ሳምንታዊ የስፖርት ጥንቅር
ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2011በአፍሪካ አህጉራዊ የማጣሪያ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድኖች በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ ግጥሚያዎች ለቀጣይ ውድድር ማለፍ የሚያስችላቸው ውጤት ማስመዘገብ ተስኗቸዋል። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌሬሽን (ካፍ) የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት ሁለቱ ክለቦች በደርሶ መልስ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከውድድር ውጭ ሆነዋል።
በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ፊት ትላንት ነሐሴ 19 በመቐለ ስቴድየም የመልስ ግጥሚያውን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ ከኢኳቶሪያል ጊኒው ካኖ ስፖርት ጋር በአንድ ለአንድ አቻ ውጤት ተለያይቷል። ያገኟቸውን መልካም ዕድሎች ያመከኑት የመቐለ 70 እንደርታዎች ገና በቅድመ ማጣሪያ ከውድድር ውጭ ለመሆን ተገድደዋል።
ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታ ወደ ታንዛንያ ያመራው ፋሲል ከነማም ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ አልቻለም። ከአዲሱ አሰልጣኙ ስዩም ከበደ ጋር ወደ ስፍራው ያቀናው ቡድኑ ከትላንት በስቲያ ነሐሴ 18 ከአዛም ስፖርት ጋር ባደረው ግጥሚያ የሶስት ለአንድ ተሸንፏል። ፋሲል ከነማዎች ባህር ዳር ላይ ባደረጉት ቀዳሚ ጨዋታቸው ተጋጣሚያቸውን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ቢያሸንፉም እንደ እንደ መቐለ 70 እንደርታ ሁሉ ሶስት ለሁለት በሆነ የድምር ውጤት ከቅድመ ማጣሪያው ውድድር ተሰናብተዋል።
አትሌቲክስ
ቅዳሜ ምሽት በተካሄደው የፓሪስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊዎች ነበሩ። በሴቶቹ በ800 ሜትር ርቀት ጉዳፍ ጸጋይ ሰባተኛ ሆኗ ውድድሯን ብታጠናቅቅም የገባችበት አንድ ደቂቃ ከ59.52 ሰከንድ የግሏ ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። ውድድሩን ያሸነፈችው አሜሪካዊቷ ግሪን ሀና ነች።
በወንዶቹ የ3000 ሜትር የመሰናክል ውድድርም ኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጫላ በዮ ጥሩ ፉክክር በማሳየት ሶስተኛ እና አራተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል። በ1500 ሜትር ርቀት ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘገብ ተጠብቆ የነበረው ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ድል ሳይቀናው ቀርቷል። በሞሮኮዊ አትሌት ሂሻም ኤል ጉሩዥ ለ22 ዓመታት ተይዞ የነበረን የርቀቱን የቤት ውስጥ ክብረ ወሰን በዚህ ዓመት የሰበረው ሳሙኤል በፓሪሱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ዘጠነኛ ሆኖ ነው ውድድሩን የጨረሰው። ሳሙኤል ከውድድሩ በኋላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው የስልጠና ጫና በውድድሩ ውጤት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮበታል።
ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ሃይማኖት ጥሩነህ
ተስፋለም ወልደየስ