የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1 2014
ያገባደድነዉ ሳምንት ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ጉዳዮች የተከወኑበት፣ጀርመን ዉስጥ አዲስ መንግስት የተመሠረተ-ሥልጣን የያዘበትም ነዉ።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ብዙ አስተያየቶችን የሰጡባቸዉን ሁነቶችና ዘገቦችን መርጣን ጎላ-ጎላ ያሉትን ግን ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን መርጠን ባጫጭሩ አናሳማችኋለን።ጥቂት ጠብቁን።
የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር፣የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ሚሊሺያና ፋኖ ደሴ፣ ኮቦልቻና ባቲን የመሳሰሉ ሥልታዊ፣ታሪካዊ፣ የኢንዱስትሪና የንግድ ከተሞችን ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እጅ ማስለቀቃቸዉን የኢትዮጵያ መንግስት ያስታወቀዉ ባለፈዉ ሰኞ ማምሻ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስትን የድል ዜና ጃሕ ማን ጃዚ በአድናቆት ነዉ የተቀበለዉ «ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል» ይላል-ጃሕ በፌስ ቡክ።
ትዕግስት ፈለቀ ግን «አዬ» ትላለች።«ሲጀመር ሴራ ነዉ እንጂ እንዳይገቡ ማድረግ ይቻል ነበር----ሆድ ይፍጀዉ» አበቃች-ትዕግስት።ስንታየሁ መኮንን «4ኪሎ የወሎ "ጭስ" እልክላችሃለሁ» አለ በፌስ ቡክ።Gtz Ethiopia የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ደግሞ «አንሰማችሁም» አለ-ብዙ የሆነ ይመስል።
ከማል ከማል ግን ምክር ብጤ ይለግሳል «እስኪ ሰከን እንበል» እያለ በፌስ ቡክ፣ ቀጠለ «ሰላም ያርድርግልን ይኸ ሁሉ ሰዉ ረግፎ» እያለ
የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ፣የካናዳ፣ የአዉስትሬሊያ፣ የዴንማርክና የኔዘርላንድስ መንግስታት የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ተ,ወላጆችን በዘራቸዉ እየፈረጀ ያስራል መባሉ እንዳሳሰባቸዉ ያስታወቁት በዚሕ ሳምንት ነበር።ሰኞ።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር የፕሬስ ሴክሪተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በማግስቱ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ ወቀሳዉን አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።
ሚኪ ኤልያስ በፌስቡክ የሰጠዉ አስያየት የመንግስትን አቋም ከመጋራትም አልፎ የመታሰር-አለመታሰሩን ሒደት በቅርብ የሚከታተል ሹም ያስመስለዋል።«ትግሬ በመሆኑ የታሠረ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ 1 ሰው የለም» አለ ሚኪ፣ «100%» ብሎም ጨመረበት።
መሉ መሉ ግን (ሴት ትሁን ወንድ አናዉቅም) ይጠይቃል።ያዉ በፌስ ቡክ «ምን ማለት ነዉ?» ብሎ።ቀጠለም «ከዚሕ በላይ ብሔር ተኮር አለ እንዴ?ከየክፍለ ሐገሩ የተወሰዱት ምንድናቸዉ?-----አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ» እያለ።«ወንጀለኛ ብሔር የለዉም፣ የማንንም ብሔር አይወክልም» የሚለዉ ከድር ሁሴይን ነዉ። በፌስ ቡክ «ለወንጀለኛ ድምፅ መሆን የሚፈልጉ ወገኖች ጉዳዩን ከማንነት ጋር ለማገናኘት ይጥራሉ» የከድር ሁሴይን አስተያየት ነዉ።
ደምመላሽ አያሌዉ ደምመላሽ ጉዳዩን ለፈጣሪ መተዉን ነዉ የመረጡት «እግዚአብሔር ይህን ክፉ ዘመን ያሳልፍልን እንጂ ችግሩ ከህዝብ እምነትና አቅም ውጭ ነው» ይላል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ከጦር ግንባር ወደ ቤተ-መንግስታቸዉ መመለሳቸዉን ባለፈዉ ሮብ አስታዉቀዋል።ሁለት ሳምንት ያክል በገፅ ተገኝተዉ ያዋጉት ጦር ያገኘዉን ድል አድንቀዉ የሳቸዉ የግንባር ዘመቻ የመጀመሪያዉ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጠዋል።
ሐና መንግስቱ «ውዱ መሪያችን እንኳን በድል ተመለስክልን!» አለች በፌስ ቡክ።መሳይ አንባዉ ግን «ዕቃ፣ ዕቃ ጨዋታ አደረጉት» ይላል።ሁለቱም በፌስ ቡክ ነዉ።
ሳምራዊት ዳንኤል በፌስ ቡክ ካሰፈረችዉ ሰፊ አስተያየት ፍሬ ሐሳቡን እነሆ «የጥቁር ህዝቦች ልዩ ምልክት የሆነችውን ኢትዮጵያን ነካክተው ድፍን አፍሪቃ በቃን ብሎ ተነስቶባቸዋል!!!ከእንገዲህ ጀግና መሪያችን ላይ ዙሩን እንዳከረራችሁበት እሱም አፍሪካውያንን በማነሳሳት ዙሩን ያከርባቸዋል»
ግዛዉ ከበደ ዋቄ «ጀግና የኛ መሪ» ብሏል ከቃለ አጋኖ ጋር
ወደ ጀርመን እንሻገር።ባለፈዉ መስከረም ጀርመን ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ላቅ ያለ የሕዝብ ድምፅ ያገኙት የሶሻል ዴሞክራቶቹ (SPD)፣ አረንጓዴዎቹ DIE GRÜNEN) እና ነፃ ዴሞክራቶቹ (FDP) ፓርቲዎች የመሰረቱት ተጣማሪ መንግስት ባለፈዉ ሮብ ሥልጣን ተረክቧል።የተጣማሪዉ መንግስት መሪ ኦላፍ ሾልስም የመራሔ መንግስትነቱን ስልጣን ከአንጌላ ሜርክል ተርክበዋል።
በምጣኔ ሐብት ከዓለም አራተኛ ከአዉሮጳ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ የምገኘዉን ጀርመንን ለ16 ዓመታት የመሩት ዶክተር አንጌላ ሜርክል ከመራሔ መንግስትነቱ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካዉም እራሳቸዉን አግልለዋል።የጀርመን የፖለቲካ ሽግግርና የአዲሱ መንግስት መርሕ መሰንበቻዉን ከጀርመን አልፎ የአዉሮጳም የተቀረዉ ዓለምም ትልቅ ርዕስ ሆኗል።
ለቢላል ከዲር ጀማል ግን ዓለም አቀፉ ጉዳይ አይመለከተዉም «በሰው ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንገባም» ይላል ከድር በፌስ ቡክ።ሰዒድ ዓሊ በጀርመንኛ በሰጠዉ አስተያየት «አንጌላ ሜርክል ጥሩ መራሒተ መንግስት ነበሩ» ይልና ለጠቅ አድርጎ «እሳቸዉ (ሾልስን ነዉ) ተመሳሳይ ስራ እንደሚሰሩ ተስፋ አለኝ።ግን SPD እና CDU የተለያየ መርሕ ስለሚከተሉ ጠብቀን ማየቱ ይሻላል» የሰዒድ ዓሊ አስተያየት ነዉ
ኢማ ኪንግ በእንግሊዝኛ---የአዲሱን የጀርመን መራሔ-መግስት «የስደተኛ መርሓቸዉ እንዴት ነዉ?» ብሎ ይጠይቃል።
ገለታዉ ዘለቀ በየነ «ለተከበሩ ኦላፍ ሾልስ መልካም የስራ ዘመን እመኛለሁ። የጀርመንና የኢትዮጵያ ትብብር ያብብ።»
አቤል መስፍን ገብሬ ግን ሥለ ጀርመኖች የስልጣን ሽግግር እንዲሕ አለ በፌስ ቡክ «ቀናሁ።»
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ