ።  ኢትዮጵያውያኑዳዊት ወልዴ እና ጫላ ረጋሳ አራተኛ እና አምስተኛ ሲወጡ፤ አስማረ ባዘዘው አበበ ነገዎ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።

አትሌቶች ለመሮጥ ተዘጋጅተው፤ መሮጫው መም ላይ መዳፋቸውን እንዳስደገፉ
አትሌቶች ለመሮጥ ተዘጋጅተው፤ መሮጫው መም ላይ መዳፋቸውን እንዳስደገፉምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

በሴቶች የሮተርዳም ማራቶን የሩጫ ፉክክር የኤርትራው ሯጭ ተስፉ ተክለጊርጊሽ ዶልሺ ለጥቂት በአራት ሰከንዶች ተበልጣ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ዩጋንዳዊቷ ዩኒስ ቹምባ በመሮጥ 2:20:31 አንደኛ ወጥታለች ። የሦስተኛ ደረጃውን የያዘችው ዩጋንዳዊቷ ሮዝ ቼሊሞ ናት ። ኢትዮጵያውያቱ ቲኪ ገላና እና መስከረም አሠፋ ስድስተኛ እና ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ።

እግር ኳስ

በሞሮኮ ቆይታው በጊኒ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ተሸንፎ ለአፍሪቃ ዋንጫ የማለፍ ዕድሉን ያጨለመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአሰልጣኝነት ተሰናብተዋል ። በምድቡ እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሦስት ነጥብ ያላት ማላዊ ቡድንም ቀደም ብሎ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኙን አሰናብቷል ። ከምድቡ አራት ነጥብ ብቻ ይዞ የተመለሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስለ ዝቅተኛ ውጤቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ ከአሠልጣኝነታቸው ይሰናበታሉ ተብሎ በስፋት ተጠብቆ ነበር ። በዕለቱ ያ ሳይሆን ግን ቀርቷል ። ሆኖም ባለፈው ዐርብ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ዐሳውቋል ።

ሁለት የግብ እዳ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመቀጠል ከግብጽ እና ከማላዊ ጋር የመልስ ጨዋታዎች አሉት ። ዋሊያዎቹ ሁለቱን ቀሪ ጨዋታዎች ቢያሸንፉ እንኳን ነጥቡ ከዘጠኝ አይሻገርም ። ግብፅ እና ጊኒ ተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ እንዲሁም አምስት እና ሦስት ግቦች አሏቸው ።  ያም በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ አሁን ተስፋ እጅግ በጣም የመነመነ ነው ።

ከመስከረም 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ውበቱ አባተ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ ፌዴሬሽኑ ዐስታውቋል ። የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የአሰልጣኙን መልቀቂያ እንደተቀበለ፤ ከአሰልጣኙ ጋርም በጋራ ስምምነት እንደተለያየ ገልጧል ።  አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን፤ ቡድኑን ማን ሊያሰለጥነው እንደሆነ ግን አልገለጠም ።
 

ፕሬሚየር ሊግ

የሊቨርፑል ተጨዋች አንድሪው ሮበርትሰን
የሊቨርፑል ተጨዋች አንድሪው ሮበርትሰንምስል Nick Potts/PA Wire/dpa/picture alliance

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጋጠማል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊድስ ዩናይትድ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ዘንድሮ ከተለያዩ የውድድሮች የሆነው ሊቨርፑል ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ44 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን አሸንፎ ወደ አውሮጳ ሊግ ተሳታፊነት ለማለፍ የዛሬም ሆነ ቀጣዩ ተስተካካይ ጨዋታዎች ለሊቨርፑል እጅግ ወሳኝ ናቸው ። ምክንያቱም የአውሮጳ ሊግ 5ኛ ደረጃን የያዘው ቶትንሀም ሆትስፐር ነጥቡ 53 ነው ። ኒውካስል ዩናይትድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ56 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዟል ። ማንቸስተር ዩናይትድም በ30 ጨዋታ 59 ነጥብ ሰብስቦ 3ኛ ደረጃን ይዟል ። በተለይ ባለፈው የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ መደበኛው  የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ሴቪያን 2 ለ0 እየመራ በማጉዬር የ90 ደቂቃ ስህተት ታክሎበት ሁለት እኩል መውጣቱ እና ነጥብ መጣሉ ደጋፊዎቹን እጅግ ያስቆጨ ነበር ። ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 70 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። መሪው አርሰናል ትናንት ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ሁለት እኩል ወጥቶ ነጥብ ጥሏል ። 74 ነጥብ አለው ። የማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴ እጅግ ያሰጋዋል ። ኖቲንግሀም ፎረስት፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳውዝሀምፕተን ከ18ኛ እስከ 20 ደረጃ ላይ ተደርድረዋል ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን በ59 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ57 ይከተላል ። ዑኒዮን ቤርሊን 52 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ላይፕትሲሽ በ52፣ ፍራይቡርግ በ50 እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን በ44 ነጥብ ከ4ኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ተደርድረዋል ። የባየርን ሙይንሽን አጥቂ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ የቡድኑ አጋር ሌሮይ ሳኔን ከንፈሩ ላይ በቡጢ በመማታቱ የገንዘብ እና የጨዋታ ቅጣት ተላልፎበታል ። ከሆፈንሀይም ጋር አንድ እኩል በተለያዩበት ግጥሚያ ሳዲዮ ማኔ አልተሰለፈም ። ሁለቱ ተጨዋቾች በሻምፒዮንስ ሊግ በማንቸስተር ሲቲ የ3 ለ0 ከባድ ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ መልበሻ ክፍል ውስጥ እንደተጨቃጨቁ እና እንደተጣሉ ተዘግቧል ።

በስፔን ላሊጋ ዛሬ ማታ ሴልታ ቪጎ ከማዮካ እንዲሁም በጣሊያን ሴሪኣ ፊዮሬንቲና ከአታላንታ ይጋጠማሉ።

ቱኒዝያ ውስጥ የፖሊስ በደለን በመቃወም ራሱን በእሳት ያቃጠለው ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋች ቀብር ላይ ግጭት ተነሳ ። «የፖሊስ አገዛዝን» በመቃወም ራሱን በእሳት ያጋየው የ35 ዓመቱ የእግር ኳስ ተጨዋች ኒዛር ኢሳዊ ካሪዮን አውራጃ ውስጥ በምትገኘው ሐፎዝ በተባለች መንደር የደረሰበት ሦስተኛ ደረጃ የእሳት አደጋ ቃጠሎ እንደነበር ወንድሙ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግሯል ። ራሱን ያቃጠለውም ከፍራፍሬ ዋጋ ጋር በተያያዘ ከነበረ ጭቅጭቅ በኋላ ፖሊስ «አሸባሪ» ብሎት ስላሰረው እና ፍትኅ ስላጣ መሆኑን ወንድሙ ማኸር ኢሳዊ አክሏል ።

ራሱን በእሳት ላጋየው የ35 ዓመቱ የእግር ኳስ ተጨዋች ኒዛር ኢሳዊ ቀብር የወጡ ተቃዋሚዎች
ራሱን በእሳት ላጋየው የ35 ዓመቱ የእግር ኳስ ተጨዋች ኒዛር ኢሳዊ ቀብር የወጡ ተቃዋሚዎችምስል Kabil Bousena/AFP

«ወንድሜ በአሸባሪነት ነው የተከሰሰው ። ለምን ቢባል? ገበያው ውስጥ ነጋዴውን ሙዝ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለአንድ ትንሽ ልጅ በ10 ዲናር ለምን ትሸጣለህ ስላለ ነው ። ነጋዴው በ5 ዲናር ለልጁ እንዲሸጥለት ናዚር ጠይቆታል ። ለፖሊሱ በሸጡለት ተመሳሳይ ዋጋ ማለት ነው ። ግን ፖሊሶች ወንድሜን ከበውት እሱንም ልጁንም ቀጠቀጧቸው ። ከዚያም ሁሉም ሰው ሊያመለክት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ ።»

ሟቹ ናዚር እና አመልካቾችን ግን ፖሊስ ጣቢያ የገጠማቸው አናዳጅ ነገር ነበር ። ወንድምዬው የሆነውን እንዲህ ያብራራል ።

«ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ምንም ሊሰሙት አልቻሉም ።ፖሊሶቹ ያደምጡ የነበረው ሌላኛውን ወገን ነበር ። አንድም ፖሊስ ሊያደምጠው አልፈለገም ። ኮሚሽነሩም ሆኑ መርማሪው አንዳቸውም አላዳመጡትም ።  እንደውም በአሸባሪነት ነበር የተከሰሰው ።  ለትንሹ ልጅ ስለተቆረቆረ በአሸባሪነት ከሰሱት ።»

ከዚያም ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቹ በንዴት እና «የፖሊስ አገዛዝ» ያለውን በመቃወም መንደር ውስጥ እራሱን ያጣልላል ። ከትንሿ መንደርም የእሳት ቃጠሎ ባለሞያዎች ወደ ሚገኝበት መዲናዪቱ ቱኒስ የሚገኝ አንድ ሐኪም ቤት ቢወሰድም የደረሰበት ሦስተኛ ደረጃ የእሳት ቃጠሎ ብርቱ ስለነበር ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም ። ሐሙስ ዕለት ሕይወቱ ታልፋለች ።

«ለወንድማችን የምንማጸነው ፍትሕ እንዲያገኝ ብቻ ነው ። ሌላ የምንጠይቀው ነገር የለም ። ጸቡን ቀድመው የጀመሩት ባለሱቆቹ እና የጥበቃ ሰዎች ላይ ፍትሕ እንሻለን ።»

የናዚር ኢሳዊ በእሳት ራሱን አቃጥሎ መሞቱ እዛው ቱኒዝያ ውስጥ ከ13 ዓመት በፊት የተከሰተ ተመሳሳይ ድርጊትን አስታውሷል ። ሞሐመድ ቦዋዚዝ የተባለ ፍራፍሬ ነጋዴ ራሱን ማቃጠሉ በወቅቱ የቱኒዝያ «የዓረብ ጸደይ» ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ማድረጉ ይታወሳል ። ተቃውሞውም በቱኒዝያም ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓረብ ሃገራት ተዛምቶ አምባገነን የረዥም ጊዜ መሪዎችን ከሥልጣን አስወግዷል ። የናዚር ኢሳዊ ቀብር ዐርብ ለት ሲፈጸምም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሟቹ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች ደጃፍ ተሰባስበዋል ። እዚያም «በደማችን እና በጽናታችን መስዋእት እንከፍልልሀለን ናዚር»  ሲሉም ፈክረዋል ። ናዚር ራሱን ከማቃጠሉ በፊት በፌስቡክ ላይ የጫነው የቪዲዮ መልእክት በርካቶች ተቀባብለውታል ። በቪዲዮው ላይ ራሱን ከማቃጠሉ አስቀድሞ፦ «የፖሊስ አገዛዝን የመታገሱ አቅም የለኝም» ሲልም ይደመጣል ። የቱኒዝያ መንግሥት በናዚር የእሳት ቃጠሎ ጉዳይ አስተያየት አልሰጠም ።

ራሱን ማቃጠሉ የቱኒዝያን ጨምሮ «የዓረብ ጸደይ» ተቃውሞ ያጫረው ሞሐመድ ቦዋዚዝ ከመሞቱ በፊት በሐኪም ቤት
ራሱን ማቃጠሉ የቱኒዝያን ጨምሮ «የዓረብ ጸደይ» ተቃውሞ ያጫረው ሞሐመድ ቦዋዚዝ ከመሞቱ በፊት በሐኪም ቤትምስል AP

ቡጢ፦

የ37 ዓመቱ ብሪታንያዊ የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ጆ ጆይስ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ለንደን ከተማ ውስጥ አስተናግዷል ። ጆ ቅዳሜ ዕለት በለንደን የኮፐር ቡጤ መድረክ ላይ በዚላይ ዣንግ ቢረታም፦ በቡጢ ስፖርት «ጉዞው እንደሚቀጥልበት» ግን ይፋ አድርጓል ። በዚላይ ተደጋጋሚ ቡጢ ዐይኑ ጠርዝ ላይ የተነረተው ጆ በዳኛ ውሳኔ ስድስተኛው ዙር ላይ ጨዋታውን እንዲያቋርጥ ተደርጓል ።  ጆ ጆይስ ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ መጠይቅ፦ «ሽንፈት ደርሶብኛል፤ ግን እመለሳለሁ» ብሏል ። «ጉዞው ይቀጥላል» ሲልም አክሏል ። ውድድሩ እንዲቋረጥ ከመደረጉ በፊት የጆ ጆይስ የበለዙ ዐይኖች ላይ ዳኛው ለሁለት ጊዜያት ቁጥጥር አድርገዋል ። ቡጢኛው ማየት ስለተሳነውም ዳኛው ፍልሚያው እንዲቆም አድርገዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

እሸቴ በቀለ