1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ይዞታ በኤርትራ

ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2007

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ልዩ ዘጋቢ የሆኑት ሼኢላ ኬቴሩት ሰኞ ዕለት ጅርጅታቸው ይፋ ባደረገው ዘገባ እንደገለፁት በኤርትራ ባለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተነሳ በርካታ የሀገሪቱ ሰዎች ከነዚህም ውስጥ በተለይ ወጣቶች ሀገሪቷን ለቀው ለስደት ተዳርገዋል።

https://p.dw.com/p/1DNtz
Flüchtlinge in Rosenheim
ምስል Bundespolizei Rosenheim

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ልዩ ዘጋቢ ሼኢላ ኬቴሩት ለዘገባቸው ባሰባበቡት መረጃ ላይ ተመርኩዘው በኤርትራ ስለሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይናገራሉ።« ኢጣሊያ ከገቡ የተለያዩ ሰዎች ጋር ተነጋግሬ የደረስኩበት ድምዳሜ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን በተመለከተ ኤርትራ ውስጥ ምንም የተቀየረ ነገር የለም። አሁን ድረስ ከመኖር መብት ጋር በተያያዘ ጥሰት ይካሄዳል ፣ የዘፈቀደ እስራት ይፈፀማል። በብሔራዊ አገልግሎቱም ውስጥ ጥሰት አለ።

ኬቴሩት በኢጣሊያ ካነጋገሯቸው ኤርትራውያን መካከል አንዳንዶቹ የብሔራዊ አገልግሎት ግዳጃቸውን መወጣት ጀምረው እንደነበር እና ከዕረፍት በጊዜ አልተመለሳችሁም በማለት ወይም በሌላ ጥቃቅን ምክንያት የተነሳ የመታሰር እጣ ገጥሟቸው እንደነበር ገልፀውላቸዋል። « ከብሔራዊ ውትድርና ካመለጡ ሴቶችም ጋር ተነጋግሬ ነበር። እነሱም ከብሔራዊው አገልግሎት ግዳጅ ወቅት የወሲብ ጥቃት እንደሚፈፀም ገልፀውልኛል።»

Flüchtlinge Lampedusa
በባህር ኢጣሊያ የሚገቡ ስደተኞችምስል picture alliance / ROPI

የኢጣሊያ መንግሥት ባወጣው ዘገባ መሰረት ካለፈው ጥር ወር አንስቶ እስከ መስከረም ድረስ ወደ 135 000 የሚጠጉ ስደተኞች ኢጣሊያ ሲገቡ ከነዚህ መካከል 32 000 የሚሆኑ ኤርትራውያን ናቸው። ከአንድ ዓመት በፊት በላምፔዱዛ አቅራቢያ ከሰመጠው የስደተኞች ጀልባ በርካታ ኤርትራውያን ህይወታቸውን እንዳጡ ይታወሳል። በኤርትራ ይፈፀማሉ የተባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማስቆም ኬቴሩት መፍትሄ የሚሉትን በመጨረሻ እንዲህ ይገልፃሉ።« በመጀመሪያ ደረጃ ክስ ሳይመሰረትባቸው እስር ቤት የሚገኙትን ፍቱ። የታሰሩበት ምክንያት ህጋዊ መሆኑ መጣራት አለበት። ይሄ አንዱ ነገር ነው። ሌላው የብሔራዊ አገልግሎቱ የጊዜ ገደብ ያልተደረገበት ሁኔታ ሊመረመር ይገባል። ሰዎች ለምንድን ነው በብሔራዊ አገልግሎት ውስጥ ያሉት? የነሱም መብት ሊጠበቅ ያስፈልጋል። ሌላው ነገር ደግሞ የመማር መብትን ይመለከታል። ተማሪዎች የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፤ «ሳዋ» በሚሉት የብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግበት ሁኔታ እንደ እኔ አመለካከት ይህ በጠቅላላ ሊቆም የሚገባ ነገር ነው።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ