የሣምንቱ ስፖርት
ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2005በዚሁ ውድድርም የኢትዮጵያ የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሯጮች አኩሪ ውጤት ሊያስመዘግቡ በቅተዋል። ሰንበቱ ከእግር ኳስ ባሻገር ከቴኒስ እስከ አውቶሞቢል እሽቅድድም ሰፊ ትኩረትን የሳቡ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር። በለንደኑ የዊምብልደን የቴኒስ ውድድር ደግሞ ድሉ ከ77 ዓመታት በኋል እንደገና ወደ ብሪታኒያ ባለቤትነት ተመልሷል። ኤንዲይ መሪይ የብሪታኒያን ክብር ሲያስመልስ ጀርመናዊቱ ዛቢነ ሊዚኪም የልጅነት ሕልሟን ዕውን ለማድረግ ብዙ የተቃረበች መስላ ታይታ ነበር።
በፓሪሱ የዳያመንድ ሊግ ውድድር የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ዩሤይን ቦልት በ 200 ሜትር ሩጫ የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል። ቦልት በአካል ጉዳት የተነሣ ለተወሰነ ጊዜ ከውድድር ተሳትፎ እንዲቆጠብ ሲገደድ ይህ የ 19,73 ሤኮንድ ጊዜው መልሶ መጠናከሩን የሚጠቁም ነው። በዚሁ ሩጫ ሌላው ጃሜይካዊ ዋረን ዋይር ሁለተኛ ሲወጣ የፈረንሣዩ የአጭር ርቀት ኮከብ ክሪስቶፍ ሌሜትር ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።
በ1,500 ሜትር የጂቡቲው አያንሌህ ሱሌይማን ሲያሸንፍ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ አማን ወቴ ሁለተኛ ወጥቷል። አሜሪካዊው ሊዮኔል ማንዛኖ ሩጫውን በሶሥተኝነት ሲፈጽም መኮንን ገ/መድሕንም 14ኛ ሆኗል። በ 3000 ሜትር መሰናክል ኬንያዊው ኤዜኪየል ኬምቦይ በዓመቱ ፈጣን ጊዜ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ጋሪ ሮባ አራተኛ ወጥቷል። የኢትዮጵያ አትሌቶች ታላቅ ድል የታየው በተለይ በሴቶች 5000 ሜትር ሩጫ ነበር።
ጥሩነሽ ዲባባ በዓመቱ ፈጣን ጊዜ አሸናፊ ስትሆን ከሁለት እስከ አምሥት የተከተሏትም በሙሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ነበሩ። አልማዝ አያና ሁለተኛ፣ ገለቴ ቡርቃ ሶሥተኛ፣ ሴሉ ኡቱራ አራተኛ፣ ቡዜ ዲሪባ አምሥተኛ! ከነዚሁ ሌላ አለሚቱ ሃሮዬ ሰባተኛና ገነት ያለው ስምንተኛ በመሆን ውድድሩን ሲፈጽሙ ከአሥሩ ቀደምት ሯጮች ሰባቱ የኢትዮጵያ መሆናቸው የጥንካሬያቸው መለያ ነው።
ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በስዊትዘርላንድ ሉሰርን ላይ በተካሄደው ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርም የኢትዮጵያ አትሌቶች ከጠንካሮቹ መካከል የሚመደቡት ነበሩ። በ 800 ሜትር መሐመድ አማን በፍጹም ልዕልና አሸናፊ ሲሆን በ 5000 ሜትር ደግሞ ሩጫው በኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ሙሉ ቁጥጥር ስር ነበር። በዚሁ ሩጫ የኔው አላምረው ሲያሸንፍ ሃጎስ ገ/ሕይወት ሁለተኛና ሙክታር አወልም ሶሥተኛ በመሆን የኢትዮጵያን ድል የተሟላ አድርገዋል። ብርሃን ተሥፋዬና ይግረም እንዳለም ሰባተኛና ስምንተኛ ወጥተዋል።
በሴቶችም በ 3000 ሜትር መሰናክል የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው ለመሸነፍ በቅተዋል። ሕይወት አያሌው አንደኛ፣ ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛ፣እቴነሽ ዲሮ ሶሥተኛ፣ አልማዝ አያና አራተኛ! ብርቱካን አዳሙም ሩጫውን በሰባተኝነት ፈጽማለች። ከዚሁ ሌላ በ 100 ሜትር አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ሩጫውን ግሩም በሆነ 9,79 ሤኮንድ ጊዜ በመፈጸም በመጪው ወር የሞስኮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የጃሜይካው ኮከብ የዩሤይን ቦልት ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን እንደገና አስመስክሯል።
የብሪታኒያው የቴኒስ ኮከብ ኤንዲይ መሪይ ትናንት በታላቁ የዊምብልደን የቴኒስ ውድድር በፍጻሜው ግጥሚያ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነውን የሰርቢያውን ኖቫክ ጆኮቪችን በማሸነፍ የማይረሳ ታሪክ ለማስመዝገብ በቅቷል። የስኮትላንዱ ተወላጅ ኖቫክ ጆኮቪችን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 6-4,7-5,7-4 ሲረታ ድሉ ለብሪታኒያ ከ 77 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። መሪይ ከግጥሚያው በኋላ እንደገለጸው ጨዋታው በሕይወቱ ያጋጠመው ከባዱ ነበር።
«በዚህ በመጨረሻው ግጥሚያ ብዙ መሥራት ነበረብኝ። ነጥቦቹ በሕይወቴ እስካሁን ከባዱን ትግል ያደረገኩባቸው ነበሩ። ጨዋታው ቀደም ካለው ከዩ ኤስ-ኦፕን የተለየ ነበር ለማለት እወዳለሁ። እናም በዊምብልደን ማሸነፌን አሁንም ላምነው አልችልም። አዕምሮዬ ሊቀበለው አልቻለም። ጨርሶ አላምነውም»
ኤንዲይ መሪይ በወቅቱ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሁለተኛውን ቦታ ይዞ ይገኛል። የብሪታኒያ ጋዜጦች ዛሬ በዓምዶቻቸው ላይ የቴኒሱን ኮከብ ሲያስቀድሙ ከሰባት አሠርተ-ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የአገሪቱን የድል ምኞት ዕውን በማድረጉ የሎርድነት ማዕረግ ሊሰጠው እንደሚገባም ዘግበዋል። በሴቶች አንድ ቀን ቀደም ሲል በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ ፈረንሣዊቱ ማሪዮን ባርቶሊም ጀርመናዊቱን ዛቢነ ሊዚኪን በተለየ ጥንካሬ 6-1,6-4 በማሸነፍ እንዲሁ ታሪካዊ ለሆነ የመጀመሪያ ግራንድ ስላም ድሏ በቅታለች።
የ 28 ዓመቷ ባርቶሊቀደም ሲል በጎርጎሮሳውያኑ 2007 ዓ-ም ለዊምብልደን ፍጻሜ ደርሳ በአሜሪካዊቱ በቬኑስ ዊሊያምስ መሸነፏ ይታወሳል። ዊሊያምስን ካነሣን ጀርመናዊቱ ዛቢነ ሊዚኪ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በወቅቱ አንደኛ የሆነችውን የቬኑስን እህት ሤሬና ዊሊያምስን በሩብ ፍጻሜው አሸንፋ ስታስወጣ በፍጻሜው ባለድል ትሆናለች ተብላ በብዙዎች የተጠበቀችው እርሷ ነበሯች። ግን አልሆነም።
በተቀረ በዊምብልደን የቅይጥ ጥንድ ፍጻሜ የካናዳው ደኒዬል ኔስቶርና ፈረንሣዊቱ ክሪስቲና ምላደኖቪች በሶሥት ምድብ ጨዋታ በ 2-1 ውጤት አሸናፊ ሆነዋል። ተጋጣሚዎቻቸው የብራዚሉ ብሩኖ ስካሬስና አሜሪካዊቱ ሊዛ ሬይመንድ ነበሩ። በወጣት ልጆች ነጠላ ፍጻሜ ደግሞ የኢጣሊያው ጃንሉዊጂ ኩዊንዚ ኮሪያዊውን ህዮን ቹንግን አሸንፏል።
ዩ ኤስ አሜሪካ ውስጥ እስከፊታችን ሐምሌ 21 ቀን የሚዘልቀው የሰሜን፣ ማዕከላዊ አሜሪካና የካራይብ የእግር ኳስ ከንፌደሬሺን የኮንካካፍ የወርቅ ዋንጫ ውድድር ትናንት በምድብ-አንድ ግጥሚያዎች ተጀምሯል። ዕለቱ ታዲያ የታናናሾቹ ነበር ሊባል ይቻላል። እስካሁን ስድሥት የኮንካካፍ ዋንጫን በመውሰድ ቀደምቷ የሆነችው ሜክሢኮ በፓናማ 2-1 ስትረታ ካናዳም በ 12 ሃገራቱ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በምትሳተፈው በማርቲኒክ 1-0 ተሸንፋለች። የሚክሢኮው ብሄራዊ ቡድን ከወጣቶችና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ተጫዋቾች የተውጣጣ መሆኑ ምናልባትም ደክሞ የመታየቱ ምክንያት ሣይሆን አልቀረም።
ለማንኛውም ቡድኑ ስኬት ከፈለገ በሚቀጥለው ጨዋታ ማርቲኒክን ማሸነፉ ግድ ነው።ፓናማ ደግሞ ከካናዳ ትጋጠማለች። ዩ ኤስ አሜሪካ ምድብ-ሶሥት ውስጥ ከቤሊስ የመጀመሪያ ግጥሚያዋን ነገ የምታካሂድ ሲሆን ኮስታሪካና ኩባ የተቀሩት ተፎካካሪዎቿ ናቸው። ዩ ኤስ አሜሪካ ቦኮንካካፍ ዋንጫ ውድድር ዋነኛዋ የሜክሢኮ ተፎካካሪ ሆና ቆይታለች። ምድብ-ሁለት ሆንዱራስ፣ ኤል ሣልቫዶር፣ ሃኢቲ እንዲሁም ትሪኒዳድና ቶቤጎ የሚገኙበት ነው። የኮንካካፍ ጎልድ-ካፕ ውድድር በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል።
ይህ በዚህ እንዳለ በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የበጋው ዕረፍት እያበቃ ክለቦቹም ቀስ በቀስ ወደ ልምምድና ዝግጅታቸው በመመለስ ላይ ናቸው። የተለያዩት ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾችን በመግዛት ራሳቸውን ለማጠናከር የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
የኢጣሊያው ቀደምት ክለብ ኢንተር ሚላን ለምሳሌ በሁለት አዳዲስ ተከላካዮች በአርጄንቲናዊው ሁጎ ካምፓኛሮና በማርኮ አንድሬዎሊ ቡድኑን አጠናክሯል። ኢንተር ከቀድሞው የሰርቢያ ብሄራዊ ቡድን ኮከብ ከዴጃን ስታንኮቪች መለያየቱም አልቀረለትም። የ 34 ዓመቱ ስታንኮቪች በፈቃዱ የሚሰናበተው ኮንትራቱ እንዲፈርስ ከክለቡ ጋር ከስምምነት በመድረስ ነው። ስሜት በተመላው ደብዳቤ ተመልካቾች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ላሳዩት ፍቅርና ለሰጡት ድጋፍ ከልብ አመስግኗል።
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ በብራዚሉ ድንቅ የመሃል ሜዳ ተጫዋች በፓውሊኞ ደምቆ ነው አዲሱን የውድድር ወቅት የሚጀምረው። ፓውሊኞ ከኮሪንቲያንስ በመሰናበት ከቶተንሃም ሆትስፐር ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ጨርሷል። የ 24 ዓመቱ ኮከብ ብራዚል በቅርቡ የኮንፌደሬሺኑን ዋንጫ ባሸነፈችበት ወቅት ደምቆ መታየቱ የቅርብ ትዝታ ነው። ሰንደርላንድ ደግሞ አሜሪካዊውን ጆዚይ አልቲዶርን ከኔዘርላንዱ ክለብ ከአልክማር በመግዛት የበኩሉን ተሃድሶ አድርጓል።
አርሰናል ሁለት ተጫዋቾቹን ፍራንሲስ ኮኬሊንንና ዮሃን ጁሩን ለጀርመን ክለቦች ለአንድ ዓመት ሲያውስ የማንቼስተር ዩናይትድ አዲስ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስም አጥቂውን ዌይን ሩኒይን የማይሸጥ የማይለወጥ ነው ብለዋል። በብራዚሉ አዲስ ኮከብ ራሱን ያጠናከረው ባርሤሎና ደግሞ ቦያን ክርኪችን ለአንድ የውድድር ወቅት ለአያክስ አምስተርዳም ለማዋስ ወስኗል። ሌላው አሳዛኝ የስፖርት ዜና ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ፊደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ መንግሥት በፌደሬሺኑ ስራ ጣልቃ ይገባል ሲል ካሜሩንን በጊዜያዊነት ማገዱ ነው።
ካሜሩን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድቧ ቶጎ ያልተፈቀደለት ተጫዋች በማሰለፍ በነጥብ በመቀጣቷ አመራሩን መያዟ ይታወቃል። ውሣኔው እስክፊታችን ነሐሴ ወር መጨረሻ ካልተነሣ ካሜሩን ከዓለም ዋንጫው ማጣሪያ መወገዷን የሚረጋገጥ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ በተለይ ለተጫዋቾቹ መሪር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።
የሶሥት ጊዜው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ትናንት በዚህ በጀርመን በኑርቡርግሪንግ የተካሄደው እሽቅድድም አሸናፊ ሆኗል። ፌትል በገዛ አገሩ ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ደስታው ወሰን አልነበረውም። ለፌትል ድሉ በአጠቃላይ 30ኛው መሆኑ ነበር። በእሽቅድድሙ የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ሁለተኛ ሲወጣ የፌትል ዋነኛ ተፎካካሪ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ አራተኛ፤ እንዲሁም የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን አምሥተኛ ሆነዋል። ፌትል ከትናንቱ ድል ወዲህ አሎንሶን በ 34 ነጥቦች ብልጫ አስከትሎ ይመራል።
ፈረንሣይ ወስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው መቶኛው የዘንድሮው ቱር-ዴ-ፍራንስ የቢስክሌት እሽቅድድም ዘጠነኛ ደረጃውን ሲያጠቃልል የዛሬውን ዕለት ዕረፍት ተከትሎ በነገው ዕለት ይቀጥላል። በዘጠነኛው እሽቅድድም የፒሬኔስ ተራራ ውጣ ውረድ ትናንት ሲያበቃ 168,5 ኪሎሜትር የሚሆነውን ርቀት በመጀመሪያ በማቋረጥ ያሸነፈው የአየርላንዱ ዳኒዬል ማርቲን ነበር። የብሪታኒያው ክሪስ ፍሮምም ተፎካካሪዎቹ በተደጋጋሚ በማምለጥ ቢጫ ሸሚዙን እንደጠበቀ ከግብ ለመድረስ ችሏል። በአጠቃላይ ነጥብ ክሪስ ፍሮም አንደኛ ሲሆን የስፓኙ አሌሃንድሮ ቫልቬርዴ ሁለተኛ ነው፤ የኔዘርላንዱ ባውከ ሞሌማ በሶሥተኝነት ይከተላል።
መሥፍን መኮንን
ተክሌ የኋላ