1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞዛምቢክ ተቃዋሚ መሪ ማፑቶ መግባት በአገሪቱ ውጥረቱን አባብሷል

ቅዳሜ፣ ጥር 3 2017

ሐሙስ ጥር 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ማፑቶ፤ የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በተኩስ ሩምታ ስትናጥ ውላለች ። ምክንያት? የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ድንገት ወደ ሞዛምቢክ መመለስ ።ከአራት መቶ በላይ ሰዎች የተገደሉባት፤ 1,500 የቆሰሉባት ሞዛምቢክ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወደ ማፑቶ መመለሳቸው ከፍተኛ ውጥረት አንግሷል ።

https://p.dw.com/p/4p2QF
Mosambik Maputo | Ankunft von Oppositionsführer Venancio Mondlane
ምስል Carlos Uqueio/AP Photo/picture alliance

የምርጫ ጣጣ ሞዛምቢክን ዕያወከ ነው

ሐሙስ ጥር 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ማፑቶ፤ የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በተኩስ ሩምታ ስትናጥ ውላለች ። ምክንያት? የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ድንገት ወደ ሞዛምቢክ መመለስ ። በጥቅምቱ የሞዛምቢክ ምርጫ ዋዜማ ብጥብጥ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች የተገደሉባት፤ 1,500 የቆሰሉባት ሞዛምቢክ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወደ ማፑቶ መመለሳቸው ከፍተኛ ውጥረት አንግሷል ። የሞዛምቢክ ፖሊስ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ቬናንሲዮ ሞንድላኔን ለመቀበል ሐሙስ ዕለት አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ጥይት ማዝነቡ ተዘግቧል ። በጥይት ውርጅብኙ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ወዲያው ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውም ተዘግቧል ።

የተቃዋሚው መሪ ቬናንሲዮ ሞንድላኔ በአገሪቱ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን በመግለጥ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉት ሐሙስ  ዕለትም ሞዛምቢክ ውስጥ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ተናግረዋል ። በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የማፑቶ አየር ማረፊያ መሬትን በመሳም ንግግር ያሰሙት ቬናንሲዮ ለሞዛምቢክ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚታገሉ ዐሳውቀዋል ።

ቬናንሲዮ ከሁለት ወራት በፊት ከአገር የሸሹት የቅርብ ሰዎቻቸው ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ለራሳቸው በመሥጋት እንደነበር ተናግረዋል ። በጥቅምቱ ምርጫ ገዥው የፍሬሊሞ ፓርቲ ማሸነፉን የሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ሸንጎ ካረጋገጠ በኋላ በአገሪቱ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር ።  በወቅቱ የተጭበረበረ ሲሉ ታቃዋሚዎች ያወገዙትን የምርጫ ውጤት ከፍተኛ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ቢያጸድቅም ንብረት ማውደም እና ዝርፊያ የተቀላቀሉበት ብጥብጥ ሞዛምቢክን ለወራት ንጧታል

በጥቅምቱ የሞዛምቢክ ምርጫ ዋዜማ ብጥብጥ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች ሲገደሉ 1,500 ቆስለዋል
በጥቅምቱ የሞዛምቢክ ምርጫ ዋዜማ ብጥብጥ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች ሲገደሉ 1,500 ቆስለዋልምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

የተቃዋሚው መሪ አገር ቤት መግባት ያነገሠው ውጥረት

ተቃዋሚዎች እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ውድቅ ያደረጉትን ምርጫ አሸንፌያለሁ ያሉት የፍሬሊሞ ፓርቲ መሪ ዳንኤል ቻፖ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጥር 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በሞዛምቢክ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ ተብሏል ። ከዚያ በፊት ግን ከተቃዋሚዎች ጋር ንግግር እንደሚያደርጉ ዐሳውቀዋል ። ለንግግሩ ይኸው እዚሁ ሞዛምቢክ አለሁ ሲሉ የተቃዋሚ መሪው ቬናንሲዮ ሞንድላኔ ማፑቶ ተገኝተዋል ። ቃል የተገባው ንግግር ላይም ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆናቸውን ዐሳውቀዋል ። የሞዛምቢክ ሕገ መንግሥታዊ ሸንጎ ያለውን ግን ዛሬም ፈጽሞ አይቀበሉትም ።

የጥቅምቱን ምርጫ የገዢው ፍሬሊሞ ፓርቲ ዳንኤል ቻፖ 65 በመቶ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸውን የተቃዋሚው እጩ ተወዳዳሪ ቬናንስዮ ሞንድላኔ ደግሞ 24 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን ነበር ሸንጎው ያሳወቀው ። 33 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት  ሞዛምቢክ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1975 ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ አንስቶ  አገሪቱን የሚያስተዳድረው ይኸው የፍሬሊሞ ፓርቲ ነው ። በቀጣይ ሁለትሳምንታት ጭንቅ ውስጥ በምትገኘው ሞዛምቢክ ምን እንደሚከሰት ዐይታወቅም ። ፍጥጫው ግን እንዳየለ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ