1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 15 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 15 2012

የጀርመን ቡንደስሊጋ ሊገባደድ አንድ ዙር ብቻ ቀርቶታል። ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ እና ወደታችኛው ዲቪዚዮን ላለመውረድ የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች በጉጉት ይጠበቃሉ። ሊቨርፑል ትናንት ነጥብ በመጋራቱ ከወዲሁ ዋንጫውን የመውሰዱን ጊዜ አራዝሟል። በሜዳ ቴኒስ የክሮሺያው ተጋጣሚ በኮሮና ተሐዋሲ በመጠቃቱ ከኖቫክ ጄኮቪች ጋር የነበረው ግጥሚያ ተሰርዟል። 

https://p.dw.com/p/3eA0d
1. FSV Mainz 05 v SV Werder Bremen - Bundesliga
ምስል Getty Images/A. Grimm

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የጀርመን ቡንደስሊጋ ሊገባደድ አንድ ዙር ብቻ ቀርቶታል። ባየር ሙይንሽን ዋንጫውን እንደተለመደው አስቀድሞ መውሰዱን አረጋግጧል። ቀሪ አንድ ዙር ጨዋታ የቀራቸው ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ እና ወደታችኛው ዲቪዚዮን ላለመውረድ የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች በጉጉት ይጠበቃሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ ዳግም በጀመረው ግጥሚያ ማሸነፍ ተስኖት ነጥብ ተጋርቷል። ሊቨርፑል ትናንት ነጥብ በመጋራቱም ከወዲሁ ዋንጫውን ለመውሰድ ጫፍ የመድረሱን ነገር ለጊዜውም ቢኾን አዘግይቶታል። ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታ ለሚቀረው ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ የሊቨርፑል ትናንት ነጥብ መጣል ቀጭን የዋንጫ ዕድሉ ላይ ተጨማሪ ተስፋ አጭሮለታል። በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የክሮሺያው ተጋጣሚ በኮሮና ተሐዋሲ በመጠቃቱ ከኖቫክ ጄኮቪች ጋር የነበረው ግጥሚያ ተሰርዟል። 

የጀርመን ቡንደስሊጋ

የባየር ሙይንሽን ለ8ኛ ጊዜ በተከታታይ የቡንደስሊጋውን ዋንጫ መውሰዱ በታወቀበት የዘንድሮ ቡንደስሊጋ ውድድር ቦሩስያ ዶርትሙንድም ኹለተናነቱን አረጋግጧል። ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑት 33ኛ የቡንደስሊጋው ግጥሚያዎች ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ30ኛው እና መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው 93ኛ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ኹለት ግቦች ለድል በቅቷል። በኧርሊንግ ሐላንድ ኹለት ግቦች የኹለተኛ ደረጃውን ዘንድሮ ማስጠበቅ የቻለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የቡንደስሊጋው የዋንጫ ፉክክር ላይ ዘንድሮም ኹለተኛ ኾኖ ማጠናቀቊ በደጋፊዎቹ ዘንድ መጠነኛም ቢኾን ቅሬታ ሳያሳድር አይቀርም። 

ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ኹለት ግቦችን ላይፕሲሽ ላይ ያስቆጠረው ኧርሊንግ ሐላንድ
ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ኹለት ግቦችን ላይፕሲሽ ላይ ያስቆጠረው ኧርሊንግ ሐላንድ ምስል Reuters/R. Hartmann

በሦስተኛ ደረጃ ለሚገኘው እና በዶርትሙንድ የ2 ለ0 ሽንፈት ለገጠመው ላይፕሲሽ ግን ቀጣዩ የመጨረሻ ግጥሚያ ሦስተኛ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያደርገው የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው። ተሸነፈም ሌሎችም አሸነፉ ግን ሰፊ የግብ ልዩነት ስላለው በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል።  በቡንደስሊጋው ላይፕሲሽ ከዶርትሙንድ በ6 ነጥብ ተበልጦ 63 ነጥቦች ሰብስቧል።  አራተኛ ደረጃን የያዘው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 62 ነጥብ አለው። ለጊዜው የአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ ውስጥ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን በ60 ነጥቡ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት የማለፍ ዕድሉ ገና አልመከነም። ቀጣዩን ቅዳሜ ዕለት ከማይንትስ ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 63 ከፍ ማድረግ ይችላል። ከሔርታ ቤርሊን ጋር የመጨረሻ ግጥሚያውን የሚያከናውነው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከተሸነፈ በ62 ነጥቡ ይወሰናል፤ እናም ባየር ሌቨርኩሰን ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ ይችላል ማለት ነው። 

20 ነጥብ ብቻ ይዞ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፓዴርቦርን ወደ ኹለተኛው ቡንደስሊጋ መውረዱ ተረጋግጧል። 17ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቬርደር ብሬመን እና ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ግን ከቡንደስሊጋው መሰናበታቸውን የሚያረጋግጡት ቅዳሜ ዕለት በሚያደርጉት በቀጣዩ የመጨረሻ ግጥሚያ ነው። 28 ነጥብ ያለው ቬርደር ብሬመን በፎርቱና ዱይስልዶርፍ የሚበለጠው በ2 ነጥብ ብቻ ነው። ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝን አሸንፎ፤ ፎርቱና ዱይስልዶርፍ በዑኒዬን ቤርሊን ቢሸነፍ ቬርደር ብሬመን በቀጥታ ከቡንደስሊጋው ከመሰናበት ይተርፋል። በቡንደስሊጋው ቀጣይ የጨዋታ ዘመን ለመቆየት ግን ከኹለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ኾኖ ከሚያጠናቅቀው ቡድን ጋር ተጋጥሞ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። 

ቡንደስሊጋ ኹለተኛው ዲቪዚዮን

ኹለተኛው ዲቪዚዮን  አርሜኒያ ቢሌፌልድ ከኦስናብሩይክ ጋር በዝግ የተጫወቱበት ሜዳ
ኹለተኛው ዲቪዚዮን አርሜኒያ ቢሌፌልድ ከኦስናብሩይክ ጋር በዝግ የተጫወቱበት ሜዳ ምስል Getty Images/S. Franklin

ከኹለተኛው ዲቪዚዮን መሪው ቢሌፌልድ እና ሽቱትጋርት ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ሽቱትጋር በቡንደስሊጋው የቆየ ተደጋጋሚ ልምድ አለው። ከሀይደንሃይም አለያም ከሐምቡርግ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናናቅቀው ቡድን በቡንደስሊጋው 16ኛ ኾኖ ከሚጨርሰው ቡድን ጋር ተጋጥሞ ካሸነፈ ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ ማለፍ ይችላል። እነዚህም ጨዋታዎች በጉጉት ይጠበቃሉ። 

ሐምቡርግ እንደ ሽቱትጋርት በዋናው ቡንደስሊጋ የቆየ ተደጋጋሚ ልምድ ያለው ቡድን ነው። በአንድ ዘመን በቡንደስሊጋው ተወዳዳሪ የነበሩት እነ ኑይረንበርግ እና ድሬድሰን ከኹለተኛው ዲቪዚዮንም አሽቆልቁለዋል። እንደውም 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ድሬድሰን ወደ ሦስተኛ ዲቪዚዮን ላለመውረድ ቀጣዩን የመጨረሻ ግጥሚያ አሸንፎ የቪስባደን እና የካርልስሩኸ ቡድኖችን መሸነፍ በተስፋ መጠበቅ ይኖርበታል። የዋናው ቡንደስሊጋም ኾኑ የኹለተኛው ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች የፊታችን ቅዳሜ ከሰአት በተመሳሳይ ሰአት ነው የሚከናወኑት። 

እጅግ ብርቱ ፉክክር የሚታየው በቡንደስሊጋው ሦስተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ነው። ከመሪው የባየር ሙይንሽን ኹለተኛ ቡድን አንስቶ እስከ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቪክቶሪያ ኮሎኝ ድረስ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በማጠናቀቅ ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን የማለፍ ዕድል አላቸው። ከመሪው  ባየር ሙይንሽን ኹለተኛው ቡድን  እስከ 13ኛው ቪክቶሪያ ኮሎኝ ድረስ የነጥብ ልዩነቱ የ14 ብቻ ሲኾን ከ1ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ልዩነቱ የአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ሦስተኛ ዲቪዚዮኑ ሊጠናቀቅ አራት ዙር ግጥሚያዎች ይቀራሉ። አጠቃላይ ግጥሚያዎች ዋናው ቡንደስሊጋ እና ኹለተኛ ዲቪዚዮን ግጥሚያዎች ከመጀመራቸው አንድ ሰአት ተኩል ቀድም ብለው ነው የሚከናወኑት። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተደረጉ ግጥሚያዎች ትናንት መሪው ሊቨርፑል ከኤቨርተን ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። ሊቨርፑል 83 ነጥብ ይዞ የፕሬሚየር ሊጉን ደረጃ ሲመራ፤ ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ነጥቡን 60 አድርሷል። በዛሬው ምሽት ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ በርንሌይን ማሸነፍ ከቻለ ለዋንጫ በሚደረገው ውድድር ተስፋውን ማለምለም ይችላል። በእርግጥ ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ እና ከራሱ ማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጋቸውን ቀጣይ ጨዋታዎች ካሸነፈ የዋንጫ ፉክክሩ ያከትምለታል። 

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተጨዋቾች ለጥቊር መብት ድጋፋቸውን ሲያሳዩ
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተጨዋቾች ለጥቊር መብት ድጋፋቸውን ሲያሳዩምስል Getty Images/AFP/C. Recine

በተለይ ደግሞ ኹለቱም ቡድኖች ቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን አሸንፈው ቢገናኙ ለኹለቱም ቡድኖች ግጥሚያው እጅግ ልዩ ነው የሚኾነው። ሊቨርፑል  ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲን ባሸነፈበት ጨዋታ ዋንጫ መውሰዱን ለማረጋገጥ፤ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ሊቨርፑል ዋንጫውን አገኝበታለኹ ያለበትን ቀን በማምከን ኹለቱም ልዩ ታሪክ መሥራት ይሻሉ። በመሀል ግን ኹለቱ ቡድኖች ነጥብ የሚጥሉ ከኾነ ይኽ ለየት ያለ ግጥሚያ ትርጉም ሊያጣም ይችል ይኾናል። በዚህም አለ በዚያ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ማታ ኹለቱ ተፎካካሪዎች የሚያደርጉት ፍልሚያ በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቅ ግጥሚያ ነው። 

ትናንት አስቶን ቪላን 2 ለ1 ድል ያደረገው ቸልሲ በቀጣይ የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ተካፋይ ለመኾን ያስቻለውን ዕድል አጠናክሯል።  46 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ዐርብ ዕለት ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ተጫውቶ አለመሸነፉ በጅቶታል። ቢሸነፍ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊነቱን ይቀማ ነበር። አንድ እኩል በመለያየቱ ግን ከዎልቭስ ጋር በግብ ልዩነት ብቻ ተለያይቶ አምስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። አንድ ተጨዋቹን በቀይ የተነጠቀው ሼፊልድ ዩናይትድ በኒውካስል 3 ለ 0 ተቀጥቷል።  ባለፈው ረቡዕ ኤትሀድ ስታዲየም ውስጥ በማንቸስተር ሲቲ 3 ለ0 የተሸነፈው አርሰናል ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል። አርሰናል ቅዳሜ ዕለት 15ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ብራይተን 2 ለ 1 ተሸንፏል። 

የማንቸስተር ዩናይትዱ ማርኩስ ራሽፎርድ
የማንቸስተር ዩናይትዱ ማርኩስ ራሽፎርድምስል Imago Images/R. Hart

የሜዳ ቴኒስ
የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቹ ግሪጎር ዲሚትሮቭ የምርመራ ውጤቱ በኮቪድ-19 እንደተጠቃ ማሳየቱን ተከትሎ ክሮሺያ ውስጥ የሜዳ ቴኒስ ውድድሩ ተሰርዟል። ተጨዋቹ የኮሮና ተሐዋሲ እንደተገኘበት ትናንትና ይፋ በማድረጉ ከዕውቊ የሜዳ ቴኒስ ባለድል ኖቫክ ጄኮቪች ጋር የነበረው ግጥሚያ ተሰርዟል። በዓለም የሜዳ ቴኒስ ፍልሚያ ለሦስት ጊዜያት ለፍጻሜ የደረሰው እና አኹን ባለው ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዲሚትሪ ከሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ተጨዋቾች በኮሮና ተሐዋሲ የተጠቃ የመጀመሪያው ተጨዋች ኾኗል። 

የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቹ ግሪጎር ዲሚትሮቭ
የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቹ ግሪጎር ዲሚትሮቭምስል picture-alliance/Pixsell/D. Stanin

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ፈረንሣይ ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየሞች ማስገባት ልትጀምር እንደኾነ ፍንጭ ዐሳይታለች። ምናልባት እስከ አምስት ሺህ የሚጠጉ የእግር ኳስ ታዳሚዎች ከሰኔ 16 ቀን ጀምሮ ወደ ስታዲየሞች መግባት ሊፈቀድላቸው ይችል ይኾናል ተብሏል። ጀርመን ውስጥም የአውሮጳ ሊግ ፍጻሜ እና የጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ የፍጻሜ ፍልሚያዎች ላይ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ሊታደሙ እንደሚችሉ ቀደም ሲል ተነግሯል። ይኽንንም የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB) ፕሬዚደንት ፍሪትስ ኬለር ባሳለፈው ሳምንት ተናግረዋል።  በጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ የባየር ሙይንሽን እና የባየር ሌቨርኩሰን የፍጻሜ ፍልሚያ  ቤርሊን በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታዲየም ውስጥ  1,000 ሰዎች እና የተወሰነ ደጋፊዎች ሊገኙ ይችላሉ ብለዋል።

ዝውውር

የባየር ሌቨርኩሰኑ አማካይ ካይ ሐቫርትስ ወደ የትኛው ቡድን እንደሚቀላቀል በቅርቡ ይፋ ይኾናል ተብሏል። ቸልሲ የሚለው ያመዝናል። ባየር ሙይንሽን በገንዘብ ጉዳይ ለጊዜው የዝውውር ጉዳዩን ትቶታል።  ስፖርት ቡዘር እና ማርካ የተሰኙ የመረጃ ምንጮች የ21 ዓመቱ አማካይ ወደ ሪያል ማድሪድ መኼድ እንደሚፈልግ ዛሬ ዘግበዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ