1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 8 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 8 2012

በጀርመን ቡንደስሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። የስፔን ላሊጋ ከጀርመን ቡንደስሊጋ ልምድ መውሰዱን የላሊጋው ባለሞያዎች ለዶይቸ ቬለ ዐስታውቋል። ጃፓን፣ ሲንጋፖር እና አዘርባጃን ውስጥ ሊከናወኑ የነበሩ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድሞች ተሰርዘዋል።

https://p.dw.com/p/3dnZd
Fußball Bundesliga |  Schalke 04 v RB Leipzig | Timo Werner
ምስል Getty Images/Bongarts/A. Grimm

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች የቀሩት የጀርመን ቡንደስሊጋ ዋንጫን ባየር ሙይንሽን ለስምንተኛ ጊዜ ለማንሳት ጫፍ ደርሷል። የኤር ቤ ላይፕሲሹ ቲሞ ቬርነር እና የባየር ሌቨርኩሰኑ ካይ ሐቫርትስ ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በተለይም ወደ ቸልሲ ሊያቀኑ ጫፍ ደርሰዋል። ስለ ኹለቱ ጀርመናውያን ወጣት የእግር ኳስ ተጨዋቾች ማንነት ቅኝት አድርገናል። የጀርመን ቡንደስሊጋን ተከትሎ የስፔን ላሊጋ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ቀሪ ውድድሮችን ማከናወን ጀምሯል። ላሊጋው ከቡንደስሊጋው ልምድ መውሰዱንም የእግር ኳስ ባለሞያዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። 

ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮም ዋንጫውን የመሰዱ ነገር አይቀሬ ኾኗል፤ የቀረው የሰአታት ጊዜ ብቻ ነው።  ባየርን የሚጠበቅበት በወራጅ ቃጣናው ከመጨረሻው ፓዴርቦን በ8 ነጥብ ከፍ ብሎ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቬርደር ብሬመንን በነገው ጨዋታ ገጥሞ ማሸነፍ ብቻ ነው።

Fußball Bundesliga FC Bayern - Mönchengladbach
ምስል Getty Images/A. Hassenstein

ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህን 2 ለ1 በትግል ባሸነፈበት ግጥሚያ ያልተሰለፉት ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ፤ ቶማስ ሙይለር እንዲሁም 62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ተከላካዩ  አልፎንሶ ዳቪስ በነገው ጨዋታ ተሰላፊ እንደሚኾኑ ተገልጧል። ያም በመኾኑ የሐንሲ ፍሊክ  ባየር ሙይንሽን የነገውን ጨዋታ አሸንፎ ዋንጫውን ለመውሰድ የሚከብደው አይመስልም። አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች በነበሩ ጊዜ ተደጋጋሚ ሽንፈት በማስተናገድ ስጋት ውስጥ ወድቆ የነበረው ባየር ሙይንሽን በአሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ አመራር በተደጋጋሚ በማሸነፍ የቀድሞ ኃያልነቱን ማስመለስ የቻለ ይመስላል።

ኒኮ ኮቫች የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ሊኾኑ ነው የሚልም ጭምጭምታ እየተሰማ ነው። የዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዝምተኛው አሰልጣኝ ሉሲያን ፋቭሬ የዘንድሮ የቡንደስሊጋ ዋንጫ ላይ የነበራቸውን ቀጭን የተስፋ ክር ከባየር ሙይንሽን ጋር በነበራቸው ግጥሚያ መበጠሳቸው ነው። የ62 ዓመቱ አሰልጣኝ በዘመናቸው ለኹለተኛ ጊዜ ጫፍ ደርሰው ከዋንጫ ሽሚያው ለጥቂት ወጥተዋል። ባለፈው ግጥሚያ ሐንሲ ፍሊክ ያሸነፏቸው በጠበበ ልዩነት 1 ለ0 ነበር።

አሰልጣኙ ሌሎች ቡድኖችንም በደንብ ቢያሳድጉም፤ ተጨዋቾችን ማፍራት ቢችሉም ወሳኙን ዋንጫ ግን ማግኘት ተስኗቸው ቆይተዋል።  እናም ቦሩስያ ዶርትሙንድ የዋነኛ ተቀናቃኙ ባየር ሙይንሽንን ጓዳ የሚያውቊት የቀድሞው አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫችን ማስመጣቱ ያዋጣዋል የሚሉም አሉ። እናስ በዘመናቸው እንደ ግናብሬ ያሉ ተጨዋቾችን ዐይን ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ያስቻሉት እንደ ቡድን ግን ባየር ሙይንሽንን መታደግ የተሳናቸው አሰልጣኝ  ኒኮ ኮቫች ወደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አቅንተው የቀድሞ ቡድናቸውን እንዳስከፋቸው ድል አድርገው በተራቸው ያስከፉት ይኾን? ወደፊት የሚታይ ነው።

Fußball Bundesliga 31. Spieltag | FC Schalke 04 vs. Bayer 04 Leverkusen | Abseitstor
ምስል Getty Images/AFP/I. Fassbender

በቡንደስሊጋው ከዋክብት ኾነው ብቅ ያሉት ጀርመናውያን ኹለት ተጨዋቾችን የዓለም ምርጥ ቡድኖች እያደኗቸው ነው። የኤርቤ ላይፕሲሹ አጥቂ ቲሞ ቬርነር እና የባየር ሌቨርኩሰኑ ካይ ሐቫርትስን በስተመጨረሻ ግን ቸልሲ የቀለባቸው ይመስላል። የቲሞ ቬርነር ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ የመኼዱ ነገር የማይቀር መኾኑ በሚነገርበት ሰአት ካይ ሐቫርትስንም ወጣቱ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ሊያስመጣው እንደኾነ እየተዘገበ ነው።

ከፍተኛ ግብ የማግባት ችግር ያጠቃው ቸልሲ ከየኛትኛውም ቡድን በተለየ ለቀጣዩ የጨዋታ ዘመን ግብ አዳኞችን ይሻል። ከ19 ዓመት በፊት ከዌስት ሀም ዩናይትድ ቸልሲን በተጨዋችነት የተቀላቀለው አሰልጣኝ  ፍራንክ ላምፓርድ ይኽን ችግር በሚገባ የተረዳ ይመስላል።

ቸልሲን በረዥም ዘመን እቅድ በፕሬሚየር ሊጉ ፍልሚያ ቊንጮ ማድረግ የሚሻው ላምፓርድ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ይተማመናል። ጀርመናዊው አጥቂ ቲሞ ቬርነር 24 ዓመቱ ነው። የባየር ሌቨርኩሰኑ የአጥቂ ባሕሪ ያለው አማካዩ ካይ ሐቫርትስ 21ኛ ዓመቱን ከያዘ ገና ጥቂት ቀናት ነው የተቆጠሩት።

ቲሞ ቬርነር፦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ ለላይፕሲሽ ተሰልፎ እየተጫወተ ይገኛል። እስከ ስድስት ዓመቱ ድረስ ለTSV ሽታይንሃለንፌልድ ተጫውቷል። ከ2002 እስከ 2016  ለሽቱትጋርት 96 ጊዜ  ተሰልፎ 14 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፤ 10 አመቻችቷል። በ20 ዓመቱ በ2016 ለላይፕሲሽ መሰለፍ የጀመረው ቲሞ በ124 ጨዋታዎች 75 ግብ አስቆጥሮ 35 ማመቻቸት ችሏል።

በቡንደስሊጋ 219 ጊዜ ተሰልፎ 88 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ በጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ DVB Pokal 16 ጊዜ ተሰልፎ  7 አስቆጥሯል። 14 ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሰልፎ  7 ግብ ከመረብ አሳርፏል።  ለአውሮጳ ሊግ 6 ጊዜ ተጫውቶ 4 ኳሶችን አስቆጥሯል። ግብ ማስቆጠር ባይችልም 4 ጊዜ ለአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ ተሳትፏል። በዚያ ላይ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን 29 ጊዜ መሰለፍ ችሏል።

Fußball Bundesliga Hoffenheim - RB Leipzig
ምስል Getty Images/U. Anspach

ቲሞ ቬርነር ፈጣን ነው። በክንፍም በመኻልም ኾኖ የማጥቃት ችሎታ አለው። በዘንድሮ ውድድር  በ31 ጨዋታ 25 ግብ አስቆጥሯል፤ 9 አመቻችቷል። ነውጠኛ የሚባል አጥቂ አይደለም። ትኩረቱ ኹሉ ኳሷ እና ግቡ ላይ ይመስላል። በዘንድሮ ግጥሚያ ቀይ ዐይቶ አያቅም አራቴ ቢጫ ተሰጥቶታል። ሌቫንዶቭስኪ በ28 ጨዋታ  30 ግቦች አሉት።  3ኛ ጄደን ሳንቾ በ29 ጨዋታ 17 ግቦች አሉት።

ላይፕሲሽ ዐርብ እለተ ሆፈንሃይምን 2 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ቲሞ ቬርነር  ግብ አላስቆጠረም። አማካዩ ዳኒ ኦልሞ ነው በ9 እና 11 ደቂቃ ላይ 2 ግቦችን ያስቆጠረው። ቲሞ ቬርነር ከሌላኛው አጥቂ ፓትሪክ ሺክ (24 ዓመት) ጋር ጎን ለጎን ኾኖ በ2 አጥቂ ነበር የተጫወቱት። ቡድኑ 3ኛ ኾኖ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን አስጠብቋል። ሆፈንሃይም ለአውሮጳ ሊግ የነበረው ተስፋ ተመናምኗል፤ 7ኛ ደረጃ።

የ24 ዓመቱ አጥቂ ለጁሊያን ናግልስማን ቡድን በጨዋታ ዘመኑ ጨራሽ የሚባል ነበር። 31 ግቦችን አስቆጥሯል። ሆፍንሃይም ላይ አለማስቆጠሩ የቸልሲ ደጋፊዎችን ስጋት አጭሮባቸዋል። ከሆፍንሃይሙ ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ባውማን ጋር ፊት ፊት ተገናኝተው ኳሷን ከአግዳሚው በላይ ነው የላካት።

እንደ አንድሬ ሼቭቼንኮ እና ፈርናንዶ ቶሬስ ያሉ የዓለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂዎች የነበሩት ቸልሲ የአጥቂ ርግማን የወረደበት ይመስላል። አልቫሮ ሞራቶ (በውሰት ለአትሌቲኮ ማድሪድ ነው የሚጫወተው) በ2017 በከፍተኛ ገንዘብ ዲዬጎ ኮስታን (አትሌቲኮ ማድሪድ) ቢተካም ያን ያኽል ለውጥ አላመጣም።

ወደ ቸልሲ ሊኼድ ነው ከተባለበት ጊዜ አንስቶ 4 ሙከራዎች አድርጎ አንዱም ወደ ግብ አልነበረም። 1 ወሳኝ ግብ ጭራሽ ስቷል። አንድም አላገባም። በዚህም አለ በዚያ ግን ቲሞ ቬርነር በእርግጥም በግብ እጦት ለሚሰቃየው ቸልሲ እጅግ አስፈላጊው ነው። የቸልሲ አጥቂዎች በፕሬሚየር ሊጉ የሚጠበቅባቸውን ያኽል ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ቆይተዋል።

Fußball RB Leipzig Timo Werner mit hochgestülptem Kragen
ምስል picture-alliance/dpa/U. Anspach

ለቸልሲ ዘንድሮ ብዙ ግብ አስቆጠረ የተባለው አጥቂ እንግሊዛዊው ቲሚ አብራሃም በ25 ጨዋታ 13 ግብ ነው ማግባት የቻለው፤ 3 ብቻ አመቻችቷል። በአንጻሩ ቲሞ ቬርነር በዘንድሮ ውድድር  በ31 ጨዋታ 25 ግብ አስቆጥሯል፤ 9 አመቻችቷል። ሌላኛው የቸልሲ ዐይን ውስጥ ያረፈው አማካዩ ካይ ሐቫርትስ ግን ዘንድሮ በቡንደስሊጋ የጨዋታ ዘመን በ27 ጨዋታዎች 11 ግብ አስቆጥሯል 5 አመቻችቷል።  

የብራዚሉ  ዊሊያም በ28 ጨዋታ ለቸልሲ ተሰልፎ 5 አስቆጥሮ 5 አመቻችቷል። እንግሊዛዊው ካሉም ሑድሰን ኦዶይ በ17 ጊዜ መሰለፍ 1 አግብቶ 4 አመቻችቷል። ሚቺ ባትሹዋይ 16 ጊዜ ተሰልፎ ያገባው 1ዴ ነው፤ 1 ብቻ አመቻችቷል። ኦሊቨር ጂሩ እና ፔድሮም 9 ጨዋታ ላይ 2 እና 1 ነው ያገቡት። ጂሩ ምንም አላመቻቸም ፔድሮ 1 አመቻችቷል። ከአማካዮች ብዙ ያገባው ማሶን ሞንት ነው፤ በ29 ጨዋታ 6 አግብቷል 4 አመቻችቷል። ሌሎቹ ከዚያ ያነሰ ነው ያላቸው። ስለዚህም ቸልሲ የግብ አዳኝ እና ፈጣን የኾኑት ጀርመናዊ ወጣቶችን ማስመጣቱ በእርግጥም አስፈላጊው ነው።

ከዚያ ባሻገር ቸልሲ ላምፓርድን ለጊዜው እንጂ በቋሚነት የሚፈልገው የኤርቢ ላይፕሲሹ የ32 ዓመቱ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንን ነው ሲል ትራንስፈር ማርኬት  ዘግቧል። 

ናግልስማን በ31 ጨዋታዎች የተሸነፉት 3ቴ ብቻ ነው። 11 ጊዜ አቻ ሲወጡ 17 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። ከላይፕሲሽ ጋር የገቡት ውላቸው እስከ 2023 ድረስ የሚቆይ ነው። አሰልጣኙን ሪያል ማድሪድም ይፈልጋቸዋል። በቋንቋ ችግር የተነሳ ግን የስፔኑ የማይኾን ይመስላል።

Deutschland Bundesliga RB Leipzig gegen Freiburg | Nagelsmann
ምስል Reuters/J. Woitas

የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ቤርንድ ሌኖ ቸልሲ ቲሞን ለማስፈረም መወሰኑን አወድሷል። ቲሞ እና ቤርንድ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊዎች ናቸው። ኹለቱም በሽቱትጋርት አካዳሚ ያደጉ ናቸው። እንግዲህ ቸልሲ ለቲሞ ቬርነር ዝውውር 53 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲኹም በሳምንት 170,000 ፓውንድ ሊከፈለው መስማማቱ ተገልጧል።  በጀርመናዊው አሰልጣኝ የሚመራው ሊቨርፑልም ሊያስመጣው ፈልጎ ነበር። ለሊቨርፑል ግን ተቸዋቹ የተወደደበት ይመስላል።

የባየር ሌቨርኩሰኑ ካይ ሐቫርትስ፤ ገና የ21 ዓመት ወጣት ጀርመናዊ አማካይ ነው። ይኸው ቸልሲ በ89 ሚሊዮን ዩሮ ሊወስደው እንደኾነ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ካይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ ለባየር ሌቨርኩሰን ተሰልፎ ነው የሚጫወተው። ኳስ የጀመረው ከአራት ዓመቱ አንስቶ ማርያዶርፍ የተባለች መንደር ውስጥ በአለማኒያ ማሪያዶርፍ ከ2003 እስከ 2009 በመጫወት ነው። ማርያ ዶርፍ ከአኸን ከተማ በስተሰሜን ነው የምትገኘው (397 ኪሎ ሜትር በመኪና የ3 ሰአት መንገድ ነው)። ከቦን ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ቤልጂየም ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።

ቤተሰቡ ኳስ በጣም ይወዳሉ። ከአባቱ እና ከወንድሙ ይልቅ ግን አያቱ ናቸው በልጅነቱ ኳስ ተጨዋች እንዲኾን መሠረት የጣሉለት። አያቱ ሪቻርድ የአለማኒያ ማሪያዶርፍ  የረዥም ጊዜ ሊቀመንበር ነበሩ። አባቱ ፖሊስ እናቱ ጠበቃ ናቸው።

Fotomontage Nico Kovac Hertha BSC Berlin
ምስል picture-alliance/SvenSimon/F. Hoermann

ከዛ ለአለማኒያ አኸን አንድ ዓመት ተጫውቶ በ11 ዓመቱ ባየር ሌቨርኩሰንን ተቀላቀለ። በባየርን ሌቨርኩሰን ታሪክ በ17 ዓመቱ 126 ቀናት በመሰለፍ የመጀመሪያው በእድሜ ትንሹ ተጫዋች መኾንም የቻለ ነው። ያኔም በቡንደስሊጋው ከ24ኛ ዙር ጨዋታ አንስቶ ተሰልፎ 4 በማግባት 6 ኳስ አመቻችቷል።

በቡንደስሊጋ 115 ተጫውቶ 35 ግቦችን አስቆጥሯል፤ 24 አመቻችቷል፡፡ በጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ (DVB Pokal) 12 ጊዜ ተሰልፎ 2 አስቆጥሯል። 8 ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሰልፎ  አንድም ግብ አላስቆጠረም። በአንጻሩ ለአውሮጳ ሊግ 9 ጊዜ ተጫውቶ 6 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል። ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን 7 ጊዜ መሰለፍ ችሏል።

በዘንድሮ የቡንደስሊጋ የጨዋታ ዘመን በ27 ጨዋታዎች 11 ግብ አስቆጥሯል 5 አመቻችቷል።

በቡንደስሊጋው በአንድ የጨዋታ ዘመን 17 ግብ ያገባ የመጀመሪያው ታዳጊ በመኾን ባለፈው የጨዋታ ዘመን ታሪክ አስመዝግቧል። 

ታዳጊ ተጨዋች ኾኖ በአንድ የቡንደስሊጋ የጨዋታ ዘመን 12 ግቦችን በማስቆጠር ከ45 ዓመታት ወዲህም የመጀመሪያው መኾን ችሏል። ዲተር ሙይለር በ1973 እስከ 74 የጨዋታ ዘመን  ነበር እንደዚያ ያስቆጠረው።

ባየር ሙይንሽን ባለፈው 4 ለ2 ባሸነፈበት ጨዋታ ካይን ለመውሰድ ገምግሞ ነበር። ግን የጡንቻ ችግር ስለነበረበት በዚያ ችግር ብቻ ትቶታል የሚል ዘገባ ወጥቷል። በዚያ ላይ ቶማስ ሙይለር እኛ ከደሞዛችን ለኮሮና እየተሰጠ 100 ሚሊዮን ዩሮ ለአንድ ተጨዋች ያለው መነጋገሪያ ኾኖ ነበር።

Fußball Spanien La Liga RCD Mallorca v FC Barcelona Messi
ምስል Reuters/A. Gea

ለባርሴሎና ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ አጨዋወት የሚመች ነው። ብዙ ኳሶችን በረዥምም በአጭርም ማቀበል የተካነ ነው። ከ10 ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳቪድ ሲልቫ (ወደ አጥቂነት ያዘነበለ አማካይ (offensive midfield) ሲቲን ለቆ ወደ ካታሩ አል ዱኃይል ቡድን ለመዛወር እየጨረሰ መኾኑ ስለተነገረ፤ ለካይ ሐቫርትስ የፔፕ ጓርዲዮላ ሲቲ የተመቸ ይኾን ነበር። ጋርዲዮላ ወጣት ተጨዋቾችን ማሳደግ ይወዳል።

ማንቸስተር ሲቲ ወይንም ባርሴሎናም ቢሔድ ይሳካለት ነበር። ኳስ ይዞ የመጫወት ብቃት አለው። ፈጣንም ነው። በቡንደስሊጋው ፈጣኑ አማካይ ተብሎም ይታወቃል። 35 ኪሜ በሰአት መሮጥ ይችላል በ2018። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ብዙ ጊዜ ኳስ ይዞ ስለሚጫወት ከሌሎቹ የቡንደስሊጋ ቡድኖች አንፃር ለካይ የተመቸ ነበር።  ባለፈው የጨዋታ ዘመን ለአብነት ያኽል ዶርትሙንድ 69 ከመቶ ኳስ ይዞ በመጫወት ከኹልም በልጦ ነበር። ጁሊያን ብራንድት አብሮት ተጫውቶ ስለነበር ለመላመድም አይከብደውም ነበር።

የገንዘብ ጉዳይ ነው ወደ ቦሩስያ እንዳይመጣ ያደረገው። ከፍተኛ የዓመት ተከፋዮች በቦሩስያ ዶርትሙንድ፦ ማርኮ ሮይስ 12 ሚሊዮን፤ ማትስ ሑመል 10 ሚሊዮን፤ ማሪዮ ጎይትሰ 10 ሚሊዮን፤ አክሰል ዊትሰል 7,5 ሚሊዮን ዩሮ ናቸው። ለካይ ባየር ሌቨርኩሰን መጀመሪያ ላይ የጠየቀው 100 ሚሊዮን ዩሮ ነው። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጠቃላይ የተጨዋቾች ደሞዝን የሚበልጥ ክፍያ ነው የተጠየቀው።

Fußball Bundesliga Kai Havertz Bayer Leverkusen
ምስል Getty Images/AFP/I. Fassbender

ለባየር ሙይንሽንም መጫወት ይችል ነበር። ግብ የማስቆጠር ብቃት አለው። ባየር ሙይንሽን በሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ግብ ማስቆጠር ላይ ነው የተመሰረተው። ባለፈው ሌቫንዶቭስኪ በሌለበት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህን በስቃይ  ነው 2 ለ1 ያሸነፈው። ባየርን አማካይ ላይ በርትቶ መጫወት የሚሻ ቡድን ነው፤ ይኼም ይመቸዋል። ከአማካይ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት የሚሻሙ ኳሶችን በመጠቀም እንደ ባየር ሙይንሽን ያለቡድን የለም በቡንደስሊጋው። ይኼም ለካይ የሚመች ነው። በማስጨነቅ ስልት ኳስን መልሶ የመቆጣጠር ጨዋታ (pressing)ባየርን የሚታወቅበት ነው። ካይ ከ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አምበል ማርኮ ሮይስ ወደ እኛ ለማስመጣት እጥራለኹ ብሎ ነበር ቀደም ሲል ባይሳካለትም።

ላሊጋ

የስፔን ላሊጋ ባሳለፍነው ሳምንት ዳግም ከመጀመሩ አስቀድሞ የሊጉ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ተወካይ ኦሊቨር ዶድ ከምስራቅ አፍሪቃ ለተወጣጡ ጋዜጠኞች አጠቃላይ ገለፃ  አድርገዋል። እንደኦሊቨር ገለፃ ከሆነ፦ ላሊጋ ከጀርመን ቡንደስሊጋ ልምዶችን ወስዶ የኮሮና ተሐዋሲን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ነው። ተጨዋቾች በተቀያሪ ወንበር ላይ ሲቀመጡ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያጠልቁ እንደሚደረግ እና ጨዋታዎች በዝግ በመደረጋቸው ምክንያት የሚደበዝዘውን የስታዲየሞች ድባብ ለማምጣት ምናባዊ (virtual) የደጋፊዎች ድምፅ እንደሚደመጥ አስረድተዋል።

Spanien Fußball | FC Barcelona vs Real Madrid
ምስል imago images/Agencia EFE/E. Fontcuberta

ኦሊቨር ከቡንደስሊጋ የስፔኑ አቻው ትምህርት መውሰዱን እንደአዎንታዊ ጎን አንስተዋል። «እርስ በእርስ ትምህርት እየወሰድን ነው።  እኔ እንደማስበው የቡንደስሊጋ ቀድሞ መጀመር ለእኛ ጥቅም አለው ምክንያቱም ምን በጥሩ ኹኔታ እንደቀጠለ እና ምን እንዳልሠራ ለመረዳት አስችሎናል። በእርግጥ ቡዙ ነገሮች ሠርተዋል ስለዚህም አዎንታዊ የሆኑትን ወስደን ለማሻሻል ሞክረናል። ቡንደስሊጋ የከወናቸው ኹሉንም በጎ ተግባራት ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው።»

በገለፃው ላይ የተሳተፈው የቀድሞ የቫሌንሲያ እና ባርሴሎና አማካይ ጋይዝካ ሜንዴይታ ለተነሱለት ጥያቄዎች መልስ የሰጠ ሲሆን፤ የቀድሞ ክለቡ ቫሌንሲያ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን የማግኘቱ ጉዳይ ተስፋ ያለው መሆኑን ለዶይቼ ቬሌ ተናግሯል።

«ቫሌንሲያ የሚያውቁ ሁሉ ክለቡ ዋንጫ እንዲያሸንፍ ወይም ደግሞ ለዋንጫ እንዲፎካከር ይፈልጋል። ይህ በእኔም የተጫዋችነት ጊዜ የነበረ አስተሳሰብ ነው። ዘንድሮ በክለቡ ውስጥ የተወሰኑ ለውጦች ተደርገዋል። በእነማርሴሊኖ እና ሳላዴስ ስር የሚፈልጉትን የጨዋታ ባህል እያግኙ ነው። ለቻምፒየንስ ሊግ ማለፍ የሚቻል ነገር ነው። የነጥብ ልዩነቱ ጠባብ ነው፤ ነገር ግን ቀላል አይሆንም እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ጌታፌ፣ ሪያል ሶሴይዳድ እና ሲቪያ ለማለፍ እየተፎካከሩ ነው። ስለዚህም ቫሌንሲያ ለማለፍ ብቃቱ እንዳለው አምናለው።»

በስብሰባው ላይ የተሳተፉትን ባለሞያዎች አነጋግሮ ዘገባውን ከአዲስ አበባ የላከልን ኦምና ታደለ ነው። ቫሌንሲያ ዘንድሮ ከመሪው ባርሴሎና በ18 ነጥብ ልዩነት ርቆ 7ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ቅዳሜ ማዮርካን 4 ለ0 ያሸነፈው መሪው ባርሴሎና 61 ነጥብ ይዞ ተከታዩ ሪያል ማድሪድን በ2 ነጥብ ይበልጣል።

አትሌቲክስ

Symbolbild Sport Jogging
ምስል picture-alliance/Zuma Press/El Nuevo Dia de Puerto Rico/Jupiterimages

40ኛ ዓመቱን መስከረም ወር ላይ የሚደፍነው ታላቊ የሰሜን ሩጫ የሚባለው የብሪታንያ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ፉክክር በኮሮና ተሐዋሲ የተነሳ ዘንድሮ እንደማይከናወን አዘጋጆቹ ዐስታወቊ። በውድድሩ ከ55,000 በላይ ሯጮች ሊሳተፉ ተመዝግበው ነበር። በኮሮና ተጽእኖ ውድድሩን ማካኼድ ባለመቻሉ እና በመሰረዙ ማዘናቸውን የሩጫው አዘጋጆች (GREAT NORTH RUN) ዛሬ በድረ ገጻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል። ተወዳዳሪዎች ለውድድሩ የከፈሉት ገንዘብ ለአስተዳደር ወጪ 5 ፓውንድ ተቀንሶ ከአንድ ወር ከ15 ቀን በኋላ እንደሚመለስላቸውም ዐስታውቀቃል። በሚቀጥለው ዓመት በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ዘንድሮ የከፈሉት ተቀማጭ ሊኾንላቸው እንደሚችልም አክለዋል። የሩጫ ውድድሩ መስከረም 3 ቀን፤ 2013 ዓም ነበር ይካኼዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው። ከዚሁ ውድድር ጋር በተያያዘ ይከናወኑ የነበሩት የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ እንዲሁም የወጣቶች እና ልጆች ውድድሮችም ተሰርዘዋል።

የፎርሙላ አንድ የዘንድሮ ውድድርን ለማድረግ አዘጋጆቹ ጥረት ቢያደርጉም ከአቅማቸው በላይ በመኾኑ  የጃፓን፣ ሲንጋፖር እና አዘርባጃን የመኪና ሽቅድምድሞች መሰረዛቸውን ያሳወቊት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነበር። በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት መሰረዛቸው ተገልጧል። ስምንት ውድድሮች ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በአውሮጳ ከተሞች ውስጥ ሊከናወኑ እንደሚችሉ ግን ተጠቅሷል። ከሽቅድምድሞቹ ኹለቱ ጀርመን ሆከንሐይም ከተሞች ውስጥ የሚከናወኑ ናቸው ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ