የሰኔ 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሰኔ 20 2014ብርቱ ፉክክር የታየበት የቤትኪንግ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል። በዛሬው ዕለት የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን ለመውሰድ በሚደረገው ፉክክር ልዩ ቦታ የሚሰጣቸው ነበበሩ። ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባ ምንጭ ከነማ። በሜዳ ቴኒስ የዌምብልደን ግጥሚያ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ በ41 ዓመቷ ለዳግም ውድድር ብቅ ብላለች። ላለፈው አንድ ዓመት ከውድድር ውጪ ነበረች። በተጨዋቾች ዝውውር አቡበከር ናስር ለደቡብ አፍሪቃው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ተሰልፎ ይጫወታል። ወደ ባየርን ሙይንሽን ያቀናው የሊቨርፑሉ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ 17 ቁጥር ለብሶ ለመጫወት ወስኗል።
ባህር ዳር ስታዲየም ውስጥ ዛሬ በተከናወኑ የቤትኪንግ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ዳሰሳ አድርገናል። ከዚያ በፊት ግን የዝውውር ዜና እናሰማችሁ። የደቡብ አፍሪቃው ንጉሥ ቡድን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የአጥቂ መስመሩን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርን ጠርቶታል። ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አቡበከርን አስፈርሞት የነበረው ከስድስት ወራት በፊት በነበረው የተጨዋቾች ዝውውር ወቅት ነበር። አቡበከር ናስርን የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ልባዊ በሆነ ሁኔታ ሽንት አድርጎለታል። የኢትዮጵያ ቡና ዛሬ በቤትኪንግ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በፋሲል ከነማ የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል።
የቤትኪንግ ፕሬሚየር ሊግ እጅግ አጓጊ በሆነ መልኩ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። በፋሲል ከነማ የበላይነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ እዚያው ባህር ዳር ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው ሌላኛው ግጥሚያ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር ተጋጥሞ ወሳኝ የኾነውን ድሉን አስመዝግቧል። በወቅቱ የጣለው ብርቱ ዝናም ተጨዋቾችን ኳስ ለመግፋት እጅግ ሲያስቸግራቸው ታይቷል። ሁለቱንም ጨዋታዎች በተመለከተ ዳሰሳ አድርገናል።
ፋሲል ከነማ ለድል በበቃበት ግጥሚያ፦ ምናልባትም ሙጂብ ቃሲም ሦስተኛ ግብ አስቆጥሮ ሔርትሪክ ለመሥራት በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ኾኖም ኳሷ ከማዕዘን በላይ ወጥታለች። በጨዋታው ሙጂብ ቃሲም እና ሱራፌል ዳኛቸው ናቸው ግብ ያስቆጠሩት። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከነዓን ማርክነህ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
በአጠቃላይ የፋሲል ከነማ እና የአርባ ምንጭ ከነማ የበላይነት የታየባቸውን የዛሬውን ጨዋታዎች ባልደረባዬ ታምራት ዲንሳ ከሞላ ጎደል ተከታትሎት ነበር። የፋሲል ከነማ ዛሬ በተከላካይም፣ በመሀል ክፍሉም ኾነ በአጥቂ መስመሩ ድንቅ ጨዋታ ነው ያካኼደው። አርባ ምንጮችም ጫና ሲፈጥሩ በዚያው ልክ በቅዱስ ጊዮርጊስ የመልሶ ማጥቃት ሲጋለጡ ተስተውለዋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ፋሲል ከነማ ዛሬ 29ኛ ጨዋታውን ሲያሸንፍ በ61 ነጥብ ለጥቂት ሰአታትም ቢሆን የሊጉ መሪነትን መቆናጠጥ ችሎ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ አከናውኖ በ62 ነጥብ ፋሲል ከነማን የሁለተኛ ደረጃን አስይዟል። እንግዲህ ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጨዋታ ይቀራቸዋል። የዛሬው ውጤት የዋንጫ አሸናፊውን ለመለየት የሚኖረው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነበር።
የተጨዋቾች ዝውውር
የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዶዮ ማኔ በጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን ቡድን የ17 ቁጥር መለያ ለብሶ ለመጫወት መወሰኑ ታውቋል። ሳዲዮ ማኔ ሊቨርፑል በነበረበት ወቅት 10 ቁጥር ማሊያ ለብሶ ነበር የሚጫወተው። 10 ቁጥር መለያ ባየርን ሙይንሽን ውስጥ በጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቹ ሌሮይ ሳኔ የተያዘ በመሆኑ ሳዲዮ ማኔ ለ17 ቁጥ ር ወስኗል። በ17 ቁጥር መለያውም ለራሱም ኾነ ለአዲስ ቡድኑ ባየርን ሙይንሽን ውጤታ ለማስመዝገብ መቁረጡን ዛሬ ዐስታውቋል። ሳዲዮ ማኔ ከባየርን ሙይንሽን ጋር ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ለመጫወት መፈረሙ ይታወቃል። ሳዲዮ ማኔ ሲመጣ ከቡድኑ የሚወጣው ሮቤርት ሌቫንዶብስኪን ለባርሴሎና ለማዛወር ባየርን ሙይንሽን ቢያንስ 60 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚፈልግ ዐስታውቋል። ዘገባው የስካይ ስፖርት ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ የመሀል ተጨዋቹ ሐሪ ማጉዌርን ባርሴሎና ለመውሰድ ያደረገውን ሙከራ ውድቅ ማድረጉን ሰን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ሊቨርፑል የቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ጁድ ቤሊንግሐምን ለማስፈረም ርግጠኛ መሆኑን ማሳወቁን ጋርዲያን ዘግቧል። የማንቸስተር ሲቲ ብራዚሊዊ አጥቂ ጋብሪዬል ጄሱስ ለአርሰናል ለአምስት ዓመት መፈረሙ ታውቋል። የማንቸስተር ዩናይትዱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ የ37 ዓመቱ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለዴቪድ ቤክሃም ኢንተር ሚያሚ እንደማይፈርም እና በኦልድ ትራፎርድ እንደሚቆይ ወስኗል።
የሜዳ ቴኒስ
አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ተጨዋች የዓመቷ ሴሬና ዊሊያምስ ወደ ዌምብልደን ዳግም ተመልሳለች። በቅርቡ የ41 ዓመት የሚሞላት ሴሬና ዊሊያምስ ዘንድሮ ወደ ዌምብልደን የተመለሰችው ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነው። አሜሪካዊቷ ተጨዋች ባለፈው አንድ ዓመትም ውድድሮችን ሳታካኺድ ቆይታለች። ነገ የምትጋጠመውም ከፈረንሳዊቷ ሐርሞኒ ታን ጋር ነው። ለሰባት ጊዜያት የዊምብልደን አሸናፊ የነበረችው ሴሬና በ41 ዓመቷ ምን ያህል ተጋጣሚዋን ታስጨንቅ እንደሆን የሚታይ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ