የሰኔ 21 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሰኔ 21 2013በአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው ግጥሚያ ኔዘርላንድ እና ፖርቹጋል ባልተጠበቀ ኹኔታ ከውድድሩ ውጪ ኾነዋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ነገ የእንግሊዝ ቡድን በሜዳው ለንደን ዌምብሌይ ስታዲየም ይጠብቀዋል። በሐንጋሪ ከውድድሩ ከመውጣት ለጥቂት የተረፈው እና በመከራ ያለፈው የጀርመን ቡድን በነገው ጨዋታ እጅግ ብዙ ይጠበቅበታል። በደቡብ አሜሪካው የኮፓ አሜሪካ የእግር ኳስ ግጥሚያ ነገ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ይኖራሉ። አርጀንቲና እና ኡራጒይ ተፎካካሪዎቻቸውን ሲጠብቊ ብራዚል ትናንት ነጥብ ጥሏል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን የ7 ጊዜያት የዓለም ባለድሉን እንቅልፍ ነስቶታል። በ18 ነጥብ እየመራ ነው።
እግር ኳስ
በዓለም ታላላቅ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እጅግ የሚፈላለጉ፣ በዐይነ ቁራኛ የሚጠባበቁ ቡድኖች። 25 ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብለን እስከ ነገው ግጥሚያ አጭር ዳሰሳ ይኖረናል። ጀርመን ከእንግሊዝ። ጀርመን እና እንግሊዝ ካለፈው ሩብ ክፍለዘመን ወዲህ እስከ ዛሬ ድረስ ባደረጓቸው አራት ታላላቅ የሚባሉ ግጥሚያዎች ጀርመን ሁለት ጊዜ አሸንፋ ሁለት ጊዜ ተሸንፋለች። የቅርብ ጊዜው ድል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 የዓለም ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በተደረገው ግጥሚያ ላይ ነበር። ያኔ ጀርመን እንግሊዝን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ የእንግሊዝን ቡድን አዋርዳለች። በያኔው ግጥሚያ በአሰልጣኝ ፋቢዮ ካፔሎ ይመራ የነበረው የእንግሊዝ ቡድንን አሳፍረው ከውድድሩ ያሰናበቱት የጀርመን ቡድን ግብ አስቆጣሪዎች፦ ሚሮስላፍ ክሎዘ፣ ሉቃስ ፖዶልስኪ እና ቶማስ ሙይለር ነበሩ። ቀደም ብሎ በተደረገው ዓለም አቀፍ ውድድር ጀርመኖች የደረሰባቸው ውርደት የተበቀሉበት ግጥሚያ ነበር ማለት ይቻላል።
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በጋራ ባዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በነበረው የማጣሪያ ግጥሚያ እንግሊዝ ጀርመንን ጉድ አድርጋ ነበር። ከ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ቀደም ብሎ በተኪያኼደው ማጣሪያ እንግሊዝ ያሸነፈችው 5 ለ1 ነበር። በዘመኑ የዓለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂ የነበረው ኦሊቨር ካን ላይ የእንግሊዞቹ የያኔው ምርጦች፦ ሚካኤል ኦወን፣ ኤሚሌይ ሔስኪይ እና ሽቴፋን ጄራርድ አምስት ግቦችን በተከታታይ አስቆጥረውበት በወቅቱ ጉድ አሰኝተው ነበር።
ከዚያ ውጪ ከ21 ዓመት በፊት ለአውሮጳ አሸናፊዎች ማጣሪያ ለማለፍ በተደረገው ግጥሚያ እንግሊዝ ጀርመንን 1 ለ0 አሸንፋለች። በዚያ ግጥሚያ እንግሊዝ ጀርመንን በታላቅ ውድድር ላይ ስታሸንፍ ከ34 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። በዚያ ታሪካዊ ድል ላይ ብቸኛዋን ግብ በ53ኛ ደቂቃ ላይ ለእንግሊዝ ያስቆጠረው አጥቂው አለን ሺረር ነበር።
የዛሬ 25 ዓመት ደግሞ ለአውሮጳ አሸናፊዎች ለንደን ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ጀርመን እንግሊዝን 6 ለ5 አሸንፋለች። የመጀመሪያውን ግብ ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ጀርመኖችን ያስደነገጠው የግብ ቀበኛው አለን ሺረር ነበር። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ግን በአሁኑ ወቅት የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከ21 ዓመት በታች ተጨዋቾች አሰልጣኝ የኾነው ሽቴፋን ኩንትስ አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል። 90 ደቂቃው ተገባዶ፤ ከዚያ በኋላ የተሰጠው የጭማሪ 30 ደቂቃም ተጠናቆ በነበረው የፍጹም ቅጣት ምት መለያ ነበር ጀርመን 6 ለ5 ያሸነፈችው። ተከላካዩ ጋሬት ሳውዝጌት የመታት ኳስ በጀርመኑ ግብ ጠባቂ አንድሪያስ ኮይፕከ በመጨናገፉ እንግሊዝ በሜዳዋ ዌምብሌይ ስታዲየም የሽንፈትን መሪር ጽዋ ተጎንችታለች። የሚደንቀው ነገ እዛው ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ በሚካኼደው ግጥሚያ የእንግሊዝን ቡድን የሚመሩት አሰልጣኝ ለያኔው ሽንፈት ሰበብ የነበሩት የያኔው ተከላካይ የአሁኑ አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት ናቸው።
ዘንድሮስ እንግሊዝ በሜዳዋ ዌምብሌይ ስታዲየም በነገው ዕለት ጀርመንን ስትገጥም ምን ይከሰት ይሆን? ታሪክ ራሱን ይደግም ይሆን፤ ወይንስ ባለፉት ዓመታት እጅግ መዳከም የተስተዋለበት የአሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ ቡድን ሽንፈት ይገጥመው ይሆን? በርካታ እንግሊዛውያን ግን ከወዲሁ ፍራቻቸውን ገልጠዋል። ባለፈው ረቡዕ ጀርመን ከሐንጋሪ ጋር ሁለት እኩል ተለያይታ ወደ ሩብ ፍጻሜው ባለፈችበት ወቅት የእንግሊዝ ጋዜጦች ከጻፉት አንዱን ሳይጠቅሱ ማለፍ የሚገባ አይመስለንም። «ምን አይነት ጣጣ ነው። ዳግም ጀርመኖች!» ሲል ስጋቱን የገለጠው ዴይሊ ሚረር የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ ነው። በጀርመኖች ተደጋጋሚ መከራ ስለደረሰበት የእንግሊዝ እግር ኳስ ጋዜጣው ያን ማለቱ የሚጠበቅ ነው። እንግሊዞች ለሁለት ጊዜያት በግማሽ ፍጻሜ፤ ለሁለት ጊዜያት በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ጉድ ያደረጋቸው የጀርመን ቡድን ዘንድሮ ከምንጊዜውም በላይ ተዳክሞ ቢገኝም በፍርሐት ዐይን መመልከታቸው ግን አልቀረም።
በነገው ጨዋታ ጋሬት ሳውዝጌት ለ25 ዓመት አብሯቸው የዘለቀውን ሽንፈት ያካክሱም ይሆናል። ምናልባትም ጀርመኖች ዳግም አሸንፈው የነገው ጨዋታ አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚኖራቸው የመጨረሻው ቆይታ ከመኾንም ሊታደጉት ይችሉ ይኾናል። ዮአኺም ሎይቭ ከአውሮጳ አሸናፊዎች ውድድር በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ለቀድሞው የባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ለማስረከብ ሁሉም ነገር ተጠናቋል። ጋሬት ሳውዝጌት ወይንስ ዮአኺም ሎይቭ? የነገውን ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ የሚካኼደውን የጀርመን እና የእንግሊዝ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ መመልከት ነው። በነገው እለት ስዊድን እና ዩክሬንም ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ይጋጠማሉ።
በነገራችን ላይ ስፔን ከክሮሺያ እየተጫወቱ ሲሆን ፈረንሳይ ከስዊትዘርላንድ ጋር የምትጋጠመ ዛሬ ማታ ነው። በትናንትናው እለት ፖርቹጋል በቤልጂየም 1 ለ0 ተሸንፋ፤ ኔዘርላንድ በቼክ ሪፐብሊክ 2 ለ0 ድል ተነስታ መሰናበታቸው በርካቶችን አስደምሟል። በተለይ በጨዋታው ልቃ የነበረችው ፖርቹጋል ሽንፈት ለደጋፊዎቿ እጅግ አሳዛኝ ነበር። ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጥርሱን እንደነከሰ፣ እንባ ያቀረሩ ዐይኖቹን መሬት ላይ ተክሎ ከሴቪያ ስታዲየም ሜዳ ሲወጣ፤ ብርቱው ተከላካይ ፔፔ በቁጭት የተብሰከሰከበትን የትናንቱን ጨዋታ ለተመለከተ ምስላቸው አሁንም ድረስ ከአዕምሮ የማይጠፋ ነው። ሮናልዶ በ36 ዓመቱ፤ ፔፔ በ38 ዓመቱ ያደረጓቸው የትናንቱ ወሳኝ ግጥሚያ ምናልባትም በእግር ኳስ የጨዋታ ዘመናቸው የመጨረሻው ሳይሆንም አይቀርም። የፖርቹጋል ወርቃማው ዘመን ትውልዶች አባል ከኾኑት የቀድሞ ተጨዋቾች ምናልባት ክርስቲያኖ ሮናልዶ አቋሙ ገና በ38 እና 39 ዓመቱም መጫወት እንደሚችል አመላካች ነው። የትናንቱ ግን በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሩን ለመወከል የመጨረሻውም ሊሆን ይችላል። በእነ ሮሜሉ ሉካኩ፣ ኬቪን ደብረወይን፤ የሐዛርድ ወንድማማቾቹ ኤደን ሐዛርድ እና ቶርጋን ሐዛርድ የሚመራው የቤልጂየሙ ብሔራዊ ቡድን በቅጽል ስሙ «ቀያዮቹ ሰይጣኖች» የፖርቹጋል ምርጦችን አፍረክርከዋል። በሩብ ፍጻሜው የፊታችን ዐርብ የሚጠብቃቸው ግን የጣሊያኑ ኃያል ቡድን ነው።
ኮፓ አሜሪካ
በደቡብ አሜሪካው የኮፓ አሜሪካ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ብራዚል ከኤኳዶር ጋር አንድ እኩል ስትለያይ፤ ፔሩ ቬኔዙዌላን 1 ለ0 ረትታለች። አርጀንቲና ከቦሊቪያ ጋር ነገ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ይጋጠማሉ። አርጀንቲና ምድቧን በ7 ነጥብ ትመራለች። በተመሳሳይ ሦስት ግጥሚያዎችን ያደረገችው ፓራጓይ በ6 ነጥብ ትከተላለች። ነገ ማታ እነ አርጀንቲና በሚጫወቱበት ተመሳሳይ ሰአት ከፓራጓይ ጋር ትጋጠማለች። ቺሌ፣ ኡራጓይ እና ቦሊቪያ 5፣ 4 እና 0 ነጥብ ይዘው ተደርድረዋል። በሌላኛው ምድብ ደግሞ ብራዚል በ10 ነጥብ ሌሎቹን ርቃ ቀዳሚ ኾናለች። በምድቡ ሁሉም አራት ግጥሚያዎችን አከናውነው ፔሩ በ7 ነጥብ ይከተላል። ኮሎምቢያ፣ ኤኳዶር እና ቬኔዙዌላ 4፣3 እና 2 ነጥብ ይዘው ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተርታ ተደርድረዋል።
ፎርሙላ አንድ
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታኒያዊው የሰባት ጊዜያት የዓለም ባለድል ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል። ኔዘርላንዳዊው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን የትናንቱን ድል ጨምሮ በ18 ነጥብ ልዩነት የፎርሙላ አንድ መሪ መሆን ችሏል። እስካሁን ድረስ 156 ነጥቦችን ሰብስቧል። ትናንት የሁለተኛ ደረጃን ያገኘው ሌዊስ ሐሚልተን እስካሁን የሰበሰበው ነጥብ 138 ነው። ሌላኛው የሬድ ቡድል አሽከርካሪ ሜክሲኮዋዊው ሠርጂዮ ፔሬዝ በ96 ነጥብ በአጠቃላይ ውድድሩ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ሠርጂዮ ፔሬዝ በትናንቱ ውድድር ከመርሴዲስ አሽከርካሪው ቫለሪ ቦታስ ቀጥሎ በመግባት የአራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች ፊንላንዳዊው አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ 74 ነጥብ ይዞ የአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የአራተኛ ደረጃውን የያዘው የማክላረን መርሴዲሱ አሽከርካሪ ብሪታንያዊው ሎንዴርኖ ነው።
ብስክሌት
በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ውድድር ቅዳሜ ዕለለት ቢያንስ 30 ብስክሌተኞች እስርስ በእርስ እንዲላተሙ ሰበብ የኾነችው ወጣት ተመልካች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው። ከውድድሩ መነሻ 45ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ሎንዴርኖ በተባለው አካባቢ ማንነቷ ያልተገለጠው ወጣት ድርጊት በርካታ ብስክሌተኞች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል። ወጣቷ ወደ ጎን ረዘም ያለ ካርቶን በእጇ እንደያዘች ድንገት ከተመልካቹ ወደ አስፋልቱ ብቅ ትላለች። ካርቶኑ ላይ በጀርመንኛ «ሁሉም ወንድ አያትዬ ሴት አያትዬ!» („Allez Opi Omi!“)የሚል ጽሑፍ ይነበብበታል። ሴት አያት እና ወንድ አያት በቁልምጫ የሚጠሩበት «ኦሚ» እና «ኦፒ» የሚሉት ቃላት በጀርመንኛ ቋንቋ ብቻ ነው የሚገኙት።
የ36 ዓመቱ ጀርመናዊ ብስክሌተኛ ቶኒ ማርቲን ከካርቶኑ ጋር ተላትሞ መስመሩን ስቶ ይወድቃል። ከዚያም በተከታታይ ከኋላው የመጡ ሌሎች ብስክሌተኞች አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ በመውደቅ ጉዳት ደርሶበታል። ወጣቷ ምናልባትም ጀርመንኛ ከሚነገርበት የፈረንሳይ አካባቢ የመጣች ሳትሆን አይቀርም ተብሏል። የቱር ደ ፍሯንስ አዘጋጆች መጥፎ ድርጊት የፈጸመችው ወጣት ብርቱ ቅጣት እንደሚጠብቃት ዝቷል። ፖሊስ ወጣቷን ለመያዝ ፍለጋ ላይ መሆኑ ተዘግቧል። ወጣቷ የካርቶኑን ምስል ውድድሩን በሚቀርጸው ካሜራ ለማሳየት ብትጥርም ያን ተከትሎ ለደረሰው ጉዳት ግን ትጠየቃለች ተብሏል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችልን ነገር ባለመገንዘብ በካሜራ ለመታየት አለያም ለየት ላለ ዝና ፍለጋ የሚፈጸም ተግባር የሚያስከትለው ጣጣ ቀላል አይደለም። ወጣቷ የቱር ደ ፍሯንስ ብስክሌት ውድድር ተመልካች ለፈጸመችው ጥፋት ምናልባትም እስከ 15 000 ዩሮ ቅጣት እንደሚጠብቃት ተነግሯል። ለሁሉም ምንጊዜም መረጋጋቱ ይበጃል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሀመድ